ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2
2
ዳዊት የይሁዳ ንጉሥ መሆኑ
1ከዚህ በኋላ ዳዊት ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንድዋ ልውጣን? ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ።
እግዚአብሔርም “አዎ ውጣ” አለው።
ዳዊትም “ወደ የትኛይቱ ከተማ ልሂድ?” ሲል ጠየቀ።
እግዚአብሔርም “ወደ ኬብሮን ከተማ ሂድ” አለው።
2ስለዚህ ዳዊት ከሁለቱ ሚስቶቹ ጋር ወደ ኬብሮን ሄደ፤ እነርሱም የኢይዝራኤል ተወላጅ የሆነችው የአሒኖዓምና የቀርሜሎሳዊው የሟቹ የናባል ሚስት አቢጌል ነበሩ። #1ሳሙ. 25፥42-43። 3እንዲሁም ዳዊት ተከታዮቹን ከነቤተሰባቸው ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ በኬብሮን ዙሪያ ባሉትም ታናናሽ ከተሞች ተቀመጡ። 4ከዚህ በኋላ የይሁዳ ሰዎች ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትንም ቀብተው የይሁዳ ንጉሥ አደረጉት። #1ሳሙ. 31፥11-13።
ዳዊት ገለዓዳውያን የሆኑ የያቤሽ ሰዎች ሳኦልን እንደ ቀበሩት በሰማ ጊዜ፥ 5ዳዊት ወደ ያቤሽ ገለዓድ ሰዎች መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ አላቸው፦ “እርሱን በመቅበር ለጌታችሁ ለሳኦል ቸርነትን ስላሳያችሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ። 6ደግሞም እግዚአብሔር ቸርነቱንና ታማኝነቱን ይግለጥላችሁ፤ እናንተ ስለ ፈጸማችሁት መልካም ነገር እኔም ለእናንተ ወሮታችሁን እመልሳለሁ። 7እንግዲህ ጠንክሩ! በርቱም! ጌታችሁ ሳኦል ሞቶአል፤ የይሁዳ ሕዝብ እኔን ቀብቶ አንግሦኛል።”
ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ መንገሡ
8የሳኦል ሠራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔር ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ ጋር የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር ወደ ማሕናይም ሸሽቶ ሄደ፤ 9በዚያም አበኔር ኢያቡስቴን በገለዓድ ግዛቶች፥ በአሴር፥ በኢይዝራኤል፥ በኤፍሬምና በብንያም ይኸውም በመላው እስራኤል ላይ እንዲነግሥ አደረገ። 10እርሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበር፤ ሁለት ዓመትም ገዛ።
የይሁዳ ነገድ ግን ዳዊትን ተከተለ፤ 11ዳዊትም በኬብሮን ተቀምጦ በመላው ይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ተኩል ነገሠ።
በእስራኤልና በይሁዳ መካከል የተደረገው ጦርነት
12አበኔርና የኢያቡስቴ ባለሟሎች ከማሕናይም ተነሥተው ወደ ገባዖን ከተማ መጡ፤ 13እናቱ ጸሩያ ተብላ የምትጠራው ኢዮአብና ሌሎቹም የዳዊት ባለሥልጣኖች ወጥተው በገባዖን ኲሬ ውሃ አጠገብ ተገናኙ፤ ሁሉም በቡድን ተከፋፍለው በኲሬው ውሃ ማዶ ለማዶ ተቀምጠው ነበር። 14በዚህ ጊዜ አበኔር ኢዮአብን “ከእያንዳንዳችን ወገን ወጣቶችን መርጠን በጦር መሣሪያ ውጊያ በመግጠም ይወዳደሩ” አለው።
ኢዮአብም “መልካም ነው” ሲል መለሰ።
15ስለዚህም ከብንያም ወገን የኢያቡስቴ ተወካዮች የሚሆኑ ዐሥራ ሁለት ሰዎች ተመርጠው ከዳዊት ወገን ከተመረጡት ዐሥራ ሁለት ሰዎች ጋር ውጊያ ገጠሙ። 16እያንዳንዱ ሰው የባለጋራውን ራስ ይዞ ሰይፉን በጐኑ ሻጠበት፤ በዚህ ዐይነት ኻያ አራቱም ሰዎች በአንድነት ወድቀው ሞቱ፤ ስለዚህም በገባዖን የሚገኘው ያ ስፍራ “የሰይፍ ምድር” ተብሎ ተጠራ።
17በዚያም ቀን ከባድ ጦርነት ተደርጎ አበኔርና እስራኤላውያን በዳዊት ሰዎች ድል ተመቱ። 18ኢዮአብ፥ አቢሳ፥ ዐሣሄል ተብለው የሚጠሩት ሦስቱም የጸሩያ ልጆች እዚያ ነበሩ፤ በሩጫ እንደ በረሓ ሚዳቋ ፈጣን የነበረው አሳሔል፥ 19አበኔርን አባሮ ለመያዝ በቀጥታ ወደ እርሱ ሮጠ፤ 20አበኔርም፥ ወደ ኋላው መለስ ብሎ “ዐሣሄል፥ አንተ ነህ?” አለ።
ዐሣሄልም “አዎ እኔ ነኝ” ሲል መለሰለት።
21አበኔርም “እኔን ማሳደድ ተው! ይልቅስ ከወታደሮቹ አንዱን በማሳደድ የያዘውን ምርኮ ውሰድ” አለው፤ ዐሣሄል ግን እርሱን ማሳደዱን ቀጠለ፤ 22እንደገናም አበኔር “እኔን ማሳደድህን ተው! ለምን እንድገድልህ ትገፋፋኛለህ? አንተንስ ብገድል የወንድምህን የኢዮአብን ፊት እንዴት ማየት እችላለሁ?” አለው። 23ዐሣሄል ግን አሁንም ማሳደዱን ሊተው አልፈቀደም፤ ስለዚህ አበኔር ጦሩን ወደ ኋላው ወርውሮ ሆዱ ላይ ሲሽጥበት ጫፉ ዘልቆ በጀርባው ወጣ፤ ዐሣሄልም መሬት ላይ ወድቆ ሞተ፤ ሬሳው በተጋደመበት ስፍራ የሚያልፍ ሰው ሁሉ በአጠገቡ ቆሞ ይመለከተው ነበር።
24ኢዮአብና አቢሳ ግን አበኔርን አሳደዱት፤ ፀሐይ በጠለቀች ጊዜም ከጊያሕ በስተ ምሥራቅ፥ ወደ ገባዖን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ወዳለው ወደ አማ ኮረብታ ደረሱ። 25የብንያም ነገድ ሰዎች እንደገና ተሰብስበው ወደ አበኔር መጡ፤ በአንድ ኮረብታም ጫፍ ላይ ለጦርነት በመዘጋጀት ተሰለፉ። 26አበኔርም፥ ኢዮአብን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ዘለዓለም ስንዋጋ እንኖራለንን? ፍጻሜውስ መራር መሆኑን አትገነዘብምን? ሰዎችህ እኛን ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ እንዲገቱ ትእዛዝ የማትሰጣቸው እስከ መቼ ነው?”
27ኢዮአብም “አንተ ይህን ቃል ባትናገር ኖሮ የእኔ ሰዎች እስከ ነገ ጠዋት ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ እንደማይገቱ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ” ሲል መለሰለት። 28ከዚህ በኋላ ኢዮአብ እምቢልታውን ነፋ፤ ሰዎችም ሁሉ ቆሙ፤ ከዚያ በኋላ እስራኤልን አላሳደዱም፤ ጦርነቱንም አልቀጠሉም።
29አበኔርና ሰዎቹ ሌሊቱን ሁሉ በመጓዝ በዓራባ ሸለቆ በኩል ሄዱ፤ ዮርዳኖስንም ተሻግረው በመጓዝ ቢትሮንን ሁሉ ዓልፈው ወደ ማኅናይም መጡ።
30ኢዮአብ አበኔርን ከማሳደድ በተመለሰ ጊዜ ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፤ በዚህ ጊዜ ከዳዊት ሰዎች መካከል ከዐሣሔል ሌላ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች መጒደላቸው ታወቀ። 31የዳዊት ሰዎች የብንያም ነገድ ከሆኑት ከአበኔር ተከታዮች ሦስት መቶ ሥልሳ ሰዎችን ገደሉ። 32ኢዮአብና ከእርሱ ጋር የነበሩት ተከታዮቹ የዐሣሄልን አስክሬን ወስደው በቤተልሔም በሚገኘው በቤተሰቡ መቃብር ውስጥ ቀበሩት፤ ሌሊቱንም ሁሉ ሲገሠግሡ አድረው ጎሕ ሲቀድ ኬብሮን ደረሱ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997