የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ሳሙኤል 2:1-32

2 ሳሙኤል 2:1-32 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከዚ​ያም በኋላ ዳዊት፥ “ከይ​ሁዳ ከተ​ሞች ወደ አን​ዲቱ ልው​ጣን?” ብሎ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ጠየቀ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም፥ “ውጣ” አለው። ዳዊ​ትም፥ “ወዴት ልውጣ?” አለ። እር​ሱም፥ “ወደ ኬብ​ሮን ውጣ” አለው። ዳዊ​ትም ከሁ​ለቱ ሚስ​ቶቹ ከኢ​ይ​ዝ​ራ​ኤ​ላ​ዊቱ ከአ​ኪ​ና​ሆ​ምና የቀ​ር​ሜ​ሎ​ሳ​ዊው የና​ባል ሚስት ከነ​በ​ረ​ችው ከአ​ቤ​ግያ ጋር ወደ​ዚያ ወደ ኬብ​ሮን ወጣ። ከእ​ር​ሱም ጋር የነ​በ​ሩት ሰዎች ሁሉ ከቤተ ሰባ​ቸው ጋር ወጡ፤ በኬ​ብ​ሮ​ንም ከተ​ሞች ተቀ​መጡ። የይ​ሁ​ዳም ሰዎች መጥ​ተው በይ​ሁዳ ቤት ይነ​ግሥ ዘንድ ዳዊ​ትን በዚያ ቀቡት። ሳኦ​ልን የቀ​በ​ሩት የኢ​ያ​ቢስ ገለ​ዓድ ሰዎች ናቸው ብለው ለዳ​ዊት ነገ​ሩት። ዳዊ​ትም ወደ ኢያ​ቢስ ገለ​ዓድ ገዦች መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ችን ላከ፤ ዳዊ​ትም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እና​ንተ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለቀ​ባው ለጌ​ታ​ችሁ ለሳ​ኦል ይህን ቸር​ነት አድ​ር​ጋ​ች​ኋ​ልና፥ እር​ሱ​ንና ልጁን ዮና​ታ​ን​ንም ቀብ​ራ​ች​ኋ​ቸ​ዋ​ልና በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የተ​ባ​ረ​ካ​ችሁ ሁኑ። አሁ​ንም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ምሕ​ረ​ት​ንና ጽድ​ቅን ያድ​ር​ግ​ላ​ችሁ፤ ይህ​ንም ነገር አድ​ር​ጋ​ች​ኋ​ልና እኔ ደግሞ ይህን በጎ​ነት እመ​ል​ስ​ላ​ች​ኋ​ለሁ። አሁ​ንም ጌታ​ችሁ ሳኦል ሞቶ​አ​ልና እጃ​ችሁ ትጽና፤ እና​ን​ተም በርቱ፤ የይ​ሁ​ዳም ቤት በእ​ነ​ርሱ ላይ ንጉሥ እሆን ዘንድ ቀብ​ተ​ው​ኛል።” የሳ​ኦ​ልም ጭፍራ አለቃ የኔር ልጅ አበ​ኔር የሳ​ኦ​ልን ልጅ ኢያ​ቡ​ስ​ቴን ወስዶ ከሰ​ፈር ወደ መሃ​ና​ይም አወ​ጣው፤ በገ​ለ​ዓ​ድና በታ​ሲሪ፥ በኢ​ይ​ዝ​ራ​ኤ​ልም፥ በኤ​ፍ​ሬ​ምም፥ በብ​ን​ያ​ምም፥ በእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ሁሉ ላይ አነ​ገ​ሠው። የሳ​ኦል ልጅ ኢያ​ቡ​ስ​ቴም በእ​ስ​ራ​ኤል ላይ በነ​ገሠ ጊዜ አርባ ዓመት ሆኖት ነበረ፤ ዳዊ​ትን ከተ​ከ​ተ​ሉት ከይ​ሁዳ ወገ​ኖች ብቻ በቀር ሁለት ዓመት ነገሠ። ዳዊ​ትም በይ​ሁዳ ቤት በኬ​ብ​ሮን የነ​ገ​ሠ​በት ዘመን ሰባት ዓመት ከስ​ድ​ስት ወር ነበረ። የኔር ልጅ አበ​ኔ​ርና የሳ​ኦል ልጅ የኢ​ያ​ቡ​ስቴ ብላ​ቴ​ኖች ከመ​ሃ​ና​ይም ወደ ገባ​ዖን ወጡ። የሶ​ር​ህያ ልጅ ኢዮ​አ​ብና የዳ​ዊት ብላ​ቴ​ኖች ከኬ​ብ​ሮን ወጥ​ተው በገ​ባ​ዖን ውኃ መቆ​ሚያ አጠ​ገብ ተገ​ና​ኙ​አ​ቸው፤ በው​ኃ​ውም መቆ​ሚያ በአ​ንዱ ወገን እነ​ዚህ፥ በሌ​ላ​ውም ወገን እነ​ዚያ ሆነው ተቀ​መጡ። አበ​ኔ​ርም ኢዮ​አ​ብን፥ “ጐል​ማ​ሶ​ቻ​ችን ይነሡ፤ በፊ​ታ​ች​ንም ይቈ​ራ​ቈሱ” አለው፤ ኢዮ​አ​ብም፥ “ይነሡ” አለ። ለሳ​ኦል ልጅ ለኢ​ያ​ቡ​ስቴ ከብ​ን​ያም ልጆች ዐሥራ ሁለት፥ ከዳ​ዊ​ትም ብላ​ቴ​ኖች ዐሥራ ሁለት ተቈ​ጥ​ረው ተነሡ። ሁሉም እያ​ን​ዳ​ንዱ የወ​ደ​ረ​ኛ​ውን ራስ በእጁ ያዘ፤ ሰይ​ፉ​ንም በወ​ደ​ረ​ኛው ጐን ሻጠ፤ ተያ​ይ​ዘ​ውም ወደቁ። የዚ​ያም ስፍራ ስም “በገ​ባ​ዖን የሸ​መቁ ሰዎች ድርሻ” ተብሎ ተጠራ፤ በዚ​ያም ቀን እጅግ ጽኑ ሰልፍ ሆነ፤ በዳ​ዊ​ትም ሰዎች ፊት አበ​ኔ​ርና የእ​ስ​ራ​ኤል ሰዎች ተሸ​ነፉ። በዚ​ያም ሦስቱ የሦ​ር​ህያ ልጆች ኢዮ​አ​ብና አቢሳ፥ አሣ​ሄ​ልም ነበሩ፤ የአ​ሣ​ሄ​ልም እግ​ሮቹ ፈጣ​ኖች ነበሩ፤ እንደ ዱር ሚዳ​ቋም ሯጭ ነበረ። አሣ​ሄ​ልም የአ​በ​ኔ​ርን ፍለጋ ተከ​ታ​ተለ፤ አበ​ኔ​ር​ንም ከማ​ሳ​ደድ ቀኝና ግራ አላ​ለም። አበ​ኔ​ርም ወደ ኋላው ተመ​ልሶ፥ “አንተ አሣ​ሄል ነህን?” አለው። እር​ሱም፥ “አዎ፥ እኔ ነኝ” አለው። አበ​ኔ​ርም፥ “ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ፈቀቅ በል፤ ከብ​ላ​ቴ​ኖ​ቹም አንድ ጐል​ማሳ ያዝ፤ መሣ​ሪ​ያ​ው​ንም ለራ​ስህ ውሰድ” አለው። አሣ​ሄል ግን እር​ሱን ከማ​ሳ​ደድ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ። አበ​ኔ​ርም አሣ​ሄ​ልን፥ “ከም​ድር ጋር እን​ዳ​ላ​ጣ​ብ​ቅህ እኔን ከማ​ሳ​ደድ ፈቀቅ በል፤ ወደ ወን​ድ​ምህ ወደ ኢዮ​አብ ፊቴን አቅ​ንቼ አይ ዘንድ እን​ዴት ይቻ​ለ​ኛል? እን​ደ​ዚህ አይ​ሆ​ን​ምና ወደ ወን​ድ​ምህ ወደ ኢዮ​አብ ተመ​ለስ” አለው። ነገር ግን ከእ​ርሱ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ። አበ​ኔ​ርም በጦሩ ጫፍ ወገ​ቡን ወጋው፤ ጦሩም በኋ​ላው ወጣ፤ በዚ​ያም ስፍራ ወድቆ በበ​ታቹ ሞተ። አሣ​ሄ​ልም ወድቆ በሞ​ተ​በት ስፍራ የሚ​ያ​ልፍ ሁሉ ይቆም ነበር። ኢዮ​አ​ብና አቢ​ሳም አበ​ኔ​ርን አሳ​ደዱ፤ ፀሐ​ይም ጠለ​ቀች፤ እነ​ር​ሱም በገ​ባ​ዖን ምድረ በዳ መን​ገድ በጋይ ፊት ለፊት እስ​ካ​ለው እስከ አማን ኮረ​ብታ ድረስ መጡ። በአ​በ​ኔር ኋላ የነ​በሩ የብ​ን​ያ​ምም ልጆች ተሰ​በ​ሰቡ፥ በአ​ን​ድ​ነ​ትም ሆኑ፤ በአ​ንድ ኮረ​ብ​ታም ራስ ላይ ቆሙ። አበ​ኔ​ርም ኢዮ​አ​ብን ጠርቶ እን​ዲህ አለው፥ “ሰይፍ ለድል የም​ታ​ጠፋ አይ​ደ​ለ​ምን? ፍጻ​ሜ​ዋስ መራራ እንደ ሆነ አታ​ው​ቅ​ምን? ሕዝቡ ወን​ድ​ሞ​ቻ​ቸ​ውን ከማ​ሳ​ደድ ይመ​ለሱ ዘንድ ሕዝ​ቡን የማ​ት​ና​ገር እስከ መቼ ነው?” ኢዮ​አ​ብም፥ “ሕያው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን! ባት​ና​ገር ኖሮ ሕዝቡ ሁሉ በጥ​ዋት በወ​ን​ድ​ሞ​ቻ​ቸው ላይ በወጡ ነበር” አለ። ኢዮ​አ​ብም ቀንደ መለ​ከት ነፋ፤ ሕዝ​ቡም ሁሉ ተመ​ለሰ፤ ከዚ​ያም በኋላ እስ​ራ​ኤ​ልን አላ​ሳ​ደ​ዱ​አ​ቸ​ውም፤ ደግ​መ​ውም አል​ተ​ዋ​ጉም። አበ​ኔ​ርና ሰዎ​ቹም ሌሊ​ቱን ሁሉ ወደ ምዕ​ራብ ሄዱ፤ ዮር​ዳ​ኖ​ስ​ንም ተሻ​ገሩ፤ ያን ቀጥ​ተኛ መን​ገድ ካለፉ በኋ​ላም ወደ ሰፈር መጡ። ኢዮ​አ​ብም አበ​ኔ​ርን ከማ​ሳ​ደድ ተመ​ለሰ፤ ሕዝ​ቡ​ንም ሁሉ ሰበ​ሰበ፤ የዳ​ዊ​ት​ንም ብላ​ቴ​ኖች አስ​ቈ​ጠ​ራ​ቸው፤ የሞ​ቱ​ትም ሰዎች ከአ​ሣ​ሄል ሌላ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች ናቸው። የዳ​ዊ​ትም ብላ​ቴ​ኖች ከብ​ን​ያም እና ከአ​በ​ኔር ሰዎች ሦስት መቶ ስድሳ ሰዎ​ችን ገደሉ። አሣ​ሄ​ል​ንም አን​ሥ​ተው በቤተ ልሔም በአ​ባቱ መቃ​ብር ቀበ​ሩት፤ ኢዮ​አ​ብና ከእ​ርሱ ጋር የነ​በሩ ሰዎ​ቹም ሌሊ​ቱን ሁሉ፤ ሄዱ፥ በኬ​ብ​ሮ​ንም አነጉ።

2 ሳሙኤል 2:1-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚህ በኋላ ዳዊት፣ “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን?” ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን ውጣ” አለው። ዳዊትም፣ “ወደ የትኛዪቱ ልሂድ?” ሲል ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “ወደ ኬብሮን” ብሎ መለሰለት። ስለዚህ ዳዊት ከሁለቱ ሚስቶቹ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ ጋር ወደዚያ ወጣ። እንዲሁም ዳዊት አብረውት የነበሩትን ሰዎች ከነቤተ ሰቦቻቸው አመጣቸው፤ እነርሱም በኬብሮን ከተሞች ተቀመጡ። የይሁዳም ሰዎች ወደ ኬብሮን መጡ፤ በዚያም ዳዊትን ቀብተው በይሁዳ ቤት ላይ አነገሡት። ሳኦልን የቀበሩት የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች መሆናቸውን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ፣ እርሱም የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ይህን እንዲነግሩ መልእክተኞች ላከ፤ “በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ ጌታችሁን ሳኦልን በመቅበር በጎነት አሳይታችኋልና እግዚአብሔር ይባርካችሁ፤ አሁንም እግዚአብሔር ጽኑ ፍቅሩንና ታማኝነቱን ይግለጥላችሁ፤ እናንተ ይህን ስላደረጋችሁ፣ እኔም እንደዚሁ በጎ ነገር አደርግላችኋለሁ፤ እንግዲህ ጠንክሩ፤ በርቱ፤ ጌታችሁ ሳኦል ሞቷልና፤ የይሁዳ ቤትም እኔን ቀብተው በላያቸው አንግሠውኛል።” በዚህ ጊዜ የሳኦል ሰራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔር፣ የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደ መሃናይም አሻገረው፤ እርሱንም በገለዓድ፣ በአሴር፣ በኢይዝራኤል፣ በኤፍሬምና በብንያም እንዲሁም በእስራኤል ሁሉ ላይ አነገሠው። የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበረ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። የይሁዳ ቤት ግን ዳዊትን ተከተለ። ዳዊት በኬብሮን ንጉሥ ሆኖ እስራኤልን የገዛው ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ። የኔር ልጅ አበኔር፣ ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ አገልጋዮች ጋር ሆኖ ከመሃናይም ተነሥተው ወደ ገባዖን ሄዱ። እነርሱንም የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ሰዎች ወጥተው በገባዖን ኵሬ አጠገብ ተገናኟቸው፤ አንዱ ወገን በኵሬው ወዲህ ማዶ፣ ሌላው ወገን ደግሞ በኵሬው ወዲያ ማዶ ተቀመጠ። ከዚያም አበኔር፣ ኢዮአብን፣ “ከእናንተም ከእኛም ጕልማሶች ይነሡና በፊታችን በጨበጣ ውጊያ ይጋጠሙ” አለው። ኢዮአብም፣ “ይሁን እሺ ይጋጠሙ” ብሎ መለሰ። ስለዚህ ከብንያም ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ ዐሥራ ሁለት፣ ለዳዊት ደግሞ ዐሥራ ሁለት ሰዎች ተነሥተው ተቈጠሩ። ከዚያም እያንዳንዱ ሰው የባለጋራውን ራስ በመያዝ ሰይፉን በጐኑ እየሻጠበት ተያይዘው ወደቁ። ስለዚህም በገባዖን የሚገኘው ያ ቦታ “የሰይፍ ምድር” ተባለ። የዚያን ዕለቱ ጦርነት እጅግ ከባድ ነበር፤ አበኔርና የእስራኤል ሰዎች በዳዊት ሰዎች ድል ሆኑ። ሦስቱ የጽሩያ ወንዶች ልጆች ኢዮአብ፣ አቢሳና አሣሄል እዚያው ነበሩ። አሣሄል እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ፤ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሳይል አበኔርን ተከታተለው። አበኔርም ወደ ኋላው ዘወር ብሎ በመመልከት፣ “አሣሄል! አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰለት። ከዚያም አበኔር፣ “ወደ ቀኝህ ወይም ወደ ግራህ ዘወር በልና አንዱን ጕልማሳ ይዘህ መሣሪያውን ንጠቀው” አለው። አሣሄል ግን እርሱን መከታተሉን አልተወም ነበር። እንደ ገናም አበኔር፣ “እኔን መከታተል ብትተው ይሻልሃል፤ እኔስ ለምን ከመሬት ጋር ላጣብቅህ? ከዚያስ የወንድምህን የኢዮአብን ፊት ቀና ብዬ እንዴት አያለሁ?” አለው። አሣሄል ግን መከታተሉን አልተወም፤ ስለዚህ አበኔር በጦሩ ጫፍ ሆዱን ወጋው፣ ጦሩም በጀርባው ዘልቆ ወጣ፤ አሣሄልም እዚያው ወደቀ፤ ወዲያው ሞተ። እያንዳንዱም አሣሄል ወድቆ ወደ ሞተበት ስፍራ ሲደርስ ይቆም ነበር። ኢዮአብና አቢሳ ግን አበኔርን ተከታተሉት፤ እያሳደዱም ወደ ገባዖን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ከጋይ አጠገብ ወዳለው ወደ አማ ኰረብታ ሲደርሱ ፀሓይ ጠለቀች። ከዚያም የብንያም ሰዎች ወደ አበኔር ተሰብስበው ግንባር በመፍጠር በኰረብታው ጫፍ ላይ ተሰለፉ። አበኔር ኢዮአብን ጠርቶ፣ “ይህ ሰይፍ ዘላለም ማጥፋት አለበትን? ውጤቱ መራራ መሆኑን አንተስ ሳታውቀው ቀርተህ ነውን? ሰዎችህ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን እንዲያቆሙ ትእዛዝ የማትሰጣቸውስ እስከ መቼ ድረስ ነው?” አለው። ኢዮአብም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ባትናገር ኖሮ፣ ሰዎቹ እስኪነጋ ድረስ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን ባላቆሙም ነበር” ብሎ መለሰ። ስለዚህ ኢዮአብ ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ከዚያም በኋላ ሰዎቹ በሙሉ እስራኤልን ማሳደዱን ተው፤ ውጊያውም በዚሁ አበቃ። አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ዓረባን ዐልፈው ሄዱ፤ ከዚያም ዮርዳኖስን በመሻገር ቢትሮንን ሁሉ ዐልፈው ወደ መሃናይም መጡ። ከዚያም ኢዮአብ አበኔርን ማሳደዱን ትቶ ተመለሰ፤ ሰዎቹንም ሁሉ አንድ ላይ በሰበሰባቸው ጊዜ፣ ከዳዊት ሰዎች አሣሄልን ሳይጨምር፣ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች መጥፋታቸው ታወቀ። የዳዊት ሰዎች ግን ከአበኔር ጋር ከነበሩት ሦስት መቶ ስድሳ ብንያማውያን ገደሉ። አሣሄልንም ከወደቀበት አንሥተው በቤተ ልሔም በአባቱ መቃብር ቀበሩት። ከዚያም ኢዮአብና ሰዎቹ ሌሊቱን ሁሉ ሲገሠግሡ ዐድረው፣ ሲነጋ ኬብሮን ደረሱ።

2 ሳሙኤል 2:1-32 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከዚያም በኋላ ዳዊት፦ ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፦ ውጣ አለው። ዳዊትም፦ ወዴት ልውጣ? አለ። እርሱም፦ ወደ ኬብሮን ውጣ አለው። ዳዊትም ከሁለቱ ሚስቶቹ ከኢይዝራኤላዊቱ ከአኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ ጋር ወደዚያ ወጣ። ዳዊትም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎችና ቤተ ሰባቸውን ሁሉ አመጣ፥ በኬብሮንም ከተሞች ተቀመጡ። የይሁዳም ሰዎች መጥተው በይሁዳ ቤት ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን በዚያ ቀቡት። ዳዊትም ወደ ኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ አላቸው፦ እናንተ ለጌታችሁ ለሳኦል ይህን ቸርነት አድርጋችኋልና፥ ቀብራችሁትማልና በእግዚአብሔር የተባረካችሁ ሁኑ። አሁንም እግዚአብሔር ቸርነትንና እውነትን ያድርግላችሁ፥ ይህንም ነገር አድርጋችኋልና እኔ ደግሞ ይህን ቸርነት እመልስላችኋለሁ። አሁንም ጌታችሁ ሳኦል ሞቶአልና እጃችሁ ትጽና፥ እናንተም ጨክኑ፥ ዳግም የይሁዳ ቤት በእነርሱ ላይ ንጉሥ እሆን ዘንድ ቀብተውኛል። የሳኦልም ጭፍራ አለቃ የኔር ልጅ አበኔር የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደ መሃናይም አሻገረው፥ በገለዓድና በአሹራውያን በኢይዝራኤልም በኤፍሬምም በብንያምም በእስራኤልም ሁሉ ላይ አነገሠው። የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴም በእስራኤል ላይ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአርባ ዓመት ሰው ነበረ፥ ሁለት ዓመትም ነገሠ፥ ነገር ግን የይሁዳ ቤት ዳዊትን ተከተለ። ዳዊትም በይሁዳ ቤት ነግሦ በኬብሮን የተቀመጠበት ዘመን ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ። የኔር ልጅ አበኔርና የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ባሪያዎች ከመሃናይም ወደ ገባዖን ወጡ። የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ባሪያዎች ወጥተው በገባዖን ውኃ መቆሚያ አጠገብ ተገናኙአቸው፥ በውኃውም መቆሚያ በአንዱ ወገን እነዚህ፥ በሌላውም ወገን እነዚያ ሆነው ተቀመጡ። አበኔርም ኢዮአብን፦ ጕልማሶች ይነሡ፥ በፊታችንም ይቆራቆሱ አለው፥ ኢዮአብም፦ ይነሡ አለ። ለብንያም ወገንና ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ አሥራ ሁለት፥ ከዳዊትም ባሪያዎች አሥራ ሁለት ተቆጥረው ተነሡ። ሁሉም እያንዳንዱ የወደረኛውን ራስ ያዘ፥ ሰይፉንም በወደረኛው ጎን ሻጠ፥ ተያይዘውም ወደቁ። የዚያም ስፍራ ስም የስለታም ሰይፍ እርሻ ተብሎ ተጠራ፥ እርሱም በገባዖን ነው። በዚያም ቀን ጽኑ ሰልፍ ሆነ፥ በዳዊትም ባሪያዎች ፊት አበኔርና የእስራኤል ሰዎች ተሸነፉ። በዚያም ሦስቱ የጽሩያ ልጆች ኢዮአብና አቢሳ አሣሄልም ነበሩ፥ አሣሄልም እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ። አሣሄልም የአበኔርን ፍለጋ ተከታተለ፥ አበኔርንም ከማሳደድ ቀኝና ግራ አላለም። አበኔርም ዘወር ብሎ ተመለከተና፦ አንተ አሣሄል ነህን? አለ። እርሱም፦ እኔ ነኝ አለ። አበኔርም፦ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ፈቀቅ በል፥ አንድ ጕልማሳ ያዝ፥ መሣርያውንም ውስድ አለው። አሣሄል ግን እርሱን ከማሳደድ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ። አበኔርም አሣሄልን፦ ከምድር ጋር እንዳላጣብቅህ እኔን ከማሳደዱ ፈቀቅ በል፥ ወደ ወንድምህ ወደ ኢዮአብ ፊቴን አቅንቼ አይ ዘንድ እንዴት ይቻለኛል? አለው። ነገር ግን ከእርሱ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ፥ አበኔርም በጦሩ ጫፍ ሆዱን ወጋው፥ ጦሩም በኋላው ወጣ፥ በዚያም ስፍራ ወድቆ ሞተ። አሣሄልም ወድቆ በሞተበቱ ስፍራ የሚያልፍ ሁሉ ይቆም ነበር። ኢዮአብና አቢሳም አበኔርን አሳደዱ፥ በገባዖንም ምድረ በዳ መንገድ በጋድ ፊት ለፊት እስካለው እስከ አማ ኮረብታ ድረስ በወጡ ጊዜ ፀሐይ ጠለቀች። የብንያምም ልጆች ወደ አበኔር ተሰበሰቡ፥ በአንድነትም ሆኑ፥ በኮረብታም ራስ ላይ ቆሙ። አበኔርም ወደ ኢዮአብ ጮኸ፦ ሰይፍ በውኑ እስከ ዘላለም ያጠፋልን? ፍጻሜውሳ መራራ እንደ ሆነ አታውቅምን? ሕዝቡ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ ይመለሱ ዘንድ ሕዝቡን የማትናገር እስከ መቼ ነው? አለው። ኢዮአብም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ባትናገር ኖሮ ሕዝቡ በጥዋት ወጥተው በሄዱ ነበር፥ ወንድሞቻቸውንም ማሳደድ በተዉ ነበር አለ። ኢዮአብም ቀንደ መለከት ነፋ፥ ሕዝቡም ሁሉ ቆመ፥ ከዚያም በኋላ እስራኤልን አላሳደደም፥ ሰይፍም አላደረገም። አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ ዓረባ እያለፉ ሄዱ፥ ዮርዳኖስንም ተሻገሩ፥ ቢትሮንንም ሁሉ ካለፉ በኋላ ወደ መሃናይም መጡ። ኢዮአብም አበኔርን ከማሳደድ ተመለሰ፥ ሕዝቡንም ሁሉ ሰበሰበ፥ ከዳዊትም ባሪያዎች ከአሣሄል ሌላ አሥራ ዘጠኝ ሰዎች ጐደሉ። የዳዊትም ባሪያዎች ከብንያምና ከአበኔር ሰዎች ሦስት መቶ ስድሳ ያህል ገደሉ። አሣሄልንም አንሥተው በቤተ ልሔም በአባቱ መቃብር ቀበሩት፥ ኢዮአብና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ፥ በኬብሮንም አነጉ።

2 ሳሙኤል 2:1-32 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ዳዊት ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንድዋ ልውጣን? ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም “አዎ ውጣ” አለው። ዳዊትም “ወደ የትኛይቱ ከተማ ልሂድ?” ሲል ጠየቀ። እግዚአብሔርም “ወደ ኬብሮን ከተማ ሂድ” አለው። ስለዚህ ዳዊት ከሁለቱ ሚስቶቹ ጋር ወደ ኬብሮን ሄደ፤ እነርሱም የኢይዝራኤል ተወላጅ የሆነችው የአሒኖዓምና የቀርሜሎሳዊው የሟቹ የናባል ሚስት አቢጌል ነበሩ። እንዲሁም ዳዊት ተከታዮቹን ከነቤተሰባቸው ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ በኬብሮን ዙሪያ ባሉትም ታናናሽ ከተሞች ተቀመጡ። ከዚህ በኋላ የይሁዳ ሰዎች ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትንም ቀብተው የይሁዳ ንጉሥ አደረጉት። ዳዊት ገለዓዳውያን የሆኑ የያቤሽ ሰዎች ሳኦልን እንደ ቀበሩት በሰማ ጊዜ፥ ዳዊት ወደ ያቤሽ ገለዓድ ሰዎች መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ አላቸው፦ “እርሱን በመቅበር ለጌታችሁ ለሳኦል ቸርነትን ስላሳያችሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ። ደግሞም እግዚአብሔር ቸርነቱንና ታማኝነቱን ይግለጥላችሁ፤ እናንተ ስለ ፈጸማችሁት መልካም ነገር እኔም ለእናንተ ወሮታችሁን እመልሳለሁ። እንግዲህ ጠንክሩ! በርቱም! ጌታችሁ ሳኦል ሞቶአል፤ የይሁዳ ሕዝብ እኔን ቀብቶ አንግሦኛል።” የሳኦል ሠራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔር ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ ጋር የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር ወደ ማሕናይም ሸሽቶ ሄደ፤ በዚያም አበኔር ኢያቡስቴን በገለዓድ ግዛቶች፥ በአሴር፥ በኢይዝራኤል፥ በኤፍሬምና በብንያም ይኸውም በመላው እስራኤል ላይ እንዲነግሥ አደረገ። እርሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበር፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። የይሁዳ ነገድ ግን ዳዊትን ተከተለ፤ ዳዊትም በኬብሮን ተቀምጦ በመላው ይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ተኩል ነገሠ። አበኔርና የኢያቡስቴ ባለሟሎች ከማሕናይም ተነሥተው ወደ ገባዖን ከተማ መጡ፤ እናቱ ጸሩያ ተብላ የምትጠራው ኢዮአብና ሌሎቹም የዳዊት ባለሥልጣኖች ወጥተው በገባዖን ኲሬ ውሃ አጠገብ ተገናኙ፤ ሁሉም በቡድን ተከፋፍለው በኲሬው ውሃ ማዶ ለማዶ ተቀምጠው ነበር። በዚህ ጊዜ አበኔር ኢዮአብን “ከእያንዳንዳችን ወገን ወጣቶችን መርጠን በጦር መሣሪያ ውጊያ በመግጠም ይወዳደሩ” አለው። ኢዮአብም “መልካም ነው” ሲል መለሰ። ስለዚህም ከብንያም ወገን የኢያቡስቴ ተወካዮች የሚሆኑ ዐሥራ ሁለት ሰዎች ተመርጠው ከዳዊት ወገን ከተመረጡት ዐሥራ ሁለት ሰዎች ጋር ውጊያ ገጠሙ። እያንዳንዱ ሰው የባለጋራውን ራስ ይዞ ሰይፉን በጐኑ ሻጠበት፤ በዚህ ዐይነት ኻያ አራቱም ሰዎች በአንድነት ወድቀው ሞቱ፤ ስለዚህም በገባዖን የሚገኘው ያ ስፍራ “የሰይፍ ምድር” ተብሎ ተጠራ። በዚያም ቀን ከባድ ጦርነት ተደርጎ አበኔርና እስራኤላውያን በዳዊት ሰዎች ድል ተመቱ። ኢዮአብ፥ አቢሳ፥ ዐሣሄል ተብለው የሚጠሩት ሦስቱም የጸሩያ ልጆች እዚያ ነበሩ፤ በሩጫ እንደ በረሓ ሚዳቋ ፈጣን የነበረው አሳሔል፥ አበኔርን አባሮ ለመያዝ በቀጥታ ወደ እርሱ ሮጠ፤ አበኔርም፥ ወደ ኋላው መለስ ብሎ “ዐሣሄል፥ አንተ ነህ?” አለ። ዐሣሄልም “አዎ እኔ ነኝ” ሲል መለሰለት። አበኔርም “እኔን ማሳደድ ተው! ይልቅስ ከወታደሮቹ አንዱን በማሳደድ የያዘውን ምርኮ ውሰድ” አለው፤ ዐሣሄል ግን እርሱን ማሳደዱን ቀጠለ፤ እንደገናም አበኔር “እኔን ማሳደድህን ተው! ለምን እንድገድልህ ትገፋፋኛለህ? አንተንስ ብገድል የወንድምህን የኢዮአብን ፊት እንዴት ማየት እችላለሁ?” አለው። ዐሣሄል ግን አሁንም ማሳደዱን ሊተው አልፈቀደም፤ ስለዚህ አበኔር ጦሩን ወደ ኋላው ወርውሮ ሆዱ ላይ ሲሽጥበት ጫፉ ዘልቆ በጀርባው ወጣ፤ ዐሣሄልም መሬት ላይ ወድቆ ሞተ፤ ሬሳው በተጋደመበት ስፍራ የሚያልፍ ሰው ሁሉ በአጠገቡ ቆሞ ይመለከተው ነበር። ኢዮአብና አቢሳ ግን አበኔርን አሳደዱት፤ ፀሐይ በጠለቀች ጊዜም ከጊያሕ በስተ ምሥራቅ፥ ወደ ገባዖን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ወዳለው ወደ አማ ኮረብታ ደረሱ። የብንያም ነገድ ሰዎች እንደገና ተሰብስበው ወደ አበኔር መጡ፤ በአንድ ኮረብታም ጫፍ ላይ ለጦርነት በመዘጋጀት ተሰለፉ። አበኔርም፥ ኢዮአብን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ዘለዓለም ስንዋጋ እንኖራለንን? ፍጻሜውስ መራር መሆኑን አትገነዘብምን? ሰዎችህ እኛን ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ እንዲገቱ ትእዛዝ የማትሰጣቸው እስከ መቼ ነው?” ኢዮአብም “አንተ ይህን ቃል ባትናገር ኖሮ የእኔ ሰዎች እስከ ነገ ጠዋት ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ እንደማይገቱ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ” ሲል መለሰለት። ከዚህ በኋላ ኢዮአብ እምቢልታውን ነፋ፤ ሰዎችም ሁሉ ቆሙ፤ ከዚያ በኋላ እስራኤልን አላሳደዱም፤ ጦርነቱንም አልቀጠሉም። አበኔርና ሰዎቹ ሌሊቱን ሁሉ በመጓዝ በዓራባ ሸለቆ በኩል ሄዱ፤ ዮርዳኖስንም ተሻግረው በመጓዝ ቢትሮንን ሁሉ ዓልፈው ወደ ማኅናይም መጡ። ኢዮአብ አበኔርን ከማሳደድ በተመለሰ ጊዜ ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፤ በዚህ ጊዜ ከዳዊት ሰዎች መካከል ከዐሣሔል ሌላ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች መጒደላቸው ታወቀ። የዳዊት ሰዎች የብንያም ነገድ ከሆኑት ከአበኔር ተከታዮች ሦስት መቶ ሥልሳ ሰዎችን ገደሉ። ኢዮአብና ከእርሱ ጋር የነበሩት ተከታዮቹ የዐሣሄልን አስክሬን ወስደው በቤተልሔም በሚገኘው በቤተሰቡ መቃብር ውስጥ ቀበሩት፤ ሌሊቱንም ሁሉ ሲገሠግሡ አድረው ጎሕ ሲቀድ ኬብሮን ደረሱ።

2 ሳሙኤል 2:1-32 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከዚህ በኋላ ዳዊት፥ “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን?” ብሎ ጌታን ጠየቀ። ጌታም፥ “አዎን ውጣ” አለው። ዳዊትም፥ “ወደ የትኛዪቱ ልሂድ?” ሲል ጠየቀ። እርሱም፥ “ወደ ኬብሮን” ብሎ መለሰለት። ስለዚህ ዳዊት ወደዚያ ወጣ፤ ሁለቱ ሚስቶቹ ኢይዝራኤላዊቷ አሒኖዓምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢጌልም ከእርሱ ጋር ነበሩ። እንዲሁም ዳዊት አብረውት የነበሩትን ሰዎች ከነቤተሰቦቻቸው አመጣቸው፤ እነርሱም በኬብሮን ከተሞች ተቀመጡ። የይሁዳም ሰዎች ወደ ኬብሮን መጡ፤ በዚያም ዳዊትን ቀብተው በይሁዳ ቤት ላይ አነገሡት። ሳኦልን የቀበሩት የያቤሽ ገለዓድ ሰዎች መሆናቸውን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ፥ እርሱም ወደ ያቤሽ ገለዓድ መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ አላቸው፥ “በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ጌታችሁን ሳኦልን በመቅበር በጎነት በማሳየታችሁ ጌታ ይባርካችሁ፤ አሁንም ጌታ ጽኑ ፍቅሩንና ታማኝነቱን ይግለጥላችሁ! እናንተ ይህን ስላደረጋችሁ፥ እኔም እንደዚሁ በጎ ነገር አደርግላችኋለሁ፤ እንግዲህ ጠንክሩ፤ በርቱ ጌታችሁ ሳኦል ሞቷልና፤ የይሁዳ ቤትም እኔን ቀብተው በላያቸው አንግሠውኛል።” በዚህ ጊዜ የሳኦል ሠራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔር፥ የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደ ማሕናይም አሻገረው፤ እርሱንም በገለዓድ ላይ፥ በአሴር፥ በኢይዝራኤል፥ በኤፍሬምና በብንያም እንዲሁም በእስራኤል ሁሉ አነገሠው። የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበረ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። የይሁዳ ቤት ግን ዳዊትን ተከተለ። ዳዊት በኬብሮን ነግሶ እስራኤልን የገዛው ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ። የኔር ልጅ አበኔር፥ ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ አገልጋዮች ጋር ሆኖ ከማሕናይም ተነሥተው ወደ ገባዖን ሄዱ። እነርሱንም የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ሰዎች ወጥተው በገባዖን ኲሬ አጠገብ ተገናቿቸው፤ አንዱ ወገን በኲሬው ወዲህ ማዶ፥ ሌላው ወገን ደግሞ በኲሬው ወዲያ ማዶ ተቀመጠ። ከዚያም አበኔር፥ ኢዮአብን፥ “ጉልማሶች ይነሡና በፊታችን ትግል ይግጠሙ” አለው። ኢዮአብም፥ “ይሁን እሺ ይግጠሙ” ብሎ መለሰ። ስለዚህም ለብንያም ወገንና ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ ዐሥራ ሁለት፥ ለዳዊት ደግሞ ዐሥራ ሁለት አገልጋዮቹ ተነሥተው ተቆጠሩ። ከዚያም እያንዳንዱ ሰው የባለጋራውን ራስ ያዘ፥ ሰይፉንም በጐኑ ሻጠ፥ ተያይዘውም ወደቁ። ስለዚህም በገባዖን የሚገኘው ያ ስፍራ “የስለታም ሰይፍ ምድር” ተባለ። የዚያን ዕለት ፍልሚያ እጅግ መራር ነበር፤ በዳዊትም አገልጋዮች ፊት አበኔርና የእስራኤል ሰዎች ተሸነፉ። ሦስቱ የጽሩያ ልጆች ኢዮአብ፥ አቢሳና አሣሄል እዚያው ነበሩ። አሣሄል እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ፤ አቤኔርን ለመያዝ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሳይል ተከተለው። አበኔርም ወደ ኋላው ዘወር ብሎ በመመልከት፥ “አሣሄል! አንተ ነህ?” ሲል፥ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰለት። ከዚያም አበኔር፥ “ወደ ቀኝህ ወይም ወደ ግራህ ዘወር በልና አንዱን ጎልማሳ ይዘህ ምርኮውን ውሰድ” አለው። አሣሄል ግን እርሱን ማሳደዱን ቀጠለ። እንደገናም አበኔር፥ “እኔን ማሳደድህን ተው! እኔስ ስለምን ከመሬት ጋር ላጣብቅህ? ከዚያስ የወንድምህን የኢዮአብን ፊት እንዴት ብዬ አያለሁ?” አለው። አሣሄል ግን ማሳደዱን አልተወም፤ ስለዚህ አበኔር በጦሩ ጫፍ ሆዱን ወጋው፥ ጦሩም በጀርባው በኩል ወጣ፤ አሣሄልም እዚያው ወደቀ፤ ወድቆም በነበረበት ስፍራ ሞተ። እያንዳንዱም ሰው አሣሄል ወድቆ ወደ ሞተበት ስፍራ ሲደርስ ይቆም ነበር። ኢዮአብና አቢሳ ግን አበኔርን ተከታተሉት፤ ፀሐይ ስትጠልቅ ወደ ገባዖን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ከጊያሕ አጠገብ ወዳለው ወደ አማ ኮረብታ ደርሱ። ከዚያም የብንያም ሰዎች ተሰብስበው ከአበኔር ጀርባ በመሆን ግንባር ፈጠሩ፤ በኰረብታውም ጫፍ ላይ ተሰለፉ። አበኔር ኢዮአብን ጠርቶ፥ “ሰይፍ በውኑ እስከ ዘለዓለም ያጠፋልን? ፍጻሜውሳ መራራ እንደሆነ አታውቅምን? ሰዎችህ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ እንዲገቱ ትእዛዝ የማትሰጣቸውስ እስከ መቼ ነው?” አለው። ኢዮአብም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ባትናገር ኖሮ፥ ሰዎቹ እስኪ ነጋ ድረስ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን ባላቆሙም ነበር” ብሎ መለሰ። ስለዚህ ኢዮአብ ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ከዚያም በኋላ ሰዎቹ በሙሉ እስራኤልን ማሳደዱን ተዉ ውጊያውንም አቆሙ። አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ዓራባን አልፈው ሄዱ፤ ዮርዳኖስንም በመሻገር ቢትሮንን ሁሉ ዐልፈው ወደ ማሕናይም መጡ። ከዚያም ኢዮአብ አበኔርን ማሳደዱን ትቶ ተመለሰ፤ ሰዎቹንም ሁሉ አንድ ላይ በሰበሰባቸው ጊዜ፥ ከዳዊት ሰዎች አሣሄልን ሳይጨምር፥ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች መጉደላቸው ታወቀ። የዳዊት አገልጋዮች ግን ከአበኔር ጋር ከነበሩት ሦስት መቶ ሥልሳ ብንያማውያን ገደሉ። አሣሄልንም ከወደቀበት አንሥተው በቤተልሔም በሚገኘው በአባቱ መቃብር ቀበሩት። ከዚያም ኢዮአብና ሰዎቹ ሌሊቱን ሁሉ ሲገሠግሡ አድረው፥ ኬብሮን ንጋት ሆነ።