ከዚህ በኋላ ዳዊት፣ “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን?” ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን ውጣ” አለው። ዳዊትም፣ “ወደ የትኛዪቱ ልሂድ?” ሲል ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “ወደ ኬብሮን” ብሎ መለሰለት። ስለዚህ ዳዊት ከሁለቱ ሚስቶቹ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ ጋር ወደዚያ ወጣ። እንዲሁም ዳዊት አብረውት የነበሩትን ሰዎች ከነቤተ ሰቦቻቸው አመጣቸው፤ እነርሱም በኬብሮን ከተሞች ተቀመጡ። የይሁዳም ሰዎች ወደ ኬብሮን መጡ፤ በዚያም ዳዊትን ቀብተው በይሁዳ ቤት ላይ አነገሡት። ሳኦልን የቀበሩት የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች መሆናቸውን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ፣ እርሱም የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ይህን እንዲነግሩ መልእክተኞች ላከ፤ “በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ ጌታችሁን ሳኦልን በመቅበር በጎነት አሳይታችኋልና እግዚአብሔር ይባርካችሁ፤ አሁንም እግዚአብሔር ጽኑ ፍቅሩንና ታማኝነቱን ይግለጥላችሁ፤ እናንተ ይህን ስላደረጋችሁ፣ እኔም እንደዚሁ በጎ ነገር አደርግላችኋለሁ፤ እንግዲህ ጠንክሩ፤ በርቱ፤ ጌታችሁ ሳኦል ሞቷልና፤ የይሁዳ ቤትም እኔን ቀብተው በላያቸው አንግሠውኛል።” በዚህ ጊዜ የሳኦል ሰራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔር፣ የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደ መሃናይም አሻገረው፤ እርሱንም በገለዓድ፣ በአሴር፣ በኢይዝራኤል፣ በኤፍሬምና በብንያም እንዲሁም በእስራኤል ሁሉ ላይ አነገሠው። የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበረ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። የይሁዳ ቤት ግን ዳዊትን ተከተለ። ዳዊት በኬብሮን ንጉሥ ሆኖ እስራኤልን የገዛው ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ። የኔር ልጅ አበኔር፣ ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ አገልጋዮች ጋር ሆኖ ከመሃናይም ተነሥተው ወደ ገባዖን ሄዱ። እነርሱንም የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ሰዎች ወጥተው በገባዖን ኵሬ አጠገብ ተገናኟቸው፤ አንዱ ወገን በኵሬው ወዲህ ማዶ፣ ሌላው ወገን ደግሞ በኵሬው ወዲያ ማዶ ተቀመጠ። ከዚያም አበኔር፣ ኢዮአብን፣ “ከእናንተም ከእኛም ጕልማሶች ይነሡና በፊታችን በጨበጣ ውጊያ ይጋጠሙ” አለው። ኢዮአብም፣ “ይሁን እሺ ይጋጠሙ” ብሎ መለሰ። ስለዚህ ከብንያም ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ ዐሥራ ሁለት፣ ለዳዊት ደግሞ ዐሥራ ሁለት ሰዎች ተነሥተው ተቈጠሩ። ከዚያም እያንዳንዱ ሰው የባለጋራውን ራስ በመያዝ ሰይፉን በጐኑ እየሻጠበት ተያይዘው ወደቁ። ስለዚህም በገባዖን የሚገኘው ያ ቦታ “የሰይፍ ምድር” ተባለ። የዚያን ዕለቱ ጦርነት እጅግ ከባድ ነበር፤ አበኔርና የእስራኤል ሰዎች በዳዊት ሰዎች ድል ሆኑ። ሦስቱ የጽሩያ ወንዶች ልጆች ኢዮአብ፣ አቢሳና አሣሄል እዚያው ነበሩ። አሣሄል እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ፤ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሳይል አበኔርን ተከታተለው። አበኔርም ወደ ኋላው ዘወር ብሎ በመመልከት፣ “አሣሄል! አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰለት። ከዚያም አበኔር፣ “ወደ ቀኝህ ወይም ወደ ግራህ ዘወር በልና አንዱን ጕልማሳ ይዘህ መሣሪያውን ንጠቀው” አለው። አሣሄል ግን እርሱን መከታተሉን አልተወም ነበር። እንደ ገናም አበኔር፣ “እኔን መከታተል ብትተው ይሻልሃል፤ እኔስ ለምን ከመሬት ጋር ላጣብቅህ? ከዚያስ የወንድምህን የኢዮአብን ፊት ቀና ብዬ እንዴት አያለሁ?” አለው። አሣሄል ግን መከታተሉን አልተወም፤ ስለዚህ አበኔር በጦሩ ጫፍ ሆዱን ወጋው፣ ጦሩም በጀርባው ዘልቆ ወጣ፤ አሣሄልም እዚያው ወደቀ፤ ወዲያው ሞተ። እያንዳንዱም አሣሄል ወድቆ ወደ ሞተበት ስፍራ ሲደርስ ይቆም ነበር። ኢዮአብና አቢሳ ግን አበኔርን ተከታተሉት፤ እያሳደዱም ወደ ገባዖን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ከጋይ አጠገብ ወዳለው ወደ አማ ኰረብታ ሲደርሱ ፀሓይ ጠለቀች። ከዚያም የብንያም ሰዎች ወደ አበኔር ተሰብስበው ግንባር በመፍጠር በኰረብታው ጫፍ ላይ ተሰለፉ። አበኔር ኢዮአብን ጠርቶ፣ “ይህ ሰይፍ ዘላለም ማጥፋት አለበትን? ውጤቱ መራራ መሆኑን አንተስ ሳታውቀው ቀርተህ ነውን? ሰዎችህ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን እንዲያቆሙ ትእዛዝ የማትሰጣቸውስ እስከ መቼ ድረስ ነው?” አለው። ኢዮአብም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ባትናገር ኖሮ፣ ሰዎቹ እስኪነጋ ድረስ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን ባላቆሙም ነበር” ብሎ መለሰ። ስለዚህ ኢዮአብ ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ከዚያም በኋላ ሰዎቹ በሙሉ እስራኤልን ማሳደዱን ተው፤ ውጊያውም በዚሁ አበቃ። አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ዓረባን ዐልፈው ሄዱ፤ ከዚያም ዮርዳኖስን በመሻገር ቢትሮንን ሁሉ ዐልፈው ወደ መሃናይም መጡ። ከዚያም ኢዮአብ አበኔርን ማሳደዱን ትቶ ተመለሰ፤ ሰዎቹንም ሁሉ አንድ ላይ በሰበሰባቸው ጊዜ፣ ከዳዊት ሰዎች አሣሄልን ሳይጨምር፣ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች መጥፋታቸው ታወቀ። የዳዊት ሰዎች ግን ከአበኔር ጋር ከነበሩት ሦስት መቶ ስድሳ ብንያማውያን ገደሉ። አሣሄልንም ከወደቀበት አንሥተው በቤተ ልሔም በአባቱ መቃብር ቀበሩት። ከዚያም ኢዮአብና ሰዎቹ ሌሊቱን ሁሉ ሲገሠግሡ ዐድረው፣ ሲነጋ ኬብሮን ደረሱ።
2 ሳሙኤል 2 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ሳሙኤል 2
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ሳሙኤል 2:1-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos