የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽ​ሐፈ ሳሙ​ኤል ካልእ 2:1-32

መጽ​ሐፈ ሳሙ​ኤል ካልእ 2:1-32 አማ2000

ከዚ​ያም በኋላ ዳዊት፥ “ከይ​ሁዳ ከተ​ሞች ወደ አን​ዲቱ ልው​ጣን?” ብሎ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ጠየቀ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም፥ “ውጣ” አለው። ዳዊ​ትም፥ “ወዴት ልውጣ?” አለ። እር​ሱም፥ “ወደ ኬብ​ሮን ውጣ” አለው። ዳዊ​ትም ከሁ​ለቱ ሚስ​ቶቹ ከኢ​ይ​ዝ​ራ​ኤ​ላ​ዊቱ ከአ​ኪ​ና​ሆ​ምና የቀ​ር​ሜ​ሎ​ሳ​ዊው የና​ባል ሚስት ከነ​በ​ረ​ችው ከአ​ቤ​ግያ ጋር ወደ​ዚያ ወደ ኬብ​ሮን ወጣ። ከእ​ር​ሱም ጋር የነ​በ​ሩት ሰዎች ሁሉ ከቤተ ሰባ​ቸው ጋር ወጡ፤ በኬ​ብ​ሮ​ንም ከተ​ሞች ተቀ​መጡ። የይ​ሁ​ዳም ሰዎች መጥ​ተው በይ​ሁዳ ቤት ይነ​ግሥ ዘንድ ዳዊ​ትን በዚያ ቀቡት። ሳኦ​ልን የቀ​በ​ሩት የኢ​ያ​ቢስ ገለ​ዓድ ሰዎች ናቸው ብለው ለዳ​ዊት ነገ​ሩት። ዳዊ​ትም ወደ ኢያ​ቢስ ገለ​ዓድ ገዦች መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ችን ላከ፤ ዳዊ​ትም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እና​ንተ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለቀ​ባው ለጌ​ታ​ችሁ ለሳ​ኦል ይህን ቸር​ነት አድ​ር​ጋ​ች​ኋ​ልና፥ እር​ሱ​ንና ልጁን ዮና​ታ​ን​ንም ቀብ​ራ​ች​ኋ​ቸ​ዋ​ልና በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የተ​ባ​ረ​ካ​ችሁ ሁኑ። አሁ​ንም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ምሕ​ረ​ት​ንና ጽድ​ቅን ያድ​ር​ግ​ላ​ችሁ፤ ይህ​ንም ነገር አድ​ር​ጋ​ች​ኋ​ልና እኔ ደግሞ ይህን በጎ​ነት እመ​ል​ስ​ላ​ች​ኋ​ለሁ። አሁ​ንም ጌታ​ችሁ ሳኦል ሞቶ​አ​ልና እጃ​ችሁ ትጽና፤ እና​ን​ተም በርቱ፤ የይ​ሁ​ዳም ቤት በእ​ነ​ርሱ ላይ ንጉሥ እሆን ዘንድ ቀብ​ተ​ው​ኛል።” የሳ​ኦ​ልም ጭፍራ አለቃ የኔር ልጅ አበ​ኔር የሳ​ኦ​ልን ልጅ ኢያ​ቡ​ስ​ቴን ወስዶ ከሰ​ፈር ወደ መሃ​ና​ይም አወ​ጣው፤ በገ​ለ​ዓ​ድና በታ​ሲሪ፥ በኢ​ይ​ዝ​ራ​ኤ​ልም፥ በኤ​ፍ​ሬ​ምም፥ በብ​ን​ያ​ምም፥ በእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ሁሉ ላይ አነ​ገ​ሠው። የሳ​ኦል ልጅ ኢያ​ቡ​ስ​ቴም በእ​ስ​ራ​ኤል ላይ በነ​ገሠ ጊዜ አርባ ዓመት ሆኖት ነበረ፤ ዳዊ​ትን ከተ​ከ​ተ​ሉት ከይ​ሁዳ ወገ​ኖች ብቻ በቀር ሁለት ዓመት ነገሠ። ዳዊ​ትም በይ​ሁዳ ቤት በኬ​ብ​ሮን የነ​ገ​ሠ​በት ዘመን ሰባት ዓመት ከስ​ድ​ስት ወር ነበረ። የኔር ልጅ አበ​ኔ​ርና የሳ​ኦል ልጅ የኢ​ያ​ቡ​ስቴ ብላ​ቴ​ኖች ከመ​ሃ​ና​ይም ወደ ገባ​ዖን ወጡ። የሶ​ር​ህያ ልጅ ኢዮ​አ​ብና የዳ​ዊት ብላ​ቴ​ኖች ከኬ​ብ​ሮን ወጥ​ተው በገ​ባ​ዖን ውኃ መቆ​ሚያ አጠ​ገብ ተገ​ና​ኙ​አ​ቸው፤ በው​ኃ​ውም መቆ​ሚያ በአ​ንዱ ወገን እነ​ዚህ፥ በሌ​ላ​ውም ወገን እነ​ዚያ ሆነው ተቀ​መጡ። አበ​ኔ​ርም ኢዮ​አ​ብን፥ “ጐል​ማ​ሶ​ቻ​ችን ይነሡ፤ በፊ​ታ​ች​ንም ይቈ​ራ​ቈሱ” አለው፤ ኢዮ​አ​ብም፥ “ይነሡ” አለ። ለሳ​ኦል ልጅ ለኢ​ያ​ቡ​ስቴ ከብ​ን​ያም ልጆች ዐሥራ ሁለት፥ ከዳ​ዊ​ትም ብላ​ቴ​ኖች ዐሥራ ሁለት ተቈ​ጥ​ረው ተነሡ። ሁሉም እያ​ን​ዳ​ንዱ የወ​ደ​ረ​ኛ​ውን ራስ በእጁ ያዘ፤ ሰይ​ፉ​ንም በወ​ደ​ረ​ኛው ጐን ሻጠ፤ ተያ​ይ​ዘ​ውም ወደቁ። የዚ​ያም ስፍራ ስም “በገ​ባ​ዖን የሸ​መቁ ሰዎች ድርሻ” ተብሎ ተጠራ፤ በዚ​ያም ቀን እጅግ ጽኑ ሰልፍ ሆነ፤ በዳ​ዊ​ትም ሰዎች ፊት አበ​ኔ​ርና የእ​ስ​ራ​ኤል ሰዎች ተሸ​ነፉ። በዚ​ያም ሦስቱ የሦ​ር​ህያ ልጆች ኢዮ​አ​ብና አቢሳ፥ አሣ​ሄ​ልም ነበሩ፤ የአ​ሣ​ሄ​ልም እግ​ሮቹ ፈጣ​ኖች ነበሩ፤ እንደ ዱር ሚዳ​ቋም ሯጭ ነበረ። አሣ​ሄ​ልም የአ​በ​ኔ​ርን ፍለጋ ተከ​ታ​ተለ፤ አበ​ኔ​ር​ንም ከማ​ሳ​ደድ ቀኝና ግራ አላ​ለም። አበ​ኔ​ርም ወደ ኋላው ተመ​ልሶ፥ “አንተ አሣ​ሄል ነህን?” አለው። እር​ሱም፥ “አዎ፥ እኔ ነኝ” አለው። አበ​ኔ​ርም፥ “ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ፈቀቅ በል፤ ከብ​ላ​ቴ​ኖ​ቹም አንድ ጐል​ማሳ ያዝ፤ መሣ​ሪ​ያ​ው​ንም ለራ​ስህ ውሰድ” አለው። አሣ​ሄል ግን እር​ሱን ከማ​ሳ​ደድ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ። አበ​ኔ​ርም አሣ​ሄ​ልን፥ “ከም​ድር ጋር እን​ዳ​ላ​ጣ​ብ​ቅህ እኔን ከማ​ሳ​ደድ ፈቀቅ በል፤ ወደ ወን​ድ​ምህ ወደ ኢዮ​አብ ፊቴን አቅ​ንቼ አይ ዘንድ እን​ዴት ይቻ​ለ​ኛል? እን​ደ​ዚህ አይ​ሆ​ን​ምና ወደ ወን​ድ​ምህ ወደ ኢዮ​አብ ተመ​ለስ” አለው። ነገር ግን ከእ​ርሱ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ። አበ​ኔ​ርም በጦሩ ጫፍ ወገ​ቡን ወጋው፤ ጦሩም በኋ​ላው ወጣ፤ በዚ​ያም ስፍራ ወድቆ በበ​ታቹ ሞተ። አሣ​ሄ​ልም ወድቆ በሞ​ተ​በት ስፍራ የሚ​ያ​ልፍ ሁሉ ይቆም ነበር። ኢዮ​አ​ብና አቢ​ሳም አበ​ኔ​ርን አሳ​ደዱ፤ ፀሐ​ይም ጠለ​ቀች፤ እነ​ር​ሱም በገ​ባ​ዖን ምድረ በዳ መን​ገድ በጋይ ፊት ለፊት እስ​ካ​ለው እስከ አማን ኮረ​ብታ ድረስ መጡ። በአ​በ​ኔር ኋላ የነ​በሩ የብ​ን​ያ​ምም ልጆች ተሰ​በ​ሰቡ፥ በአ​ን​ድ​ነ​ትም ሆኑ፤ በአ​ንድ ኮረ​ብ​ታም ራስ ላይ ቆሙ። አበ​ኔ​ርም ኢዮ​አ​ብን ጠርቶ እን​ዲህ አለው፥ “ሰይፍ ለድል የም​ታ​ጠፋ አይ​ደ​ለ​ምን? ፍጻ​ሜ​ዋስ መራራ እንደ ሆነ አታ​ው​ቅ​ምን? ሕዝቡ ወን​ድ​ሞ​ቻ​ቸ​ውን ከማ​ሳ​ደድ ይመ​ለሱ ዘንድ ሕዝ​ቡን የማ​ት​ና​ገር እስከ መቼ ነው?” ኢዮ​አ​ብም፥ “ሕያው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን! ባት​ና​ገር ኖሮ ሕዝቡ ሁሉ በጥ​ዋት በወ​ን​ድ​ሞ​ቻ​ቸው ላይ በወጡ ነበር” አለ። ኢዮ​አ​ብም ቀንደ መለ​ከት ነፋ፤ ሕዝ​ቡም ሁሉ ተመ​ለሰ፤ ከዚ​ያም በኋላ እስ​ራ​ኤ​ልን አላ​ሳ​ደ​ዱ​አ​ቸ​ውም፤ ደግ​መ​ውም አል​ተ​ዋ​ጉም። አበ​ኔ​ርና ሰዎ​ቹም ሌሊ​ቱን ሁሉ ወደ ምዕ​ራብ ሄዱ፤ ዮር​ዳ​ኖ​ስ​ንም ተሻ​ገሩ፤ ያን ቀጥ​ተኛ መን​ገድ ካለፉ በኋ​ላም ወደ ሰፈር መጡ። ኢዮ​አ​ብም አበ​ኔ​ርን ከማ​ሳ​ደድ ተመ​ለሰ፤ ሕዝ​ቡ​ንም ሁሉ ሰበ​ሰበ፤ የዳ​ዊ​ት​ንም ብላ​ቴ​ኖች አስ​ቈ​ጠ​ራ​ቸው፤ የሞ​ቱ​ትም ሰዎች ከአ​ሣ​ሄል ሌላ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች ናቸው። የዳ​ዊ​ትም ብላ​ቴ​ኖች ከብ​ን​ያም እና ከአ​በ​ኔር ሰዎች ሦስት መቶ ስድሳ ሰዎ​ችን ገደሉ። አሣ​ሄ​ል​ንም አን​ሥ​ተው በቤተ ልሔም በአ​ባቱ መቃ​ብር ቀበ​ሩት፤ ኢዮ​አ​ብና ከእ​ርሱ ጋር የነ​በሩ ሰዎ​ቹም ሌሊ​ቱን ሁሉ፤ ሄዱ፥ በኬ​ብ​ሮ​ንም አነጉ።