ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 22
22
1ዳዊትም እግዚአብሔር ከሳኦል እጅና ከጠላቶቹ እጅ ሁሉ ባዳነው ቀን የዚህን ቅኔ ቃል ለእግዚአብሔር ተናገረ። 2እንዲህም አለ፦ እግዚአብሔር ዓለቴ አምባዬ መድኃኒቴ ነው፥ 3እግዚአብሔር ጠባቂያ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ፥ ጋሻዬና የረድኤቴ ቀንድ፥ መጠጊያዬና መሸሸጊያዬ፥ መድኃኒቴ ሆይ፥ ከግፍ ሥራ ታድነኛለህ። 4ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፥ ከጠላቶቼም እድናለሁ። 5የሞት ጣር ያዘኝ፥ የዓመፅ ፈሳሽም አስፈራኝ፥ 6የሲኦል ጣር ከበበኝ፥ የሞት ወጥመድ ደረሰብኝ። 7በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፥ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኽቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ። 8ምድርም ተንቀጠቀጠች፥ ተናወጠችም፥ የሰማዮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፥ እግዚአብሔርም ተቆጥቶአልና ተንቀጠቀጡ። 9ከቁጣው ጢስ ወጣ፥ ከአፉም የሚበላ እሳት ነደደ፥ ፍምም ከእርሱ በራ። 10ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ፥ ወረደም፥ ጨለማም ከእግሩ በታች ነበረ። 11በኪሩብም ላይ ተቀምቶ በረረ፥ በነፋስም ክንፍ ሆኖ ታየ፥ 12መሰወርያውን ጨለማ፥ በዙሪያውም የነበረውን ድንኳን፥ በደመና ውስጥ የነበረ የጨለማ ውኃ አደረገ። 13በፊቱም ካለው ብርሃን የተነሣ ፍም ተቃጠለ። 14እግዚአብሔርም ከሰማያት አንጎደጎደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ፥ 15ፍላጻውን ላከ፥ በተናቸውም፥ መብረቆችን ላከ፥ አወካቸውም። 16ከእግዚአብሔር ዘለፋ፥ ከመዓቱም መንፈስ እስትንፋስ የተነሣ፥ የባሕር ፈሳሾች ታዩ፥ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ። 17ከላይ ሰደደ፥ ወሰደኝም፥ ከብዙ ውኆችም አወጣኝ። 18ከብርቱዎች ጠላቶቼ፥ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፥ በርትተውብኝ ነበርና። 19በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፥ እግዚአብሔር ግን ደገፋዬ ሆነ። 20ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፥ ወድዶኛልና አዳነኝ። 21እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፥ እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል፥ 22የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁምና። 23ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፥ ከሥርዓቱም አልራቅሁምና። 24በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ። 25እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ፥ እንደ እጄም ንጽሕና በዓይኖቹ ፊት መለሰልኝ። 26ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፥ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፥ 27ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፥ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ። 28አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፥ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ። 29አቤቱ፥ አንተ መብራቴ ነህና፥ እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል። 30በአንተ ኃይል በጭፍራ ላይ እሮጣለሁና፥ በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁና። 31የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው፥ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፥ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው። 32ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችንስ በቀር አምባ ማን ነው? 33ኃይልን የሚያስታጥቀኝ፥ መንገዴንም የሚያቃና፥ 34እግሮቼን እንደ ብሆር እግሮች የሚያረታ፥ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው። 35እጆቼን ሰልፍ ያስተምራል፥ በክንዴ የናስ ቀስት እገትራለሁ። 36የማዳንህንም ጋሻ ሰጠኸኝ፥ ተግሣጽህም አሳደገኝ። 37አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፥ እግሮቼም አልተንሸራተቱም። 38ጠላቶቼን አሳድዳቸዋለሁ፥ አጠፋቸውማለሁ፥ እስካጠፋቸውም ድረስ አልመለስም። 39አስጨንቃቸዋለሁ መቆምም አይችሉም፥ ከእግሬም በታች ይወድቃሉ። 40ለሰልፍም ኃይልን ታስታጥቀኛለህ፥ በላዬ የቆሙትን በበታቼ ታስገዛቸዋለህ። 41የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ፥ የሚጠሉኝንም አጠፋሃቸው። 42ጮኹ፥ የሚረዳቸውም አልነበረም፥ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ አልሰማቸውምም። 43እንደ ምድር ትቢያ ፈጨኋቸው፥ እንደ አደባባይም ጭቃ ረገጥኋቸው፥ ደቀደቅኋቸውም። 44ከሕዝብ ክርክር ታድነኛለህ፥ የአሕዛብም ራስ አድርገህ ትሾመኛለህ፥ የማላውቀው ሕዝብም ይገዛልኛል። 45የባዕድ ልጆች ደለሉኝ፥ በጆሮ ሰምተው ተገዙልኝ። 46የባዕድ ልጆች እየጠፉ ይሄዳሉ፥ ከተዘጉ ስፍሮች እየተንቀጠቁ ይወጣሉ። 47እግዚአብሔር ሕያው ነው፥ ጠባቂዬም፥ ቡሩክ ነው፥ የመድኃኒቴ ጠባቂ አምላኬ ከፍ ከፍ ይበል፥ 48በቀሌን የሚመልስልኝ አምላክ፥ አሕዛብን በበታቼ የሚያስገዛ፥ 49ከጠላቶቼ የሚያወጣኝ እርሱ ነው፥ በእኔም ላይ ከቆሙ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፥ ከግፈኛ ሰው ታድነኛለህ። 50አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም እዘምራለሁ። 51የንጉሡን መድኃኒት ታላቅ ያደርጋል፥ ቸርነቱንም ለቀባው፥ ለዳዊትና ለዘሩ፥ ለዘላለም ይሰጣል።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 22: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ