ከዚህ በኋላ ዳዊት፥ “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን?” ብሎ ጌታን ጠየቀ። ጌታም፥ “አዎን ውጣ” አለው። ዳዊትም፥ “ወደ የትኛዪቱ ልሂድ?” ሲል ጠየቀ። እርሱም፥ “ወደ ኬብሮን” ብሎ መለሰለት። ስለዚህ ዳዊት ወደዚያ ወጣ፤ ሁለቱ ሚስቶቹ ኢይዝራኤላዊቷ አሒኖዓምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢጌልም ከእርሱ ጋር ነበሩ። እንዲሁም ዳዊት አብረውት የነበሩትን ሰዎች ከነቤተሰቦቻቸው አመጣቸው፤ እነርሱም በኬብሮን ከተሞች ተቀመጡ። የይሁዳም ሰዎች ወደ ኬብሮን መጡ፤ በዚያም ዳዊትን ቀብተው በይሁዳ ቤት ላይ አነገሡት። ሳኦልን የቀበሩት የያቤሽ ገለዓድ ሰዎች መሆናቸውን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ፥ እርሱም ወደ ያቤሽ ገለዓድ መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ አላቸው፥ “በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ጌታችሁን ሳኦልን በመቅበር በጎነት በማሳየታችሁ ጌታ ይባርካችሁ፤ አሁንም ጌታ ጽኑ ፍቅሩንና ታማኝነቱን ይግለጥላችሁ! እናንተ ይህን ስላደረጋችሁ፥ እኔም እንደዚሁ በጎ ነገር አደርግላችኋለሁ፤ እንግዲህ ጠንክሩ፤ በርቱ ጌታችሁ ሳኦል ሞቷልና፤ የይሁዳ ቤትም እኔን ቀብተው በላያቸው አንግሠውኛል።” በዚህ ጊዜ የሳኦል ሠራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔር፥ የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደ ማሕናይም አሻገረው፤ እርሱንም በገለዓድ ላይ፥ በአሴር፥ በኢይዝራኤል፥ በኤፍሬምና በብንያም እንዲሁም በእስራኤል ሁሉ አነገሠው። የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበረ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። የይሁዳ ቤት ግን ዳዊትን ተከተለ። ዳዊት በኬብሮን ነግሶ እስራኤልን የገዛው ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ። የኔር ልጅ አበኔር፥ ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ አገልጋዮች ጋር ሆኖ ከማሕናይም ተነሥተው ወደ ገባዖን ሄዱ። እነርሱንም የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ሰዎች ወጥተው በገባዖን ኲሬ አጠገብ ተገናቿቸው፤ አንዱ ወገን በኲሬው ወዲህ ማዶ፥ ሌላው ወገን ደግሞ በኲሬው ወዲያ ማዶ ተቀመጠ። ከዚያም አበኔር፥ ኢዮአብን፥ “ጉልማሶች ይነሡና በፊታችን ትግል ይግጠሙ” አለው። ኢዮአብም፥ “ይሁን እሺ ይግጠሙ” ብሎ መለሰ። ስለዚህም ለብንያም ወገንና ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ ዐሥራ ሁለት፥ ለዳዊት ደግሞ ዐሥራ ሁለት አገልጋዮቹ ተነሥተው ተቆጠሩ። ከዚያም እያንዳንዱ ሰው የባለጋራውን ራስ ያዘ፥ ሰይፉንም በጐኑ ሻጠ፥ ተያይዘውም ወደቁ። ስለዚህም በገባዖን የሚገኘው ያ ስፍራ “የስለታም ሰይፍ ምድር” ተባለ። የዚያን ዕለት ፍልሚያ እጅግ መራር ነበር፤ በዳዊትም አገልጋዮች ፊት አበኔርና የእስራኤል ሰዎች ተሸነፉ። ሦስቱ የጽሩያ ልጆች ኢዮአብ፥ አቢሳና አሣሄል እዚያው ነበሩ። አሣሄል እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ፤ አቤኔርን ለመያዝ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሳይል ተከተለው። አበኔርም ወደ ኋላው ዘወር ብሎ በመመልከት፥ “አሣሄል! አንተ ነህ?” ሲል፥ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰለት። ከዚያም አበኔር፥ “ወደ ቀኝህ ወይም ወደ ግራህ ዘወር በልና አንዱን ጎልማሳ ይዘህ ምርኮውን ውሰድ” አለው። አሣሄል ግን እርሱን ማሳደዱን ቀጠለ። እንደገናም አበኔር፥ “እኔን ማሳደድህን ተው! እኔስ ስለምን ከመሬት ጋር ላጣብቅህ? ከዚያስ የወንድምህን የኢዮአብን ፊት እንዴት ብዬ አያለሁ?” አለው። አሣሄል ግን ማሳደዱን አልተወም፤ ስለዚህ አበኔር በጦሩ ጫፍ ሆዱን ወጋው፥ ጦሩም በጀርባው በኩል ወጣ፤ አሣሄልም እዚያው ወደቀ፤ ወድቆም በነበረበት ስፍራ ሞተ። እያንዳንዱም ሰው አሣሄል ወድቆ ወደ ሞተበት ስፍራ ሲደርስ ይቆም ነበር። ኢዮአብና አቢሳ ግን አበኔርን ተከታተሉት፤ ፀሐይ ስትጠልቅ ወደ ገባዖን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ከጊያሕ አጠገብ ወዳለው ወደ አማ ኮረብታ ደርሱ። ከዚያም የብንያም ሰዎች ተሰብስበው ከአበኔር ጀርባ በመሆን ግንባር ፈጠሩ፤ በኰረብታውም ጫፍ ላይ ተሰለፉ። አበኔር ኢዮአብን ጠርቶ፥ “ሰይፍ በውኑ እስከ ዘለዓለም ያጠፋልን? ፍጻሜውሳ መራራ እንደሆነ አታውቅምን? ሰዎችህ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ እንዲገቱ ትእዛዝ የማትሰጣቸውስ እስከ መቼ ነው?” አለው። ኢዮአብም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ባትናገር ኖሮ፥ ሰዎቹ እስኪ ነጋ ድረስ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን ባላቆሙም ነበር” ብሎ መለሰ። ስለዚህ ኢዮአብ ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ከዚያም በኋላ ሰዎቹ በሙሉ እስራኤልን ማሳደዱን ተዉ ውጊያውንም አቆሙ። አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ዓራባን አልፈው ሄዱ፤ ዮርዳኖስንም በመሻገር ቢትሮንን ሁሉ ዐልፈው ወደ ማሕናይም መጡ። ከዚያም ኢዮአብ አበኔርን ማሳደዱን ትቶ ተመለሰ፤ ሰዎቹንም ሁሉ አንድ ላይ በሰበሰባቸው ጊዜ፥ ከዳዊት ሰዎች አሣሄልን ሳይጨምር፥ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች መጉደላቸው ታወቀ። የዳዊት አገልጋዮች ግን ከአበኔር ጋር ከነበሩት ሦስት መቶ ሥልሳ ብንያማውያን ገደሉ። አሣሄልንም ከወደቀበት አንሥተው በቤተልሔም በሚገኘው በአባቱ መቃብር ቀበሩት። ከዚያም ኢዮአብና ሰዎቹ ሌሊቱን ሁሉ ሲገሠግሡ አድረው፥ ኬብሮን ንጋት ሆነ።
2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2:1-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos