2 ሳሙኤል 15:1-37
2 ሳሙኤል 15:1-37 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ አቤሴሎም ሰረገላና ፈረሶች፥ በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ። አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ በበሩ ጎዳና ይቆም ነበር፤ አቤሴሎምም ከንጉሥ ለማስፈረድ ጉዳይ የነበረውን ሁሉ ወደ እርሱ እየጠራ፥ “አንተ ከወዴት ከተማ ነህ?” ብሎ ይጠይቅ ነበር። እርሱም፥ “እኔ አገልጋይህ ከእስራኤል ወገን ከአንዲቱ ነኝ” ይለው ነበር። አቤሴሎምም፥ “ነገርህ መልካም ነው፤ ቀላልም ነው፤ ነገር ግን ከንጉሥ ዘንድ የሚሰማህ የለም” ይለው ነበር። አቤሴሎምም፥ “ነገርና ክርክር ያለው ሁሉ ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ፥ ቅንም ፍርድ እፈርድለት ዘንድ በሀገር ላይ ፈራጅ አድርጎ ማን በሾመኝ?” ይል ነበር። ሰውም እጅ ለመንሣት ወደ እርሱ በቀረበ ጊዜ እጁን ዘርግቶ አቅፎ ይስመው ነበር። በንጉሡ ዘንድ ሊፋረዱ ለሚመጡ ለእስራኤል ሁሉ አቤሴሎም እንዲህ ያደርግ ነበር፤ አቤሴሎምም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ማረከ። እንዲህም ሆነ፤ ከአራት ዓመት በኋላ አቤሴሎም አባቱን፥ “ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት በኬብሮን አደርግ ዘንድ ልሂድ። እኔ አገልጋይህ በሶርያ ጌድሶር ሳለሁ፦ እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም ቢመልሰኝ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀርባለሁ ብዬ ስእለት ተስዬ ነበርና” አለው። ንጉሡም፥ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ተነሥቶም ወደ ኬብሮን ሄደ። አቤሴሎምም፥ “የመለከት ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፥ አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ” በሉ የሚሉ ጕበኞችን ወደ እስራኤል ነገድ ሁሉ ላከ። የተጠሩትም ሁለት መቶ ሰዎች ከአቤሴሎም ጋር ከኢየሩሳሌም ሄዱ፤ እነርሱም በየዋህነት ሄዱ፤ ነገሩንም ሁሉ ከቶ አያውቁም ነበር። አቤሴሎምም መሥዋዕት በሚሠዋበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ ወደ ነበረው ጌሎናዊው አኪጦፌል ወደ ከተማው ጊሎ ላከ። ሴራውም ጽኑ ሆነ፤ ከአቤሴሎምም ጋር ያለው ሕዝብ እጅግ በዛ። የእስራኤልም ሰዎች ልብ ወደ አቤሴሎም ተመልሶአል የሚል መልእክተኛ ወደ ዳዊት ሄደ። ዳዊትም ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ያሉትን አገልጋዮቹን ሁሉ፥ “ተነሡ እንሽሽ፤ ከአቤሴሎም እጅ የምንድንበት የለንምና፤ ፈጥኖ እንዳይዘን፥ ክፉም እንዳያመጣብን፤ ከተማዪቱንም በሰልፍ ስለት እንዳይመታ ፈጥናችሁ እንሂድ” አላቸው። የንጉሡም ብላቴኖች ንጉሡን፥ “እነሆ፥ ጌታችን ንጉሥ የመረጠውን ሁሉ እኛ አገልጋዮችህ እናደርጋለን” አሉት። ንጉሡና ከእርሱም በኋላ ቤተ ሰቡ ሁሉ በእግራቸው ወጡ፤ ንጉሡም ቁባቶቹ የነበሩ ዐሥሩን ሴቶች ቤቱን ይጠብቁ ዘንድ ተወ። ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ በእግር ወጡ፤ በሩቅም ቦታ ቆሙ። ብላቴኖቹም ሁሉ ተከተሉት፤ ኬልቲያውያንና ፌልታውያንም ሁሉ በምድረ በዳ በወይራ ሥር ቆሙ። ሕዝቡም ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሄዱ ነበር። ከእርሱ ጋር ያሉ ሰዎችም ሁሉ ስድስት መቶ ነበሩ። ከእርሱ ጋር ፌልታውያንና ኬልቲያውያን፥ በእግራቸው ከጌት የመጡ ስድስት መቶ ጌታውያንም ነበሩ። በንጉሡም ፊት ይሄዱ ነበር። ንጉሡም ጌታዊውን ኤቲን፥ “ከእኛ ጋር ለምን መጣህ? አንተ ከስፍራህ የመጣህ ስደተኛና እንግዳ ነህና ተመለስ፤ ከንጉሡም ጋር ተቀመጥ፤ የመጣኸው ትናንት ነው፤ ዛሬ ከእኛ ጋር ላዙርህን? እኔ ወደምሄድበት እሄዳለሁ፤ አንተ ግን ተመለስ፤ ወንድሞችህንም ከአንተ ጋር መልሳቸው፤ እግዚአብሔርም ምሕረቱንና እውነቱን ያድርግልህ” አለው። ኤቲም ለንጉሡ መልሶ፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! በጌታዬም በንጉሡ ሕይወት እምላለሁ! ጌታዬ ባለበት ስፍራ ሁሉ፥ በሞትም ቢሆን በሕይወትም፥ በዚያ ደግሞ እኔ አገልጋይህ እሆናለሁ” አለው። ንጉሡም ኤቲን፥ “ና ከእኔ ጋር ተሻገር” አለው፤ ጌታዊው ኤቲና ንጉሡም፥ አገልጋዮቹም፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝቡ ሁሉ ተሻገሩ። ሀገሪቱም ሁላ በታላቅ ድምፅ አለቀሰች። ሕዝቡም ሁሉ በቄድሮን ወንዝ ተሻገሩ፤ ንጉሡም ደግሞ የቄድሮንን ወንዝ ተሻገረ፤ ንጉሡና ሕዝቡም ሁሉ ወደ ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ተሻገሩ። እነሆም፥ ደግሞ፥ ሳዶቅና ከእርሱም ጋር ሌዋውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት አመጡ፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት አስቀመጡ፤ ሕዝቡም ሁሉ ከከተማዪቱ ፈጽሞ እስኪያልፉ ድረስ አብያታር ወጣ። ንጉሡም ሳዶቅን፥ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማ መልስ፤ በእግዚአብሔር ዐይን ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆንሁ፥ መልሶ እርሷንና ክብሯን ያሳየኛል፤ ነገር ግን አልወድድህም ቢለኝ፥ እነሆኝ በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን ያድርግብኝ” አለው። ንጉሡም ደግሞ ካህኑን ሳዶቅን፥ “እነሆ፥ አንተና ልጅህ አኪማኦስ፥ የአብያታርም ልጅ ዮናታን፥ ሁለቱ ልጆቻችሁ ከእናንተ ጋር በሰላም ወደ ከተማ ተመለሱ። እዩ፤ እኔም እነሆ፥ ከእናንተ ዘንድ ወሬ እስኪመጣልኝ ድረስ በምድረ በዳው ውስጥ በሜዳው እቈያለሁ” አለው። ሳዶቅና አብያታርም የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም መለሷት፤ በዚያም ተቀመጡ። ዳዊትም ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ወጣ፤ ሲወጣም ያለቅስ ነበር፤ ራሱንም ተከናንቦ ነበር፤ ያለጫማም ይሄድ ነበር፤ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተከናንበው ነበር፤ እያለቀሱም ይወጡ ነበር። አኪጦፌል ከአቤሴሎም ጋር በሴራ አንድ ነው ብለው ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም፥ “አቤቱ የአኪጦፌልን ምክር ለውጥ” አለ። ዳዊትም ለእግዚአብሔር ወደ ሰገደበት ወደ ተራራው ራስ መጣ፤ ወዳጁ ኵሲም ልብሱን ቀደደ፤ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ። ዳዊትም አለው፥ “ከእኔ ጋር ብትሻገር ሸክም ትሆንብኛለህ፤ ወደ ከተማ ግን ተመልሰህ ለአቤሴሎም፦ ወንድሞችህ፥ ንጉሡም መጡ። እነሆ፥ በኋላዬ ናቸው። ንጉሥ ሆይ፥ አገልጋይህ ነኝ፤ አስቀድሞ ለአባትህ አገልጋይ ነበርሁ፥ እንዲሁ አሁንም ለአንተ አገልጋይ ነኝ፥ ተወኝ ልኑር ብትለው የአኪጦፌልን ምክር ትለውጥልኛለህ። እነሆ፥ ካህናቱ ሳዶቅና አብያታርም በዚያ ከአንተ ጋር ናቸው። ከንጉሡ ቤትም የምትሰማውን ነገር ሁሉ ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ንገራቸው። እነሆ፥ የሳዶቅ ልጅ አኪማኦስና የአብያታር ልጅ ዮናታን፥ ልጆቻቸው በዚያ ከእነርሱ ጋር አሉ፤ የምትሰሙትን ሁሉ በእነርሱ እጅ ላኩልኝ።” የዳዊትም ወዳጅ ኩሲ ወደ ከተማ መጣ፤ አቤሴሎምም ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ።
2 ሳሙኤል 15:1-37 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ አቤሴሎም ሠረገላና ፈረሶች እንዲሁም ፊት ፊቱ የሚሮጡ ዐምሳ ሰዎች ለራሱ አዘጋጀ። አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ሆነ ብሎ ይቆም ነበር። ማንኛውም ባለጕዳይ አቤቱታውን ለንጉሡ አቅርቦ ለማስወሰን በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ፣ አቤሴሎም ወደ እርሱ እየጠራ፣ “አንተ ከየትኛው ከተማ ነው የመጣኸው?” በማለት ይጠይቀዋል፤ ያም ሰው፣ “አገልጋይህ ከአንዱ የእስራኤል ነገዶች ነው” ብሎ ይመልስለታል። ከዚያም አቤሴሎም፣ “ተመልከት! ጕዳይህማ ትክክልና ተገቢም ነው፤ የትኛው የንጉሥ እንደራሴ ነው ታዲያ የሚያይልህ?” ይለዋል። ቀጠል አድርጎም፣ “ምነው ዳኛ ሆኜ በምድሪቱ ላይ በተሾምሁ አቤቱታ ወይም ክስ ያለበት ሁሉ ወደ እኔ እየመጣ ፍትሕ እንዲያገኝ አደርገው ነበር” ይል ነበር። እንዲሁም ማንኛውም ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ እጅ በሚነሣው ጊዜ፣ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር። አቤሴሎም ፍትሕ ለማግኘት ወደ ንጉሡ የሚመጣውን እስራኤላዊ ሁሉ የሚቀርበው በዚህ መንገድ ስለ ነበር፣ የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ። ከአራት ዓመት በኋላም አቤሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት ለማድረስ ወደ ኬብሮን እንድሄድ ፍቀድልኝ፤ እኔ አገልጋይህ በሶርያ ምድር በጌሹር ሳለሁ ‘እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም የመለሰኝ እንደ ሆነ፣ በኬብሮን ለእግዚአብሔር እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስያለሁ።” ንጉሡም፣ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ስለዚህ አቤሴሎም ወደ ኬብሮን ሄደ። ከዚያም አቤሴሎም፣ “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ፣ ‘አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ’ ” የሚሉ የምስጢር ሠራተኞችን በመላው የእስራኤል ነገዶች አሰማራ። ከኢየሩሳሌምም ሁለት መቶ ሰዎች አቤሴሎም ሄዱ፤ በእንግድነት ተጋብዘው በየዋህነት ከመሄዳቸው በቀር፣ ስለ ጕዳዩ የሚያውቁት አንዳችም ነገር አልነበረም። አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ የሆነው የጊሎን ሰው አኪጦፌል ከአገሩ ከጊሎ ወደ እርሱ እንዲመጣ ላከበት፤ ስለዚህ ሤራው ጥንካሬ አገኘ፤ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቍጥር እየጨመረ መጣ። መልእክተኛም መጥቶ፣ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋራ ሆኗል” ብሎ ለዳዊት ነገረው። ከዚያም ዳዊት በኢየሩሳሌም ላሉት ሹማምቱ ሁሉ፣ “ተነሡ እንሽሽ፤ አለዚያ አንዳችንም ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ አንችልም፤ አሁኑኑ ከዚህ መውጣት አለብን፤ ካልሆነ ገሥግሦ መጥቶ ከያዘን እኛን ያጠፋናል፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ይመታታል” አላቸው። የንጉሡ ሹማምትም፣ “ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ ለማድረግ እኛ አገልጋዮችህ ዝግጁ ነን” ብለው መለሱለት። ንጉሡ ከመላው ቤተ ሰቡ ጋራ ወጣ፤ ቤተ መንግሥቱንም እንዲጠብቁ ዐሥር ቁባቶች አስቀረ። ስለዚህ ንጉሡ መላውን ሕዝብ አስከትሎ ወጣ፤ ጥቂት ርቀው ከሄዱ በኋላም በአንዲት ቦታ ቆሙ። ሰዎቹ ሁሉ፣ ከሊታውያን፣ ፈሊታውያን እንዲሁም ከጋት ዐብረውት የመጡትን ስድስት መቶ ጋታውያንን ሁሉ ጨምሮ ተሰልፈው በንጉሡ ፊት ዐለፉ። ንጉሡም ጋታዊውን ኢታይን እንዲህ አለው፤ “ከእኛ ጋራ የመጣኸው ለምንድን ነው? ተመለስና ከንጉሡ ከአቤሴሎም ጋራ ተቀመጥ፤ አንተ ለራስህ ከአገርህ ተወስደህ የመጣህ እንግዳ ነህ፤ የመጣኸውም ገና ትናንት ነው፤ ታዲያ የት እንደምሄድ የማላውቅ ሰው እንዴት ዛሬ ከእኛ ጋራ እንድትንከራተት ላድርግ? በል አሁንም ሰዎችህን ይዘህ ተመለስ፤ በጎነትና ታማኝነትም ከአንተ ጋራ ይሁን” አለው። ኢታይ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ እምላለሁ፤ ሕይወትም ይሁን ሞት በየትም ቦታ ንጉሥ ጌታዬ የሚሆነውን ሁሉ አገልጋይህም እንደዚያው ይሆናል” ብሎ መለሰለት። ዳዊትም ኢታይን፣ “በል እንግዲያው ቅደምና ሂድ” አለው። ስለዚህ ጋታዊው ኢታይን ሰዎቹን ሁሉና ዐብረውት የነበሩትን ቤተ ሰቦቹን ይዞ ሄደ። ሕዝቡ ሁሉ በሚያልፍበትም ጊዜ ባላገሩ በሙሉ እየጮኸ አለቀሰ፤ ንጉሡም የቄድሮንን ሸለቆ ተሻገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሻግሮ ወደ ምድረ በዳው ተጓዘ። ሳዶቅም በዚያ ነበር፤ ዐብረውት የነበሩትም ሌዋውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ነበር። እነርሱም የእግዚአብሔርን ታቦት ዐሳረፉ፤ አብያታርም ሕዝቡ በሙሉ ከከተማዪቱ ለቅቆ እስኪወጣ ድረስ መሥዋዕት አቀረበ። ከዚያም ንጉሡ ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማዪቱ ይዘህ ተመለስ፤ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፣ እርሱ እኔንም መልሶ ታቦቱንና ማደሪያውን እንደ ገና ለማየት ያበቃኛል፤ ነገር ግን እርሱ፣ ‘ባንተ አልተደሰትሁም’ የሚል ከሆነ፣ መልካም መስሎ የታየውን ነገር ያድርግብኝ፤ እኔም ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።” እንዲሁም ንጉሡ ካህኑን ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ ነቢይ አይደለህምን? እንግዲህ አንተም ልጅህን አኪማአስን፣ የአብያታርን ልጅ ዮናታንን ይዘህ በሰላም ወደ ከተማዪቱ ተመለስ። አንተና አብያታር ሁለቱን ልጆቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ። እኔም ከአንተ ዘንድ ወሬ እስካገኝ ድረስ በምድረ በዳው በሚገኘው በወንዙ መሻገሪያ እቈያለሁ” ስለዚህ ሳዶቅና አብያታር የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም በመመለስ እዚያው ቈዩ። ዳዊት ግን እያለቀሰ የደብረ ዘይትን ተራራ ሽቅብ ወጣ፤ ራሱን ተከናንቦ፣ ባዶ እግሩን ነበር፤ ዐብሮት ያለውም ሕዝብ ሁሉ እንደዚሁ ራሱን ተከናንቦ እያለቀሰ ሽቅብ ይወጣ ነበር። በዚህ ጊዜ፣ “ከአቤሴሎም ጋራ ካሤሩት መካከል አንዱ አኪጦፌል ነው” ብለው ለዳዊት ነገሩት። ስለዚህ ዳዊት፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህን የአኪጦፌልን ምክር ወደ ከንቱነት ለውጠው” ብሎ ጸለየ። ዳዊትም ሕዝቡ እግዚአብሔርን ወደሚያመልክበት ወደ ተራራው ጫፍ ሲደርስ፣ አርካዊው ኩሲ ልብሱን ቀድዶ ትቢያ በራሱ ላይ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ። ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለው፤ “ዐብረኸኝ ብትሄድ ሸክም ትሆንብኛለህ፤ ነገር ግን ወደ ከተማዪቱ ተመልሰህ አቤሴሎምን፣ ‘ንጉሥ ሆይ፤ አገልጋይህ እሆናለሁ፤ ቀድሞ የአባትህ አገልጋይ እንደ ነበርሁ ሁሉ፣ ዛሬም አንተን አገለግልሃለሁ’ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር በማፍረስ ትረዳኛለህ። ካህናቱ ሳዶቅና አብያታር እዚያው ከአንተው ጋራ ይሆኑ የለምን? ከንጉሡ ቤትም የምትሰማትን ሁሉ ንገራቸው። የሳዶቅ ልጅ አኪማአስና የአብያታር ልጅ ዮናታን፣ ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው እዚያው ዐብረዋቸው ይገኛሉ። የምትሰማትን ሁሉ በእነርሱ ላክልኝ።” ስለዚህ የዳዊት ወዳጅ ኩሲ ልክ አቤሴሎም ኢየሩሳሌም በገባበት ሰዓት እዚያው ከተማ ደረሰ።
2 ሳሙኤል 15:1-37 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዚህም በኋላ አቤሴሎም ሰረገላና ፈረሶች፥ በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ። አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ በበሩ አደበባይ ይቆም ነበር፥ አቤሴሎምም ከንጉሥ ለማስፈረድ ጉዳይ የነበረውን ሁሉ ወደ እርሱ እየጠራ፦ አንተ ከወዴት ከተማ ነህ? ብሎ ይጠይቅ ነበር። እርሱም፦ እኔ ባሪያህ ከእስራኤል ነገድ ከአንዲቱ ነኝ ብሎ ይመልስ ነበር። አቤሴሎምም፦ ነገርህ እውነትና ቅን ነው፥ ነገር ግን ከንጉሥ ታዝዞ የሚሰማህ የለም ይለው ነበር። አቤሴሎምም፦ ነገርና ክርክር ያለው ሁሉ ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ ቅንም ፍርድ እፈርድለት ዘንድ በአገር ላይ ፈራጅ አድርጎ ማን በሾመኝ? ይል ነበር። ሰውም እጅ ሊነሣው ወደ እርሱ በቀረበ ጊዜ እጁን ዘርግቶ ይይዝና ይስመው ነበር። እንዲሁም አቤሴሎም ከንጉሥ ፍርድ ሊሰማ ከእስራኤል ዘንድ በሚመጣ ሁሉ ያደርግ ነበር፥ አቤሴሎምም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ። እንዲህም ሆነ፥ ከአራት ዓመት በኋላ አቤሴሎም ንጉሡን፦ ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት ለመስጠት ወደ ኬብሮን፥ እባክህ፥ ልሂድ። እኔ ባሪያህ በሶርያ ጌሹር ሳለሁ፦ እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም ቢመልሰኝ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀርባለሁ ብዬ ስእለት ተስዬ ነበር አለው። ንጉሡም፦ በደኅና ሂድ አለው፥ ተነሥቶም ወደ ኬብሮን ሄደ። አቤሴሎምም በእስራኤል ነገድ ሁሉ፦ የቀንደ መለከት ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፦ አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ የሚሉ ጉበኞች ላከ። የተጠሩትም ሁለት መቶ ሰዎች ከአቤሴሎም ጋር በየዋህነት ከኢየሩሳሌም ሄዱ፥ የሚሆነውንም ነገር ከቶ አያውቁም ነበር። አቤሴሎምም የዳዊት መካር የነበረውን የጊሎ ሰው አኪጦፌልን ከከተማው ከጊሎ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ አስጠራው። ሴራውም ጽኑ ሆነ፥ ከአቤሴሎምም ጋር ያለውች ሕዝብ እየበዛ ሄደ። ለዳዊትም፦ የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኖአል የሚል ወሬኛ መጣለት። ዳዊትም ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ያሉትን ባሪያዎቹን ሁሉ፦ ተነሡ፥ እንሽሽ፥ ያለዚያ ከአቤሴሎም እጅ የሚድን ከእኛ የለምና፥ መጥቶም እንዳይዘን፥ ክፉም እንዳያመጣብን ከተማይቱንም በሰይፍ ስለት እንዳይመታ ፈጥናችሁ እንሂድ አላቸው። የንጉሡም ባሪያዎች ንጉሡን፦ እነሆ፥ ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ እኛ ባሪያዎችህ እሺ ብለን እናደርጋለን አሉት። ንጉሡም ከእርሱም በኋላ ቤተ ሰቡ ሁሉ ወጡ፥ ንጉሡም አሥሩን ሴቶች ቁባቶቹን ቤቱን ይጠብቁ ዘንድ ተወ። ንጉሡም ከእርሱም በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ወጡ፥ በቤትሜርሐቅም ቆሙ። ባሪያዎቹም ሁሉ በፊቱ አለፉ፥ ከሊታውያንና ፈሊታውያንም ሁሉ፥ ከእርሱም በኋላ ከጌት የመጡት ስድስት መቶው ጌታውያን ሁሉ በንጉሡ ፊት አለፉ። ንጉሡም የጌት ሰው ኢታይን፦ ከእኛ ጋር ለምን መጣህ? አንተ ከስፍራህ የመጣህ እንግዳና ስደተኛ ነህና ተመለስ፥ ከንጉሡም ጋር ተቀመጥ። የመጣኸው ትናንት ነው፥ ዛሬ ከእኛ ጋር ላዙርህን? እኔ ወደምሄድበት እሄዳለሁ፥ አንተ ግን ተመለስ፥ ወንድሞችህንም ከአንተ ጋር ውሰድ፥ እግዚአብሔርም ምሕረቱንና እውነቱን ያድርግልህ አለው። ኢታይም ለንጉሡ መልሶ፦ ሕያው እግዚአብሔርን! በጌታዬም በንጉሡ ሕይወት እምላለሁ! በእውነት ጌታዬ ባለበት ስፍራ ሁሉ፥ በሞትም ቢሆን በሕይወትም፥ በዚያ ደግሞ እኔ ባሪያህ እሆናለሁ አለው። ዳዊትም ኢታይን፦ ሂድ ተሻገር አለው፥ የጌት ሰው ኢታይና ሰዎቹም ሁሉ፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕፃናት ሁሉ ተሻገሩ። በአገርም የነበሩት ሁሉ በታላቅ ድምፅ አለቀሱ፥ ሕዝቡም ሁሉ ተሻገሩ፥ ንጉሡም ደግሞ የቄድሮንን ፈፋ ተሻገረ፥ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ምድረ በዳ መንገድ ተሻገሩ። እነሆም፥ ደግሞ ሳዶቅ ከእርሱም ጋር ሌዋውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው መጡ፥ የእግዚአብሔርንም ታቦት አስቀመጡ፥ ሕዝቡም ሁሉ ከከተማይቱ ፈጽሞ እስኪያልፉ ድረስ አብያታር ወጣ። ንጉሡም ሳዶቅን፦ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማ መልስ፥ በእግዚአብሔር ዓይን ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆንሁ፥ መልሶ እርሱንና ማደሪያውን ያሳየኛል፥ ነገር ግን፦ አልወድድህም ቢለኝ፥ እነሆኝ፥ ደስ የሚያሰኘውን ያድርግብኝ አለው። ንጉሡም ደግሞ ካህኑን ሳዶቅን፦ እነሆ አንተና ልጅህ አኪማአስ የአብያታርም ልጅ ዮናታን ሁለቱ ልጆቻችሁ በደኅና ወደ ከተማ ተመለሱ። እኔም፥ እነሆ፥ ከእናንተ ዘንድ ወሬ እስኪመጣልኝ ድረስ በምድረ በዳው መሻገርያ እቆያለሁ አለው። ሳዶቅም አብያታርም የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም መለሱት፥ በዚያም ተቀመጡ። ዳዊትም ተከናንቦ ያለ ጫማ እያለቀሰ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ወጣ፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተከናንበው እያለቀሱ ወጡ። አኪጦፌል ከአቤሴሎም ጋር በሴራ አንድ ነው ብለው ለዳዊት ነገሩት፥ ዳዊትም፦ አቤቱ፥ የአኪጦፌልን ምክር ስንፍና አድርገህ እንድትለውጥ እለምንሃለሁ አለ። ዳዊትም ለእግዚአብሔር ወደ ሰገደበት ወደ ተራራው ራስ በመጣ ጊዜ፥ አርካዊው ኩሲ ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ። ዳዊትም አለው፦ ከእኔ ጋር ብትመጣ ትከብደኛለህ፥ ወደ ከተማ ግን ተመልሰህ ለአቤሴሎም፦ ንጉሥ ሆይ፥ ባሪያ እሆንሃለሁ፥ አስቀድሞ ለአባትህ ባሪያ እንደ ነበርሁ እንዲሁ አሁን ለአንተ ባሪያ እሆንሃለሁ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር ከንቱ ታደርግለኛለህ። ካህናቱ ሳዶቅና አብያታርም በዚያ ከአንተ ጋር አይደሉምን? ከንጉሡ ቤትም የምትሰማውን ነገር ሁሉ ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ንገራቸው። እነሆ፥ የሳዶቅ ልጅ አኪማአስና የአብያታር ልጅ ዮናታን ልጆቻቸው በዚያ ከእነርሱ ጋር አሉ፥ የምትሰሙትን ሁሉ በእነርሱ እጅ ላኩልኝ። የዳዊትም ወዳጅ ኩሲ ወደ ከተማ መጣ፥ አቤሴሎምም ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ።
2 ሳሙኤል 15:1-37 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ አቤሴሎም አንድ ሠረገላና ፈረሶች ለራሱ አደራጀ፤ እንዲሁም ኀምሳ ጋሻ ጃግሬዎች እንዲኖሩት አደረገ፤ በማለዳ እየተነሣ በመሄድ ወደ ከተማይቱ ቅጽር በር በሚያስገባው መንገድ ዳር ይቆም ነበር፤ ንጉሡ ጉዳዩን እንዲያይለት የሚፈልግ ጠብ ክርክር ያለበት ሰው ሁሉ ወደዚያ ሲመጣ አቤሴሎም ጠርቶ ከወዴት እንደ መጣ ይጠይቀዋል፤ ሰውየው ከየትኛው ነገድ መሆኑን ከነገረው በኋላ፥ አቤሴሎም፥ “ተመልከት፤ ሕግ አንተን ይደግፍሃል፤ ነገር ግን በንጉሡ ተወክሎ ጉዳይህን በትክክል የሚያይልህ የለም” ይለዋል፤ ንግግሩንም በመቀጠል “እኔ ዳኛ ብሆን እንዴት በወደድሁ ነበር! ክርክር ወይም አቤቱታ ያለበት ሰው ወደ እኔ ሲመጣ እኔ ትክክለኛውን ፍርድ እሰጠው ነበር” ይለዋል። ሰውየው በፊቱ ለጥ ብሎ እጅ ለመንሣት በሚቀርብበት ጊዜ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ በማቀፍ ይስመዋል። አቤሴሎም ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ ለሚመጡት ሁሉ እንደዚህ ያደርግ ስለ ነበር የእነርሱን ልብ ለመማረክ ቻለ። ከአራት ዓመት በኋላ አቤሴሎም ንጉሥ ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ ሆይ! ለእግዚአብሔር የተሳልኩትን ስእለት ለመፈጸም ወደ ኬብሮን እንድሄድ ፍቀድልኝ! እኔ አገልጋይህ በሶርያ በምትገኘው በገሹር በኖርኩበት ጊዜ ‘ወደ ኢየሩሳሌም ብትመልሰኝ መሥዋዕት አቀርብልሃለሁ’ ብዬ ለእግዚአብሔር ስእለት ተስዬ ነበር።” ንጉሡም “በሰላም ሂድ!” አለው፤ ስለዚህም አቤሴሎም ወደ ኬብሮን ሄደ፤ “ነገር ግን ወደ እስራኤል ነገዶች ሁሉ መልእክተኞችን ልኮ የእምቢልታ ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ ድምፃችሁን ከፍ በማድረግ ‘አቤሴሎም የኬብሮን ንጉሥ ሆኗል!’ ብላችሁ ጩኹ” ብለው እንዲነግሩአቸው አደረገ። በአቤሴሎም ጋባዥነት ከእርሱ ጋር ከኢየሩሳሌም የሄዱ ሁለት መቶ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ተከትለውት የሄዱት ስለ ሤራው ምንም ነገር ሳያውቁ በቅንነት ነበር። አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ከንጉሥ ዳዊት አማካሪዎች አንዱ የሆነውን አኪጦፌል ተብሎ የሚጠራውን ሰው መልእክተኛ በመላክ ከጊሎ ከተማ አስጠራ፤ በንጉሡ ላይ የተጠነሰሰው ሤራ እየጠነከረ፥ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቊጥር እየጨመረ ሄደ። አንድ መልእክተኛ ዳዊትን “እስራኤላውያን ታማኝነታቸውን ለአቤሴሎም በመግለጥ ላይ ናቸው” አለው። ስለዚህም ዳዊት ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ለሚገኙት መኳንንቱ ሁሉ “ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ ከፈለግን በፍጥነት ከዚህ ሸሽተን እንውጣ! እንግዲህ ፍጠኑ! አለበለዚያ በፍጥነት መጥቶ ድል ይመታናል፤ በከተማይቱ ያገኘውንም ሁሉ ይገድላል!” አላቸው። እነርሱም “እሺ ንጉሥ ሆይ! አንተ ያልከውን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁዎች ነን” ሲሉ መለሱለት። ስለዚህ ንጉሡ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቁለት ዘንድ ካስቀራቸው ዐሥር ቊባቶች በቀር ቤተሰቡንና መኳንንቱን ሁሉ በማስከተል ሸሽቶ ሄደ። ንጉሡና ተከታዮቹ ሁሉ ከከተማይቱ ወጥተው በሚሄዱበት ጊዜ በከተማይቱ መጨረሻ ላይ በሚገኘው አንድ ቤት አጠገብ ቆሙ፤ ባለሟሎቹ ሁሉ በእርሱ በኩል አለፉ፤ የዳዊት ክብር ዘበኞች የነበሩት ከሪታውያንና ፈሊታውያን፥ እንዲሁም ከጋት የመጡ ስድስት መቶ ጌታውያን በንጉሡ ፊት አለፉ፤ ንጉሡም ኢታይ ተብሎ የሚጠራውን የጌት ሰው እንዲህ አለው፤ “ከእኛ ጋር ለምን ትሄዳለህ? ተመልሰህ ከአዲሱ ንጉሥ ጋር ቈይ፤ አንተ ከአገርህ ወጥተህ በመጻተኛነት እዚህ የምትኖር የውጪ አገር ሰው ነህ፤ በዚህ አገር የኖርከውም ለአጭር ጊዜ ነው፤ ታዲያ አንተ ከእኔ ጋር የምትንከራተተው ስለምንድን ነው? እኔ የት እንደምሄድ እንኳ አላውቅም፤ ስለዚህ የአገርህን ሰዎች ይዘህ ተመለስ፤ እግዚአብሔር ቸርነቱንና እውነተኛነቱን ይግለጥልህ።” ኢታይ ግን ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ጌታዬ በሚኖርበት ቦታ ሁሉ፥ በሞትም ሆነ በሕይወት እኔ አገልጋይህ በዚያ እንደምገኝ በእግዚአብሔር ስም እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ ሕይወት እምላለሁ።” ዳዊትም “መልካም ነው! እንግዲህ ጒዞህን ቀጥል!” አለው፤ ስለዚህም ኢታይ ከወታደሮቹ ሁሉና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጒዞውን ቀጠለ፤ የዳዊት ተከታዮች ወጥተው በሄዱ ጊዜ ሕዝቡ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ንጉሡ ከተከታዮቹ ጋር የቄድሮንን ወንዝ ተሻገረ፤ በአንድነትም ሆነው ወደ በረሓው አመሩ። ካህኑ ሳዶቅም እዚያው ነበር፤ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ሌዋውያን ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ የቃል ኪዳኑን ታቦት፥ ሕዝቡ ሁሉ ከተማውን ለቆ እስኪወጣ ድረስ በአብያታር አጠገብ አስቀመጡት። ከዚህ በኋላ ንጉሡ ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ከተማይቱ መልሰህ ውሰድ፤ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያገኘሁ እንደ ሆነ አንድ ቀን ታቦቱንና ማደሪያውን እንዳይ ይፈቅድልኝ ይሆናል፤ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ባላገኝ ግን በእኔ ላይ የወደደውን ያድርግ።” ንግግሩንም በመቀጠል ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “ተመልከት፤ ልጅህን አሒማዓጽንና የአብያታርንም ልጅ ዮናታንን ይዘህ ወደ ከተማይቱ በሰላም ሂድ፤ እኔም ከአንተ ወሬ እስከማገኝ ድረስ በበረሓው ውስጥ በሚገኘው በወንዙ መሸጋገሪያ ላይ እጠባበቃለሁ።” ስለዚህም ሳዶቅና አብያታር የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም መልሰው ወሰዱ፤ በዚያም ቈዩ። ዳዊትም ሐዘኑን በመግለጥ ጫማ ሳያደርግ ራሱን ተከናንቦ የደብረ ዘይትን አቀበት እያለቀሰ ወጣ፤ የተከተሉትም ሁሉ ደግሞ ራሳቸውን ተከናንበው ያለቅሱ ነበር። ዳዊት፥ አኪጦፌል ከአቤሴሎም ጋር በዐመፅ መተባበሩን በሰማ ጊዜ “እግዚአብሔር ሆይ! የአኪጦፌልን ምክር ወደ ከንቱነት እንድትለውጥበት እለምንሃለሁ!” ሲል ጸለየ። ዳዊት የማምለኪያ ስፍራ ወዳለበት ወደ ኮረብታው ጫፍ በደረሰ ጊዜ ታማኝ ጓደኛው የሆነው አርካዊው ሑሻይ ልብሱን ቀዶና በራሱ ላይ ትቢያ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ። ዳዊትም እንዲህ አለው፦ “አንተ እኔን ተከትለህ ብትሄድ ወደ ኋላ ትጐትተናለህ፤ አንተ እኔን ልትረዳኝ የምትችለው ግን ወደ ከተማይቱ ተመልሰህ አቤሴሎምን፥ አባትህን እንዳገለገልኩ አንተንም በታማኝነት አገለግላለሁ ብለህ ብትነግረው እንዲሁም አኪጦፌል የሚሰጠውን ምክር ሁሉ ብትቃወምልኝ ነው፤ ካህናቱ ሳዶቅና አብያታርም በዚያው ይገኛሉ፤ በቤተ መንግሥት የምትሰማውን ነገር ሁሉ ለእነርሱ ትነግራቸዋለህ፤ ከእነርሱም ጋር ልጆቻቸው አሒማዓጽና ዮናታን ይገኛሉ፤ የምታገኘውንም ወሬ ሁሉ በእነርሱ በኩል ልትልክብኝ ትችላለህ።” ስለዚህም የዳዊት ወዳጅ ሑሻይ ወደ ከተማይቱ ተመለሰ፤ አቤሴሎምም ወዲያውኑ እዚያ ደረሰ።
2 ሳሙኤል 15:1-37 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚህ በኋላ አቤሴሎም ሠረገላና ፈረሶች፥ ፊት ፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ። አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ይቆም ነበር። ማናቸውም ባለ ጉዳይ አቤቱታውን ለንጉሡ አቅርቦ ለማስወሰን በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ፥ አቤሴሎም ወደ እርሱ እየጠራ፥ “አንተ ከየትኛው ከተማ ነው የመጣኸው?” በማለት ይጠይቀዋል፤ ያም ሰው፥ “አገልጋይህ ከእስራኤል ነገዶች ከአንዱ ነው” ብሎ ይመልስለታል። ከዚያም አቤሴሎም፥ “ተመልከት! ጉዳይህማ ትክክልና ተገቢም ነው፤ ነገር ግን ከንጉሥ ተወክሎ የሚሰማህ የለም” ይለው ነበር። ከዚህም ሌላ አቤሴሎም፥ “በምድሪቱ ላይ ዳኛ እኔ በሆንኩ ኖሮ! አቤቱታ ወይም ክስ ያለበት ሁሉ ወደ እኔ ሲመጣ፥ ፍትሕ እንዲያገኝ ባደረግሁ ነበር” ይል ነበር። እንዲሁም ማናቸውም ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ እጅ በሚነሣው ጊዜ፥ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር። አቤሴሎም ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ ለሚመጣ እስራኤላዊ ሁሉ አቀራረቡ እንዲህ ነበር፤ ስለዚህ አቤሴሎም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ። ከአራት ዓመት በኋላም አቤሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “በኬብሮን ለጌታ የተሳልሁትን ስእለት ለማድረስ እንድሄድ ፍቀድልኝ፤ እኔ አገልጋይህ በሶርያ ምድር በገሹር ሳለሁ ‘ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም የመለሰኝ እንደሆነ፥ በኬብሮን ለጌታ እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስያለሁ።” ንጉሡም፥ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ተነሥቶም ወደ ኬብሮን ሄደ። ነገር ግን አቤሴሎም፥ በመላው የእስራኤል ነገዶች መሀል “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ፥ ‘አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ’ ” የሚሉ የምስጢር መልእክተኞችን ላከ። ከአቤሴሎም ጋር ከኢየሩሳሌምም ሁለት መቶ ሰዎች አብረውት ሄደው ነበር፤ በእንግድነት ተጋብዘው በቅንነት ከመሄዳቸው በስተቀር፥ ስለጉዳዩ ምንም ነገር አያውቁም ነበር። አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ የሆነው ጊሎአዊው አኪጦፌል ከአገሩ ከጊሎ ወደ እርሱ እንዲመጣ ላከበት፤ ስለዚህ ሤራው ጥንካሬ አገኘ፤ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቍጥር እየበዛ ሄደ። መልእክተኛም መጥቶ፥ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኖአል” ብሎ ለዳዊት ነገረው። ከዚያም ዳዊት በኢየሩሳሌም ላሉት አገልጋዮቹ ሁሉ፥ “ተነሡ እንሽሽ፤ ያለበለዚያ ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ አንችልም፤ ፈጥኖ እንዳይዘን፥ ክፉም እንዳያመጣብን፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ስለት እንዳይመታ ፈጥናችሁ እንሂድ” አላቸው። የንጉሡ አገልጋዮቹም፥ “ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ ለማድረግ እኛ አገልጋዮችህ ዝግጁ ነን” ብለው መለሱለት። ስለዚህ ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ ካስቀራቸው ዐሥር ዕቁባቶች በቀር፥ ንጉሡም እርሱንም ተከትለው መላው ቤተሰቡ ሸሹ፤ ንጉሡም እርሱንም ተከትለው ሕዝቡ ሁሉ ወጣ፤ ርቀው ከሄዱ በኋላም በአንዲት ቤት ቆሙ። አገልጋዮቹ ሁሉ፥ ከሊታውያን፥ ፈሊታውያን እንዲሁም ከጌት አብረውት የመጡትን ስድስት መቶ ጌታውያን ሁሉን ጨምሮ ተሰልፈው በንጉሡ ፊት ዐለፉ። ንጉሡም የጌታዊውን ሰው ኢታይን እንዲህ አለው፤ “አንተም ከእኛ ጋር አብረህ የመጣኸው ለምንድን ነው? ተመለስና ከንጉሥ አቤሴሎም ጋር ተቀመጥ፤ አንተ እኮ ከስፍራህ በግዞት የመጣህ መጻተኛ ነህ፤ የመጣኸውም ገና ትናንት ነው፤ ታዲያ የት እንደምሄድ የማላውቅ ሰው እንዴት ዛሬ ከእኛ ጋር እንድትንከራተት ላድርግ? ተነሥ ሰዎችህን ይዘህ ተመለስ፤ ታማኝነትና እውነተኛነትም ከአንተ ጋር ይሁን” አለው። ኢታይ ግን፥ “በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ! እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ እምላለሁ፤ ሕይወትም ይሁን ሞት በየትም ቦታ ንጉሥ ጌታዬ የሚሆነውን ሁሉ አገልጋይህም እንደዚያው እሆናለሁ” ብሎ መለሰለት። ዳዊትም ኢታይን፥ “እንግዲያውስ ቅደምና ሂድ” አለው። ስለዚህ ጌታዊው ኢታይ ሰዎቹን ሁሉና አብረውት የነበሩትን ቤተሰቦቹን ይዞ ሄደ። ሕዝቡ ሁሉ በሚያልፍበትም ጊዜ ባላገሩ በሙሉ እየጮኸ አለቀሰ፤ ንጉሡም የቄድሮንን ወንዝ ተሻገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሻግሮ ወደ ምድረ በዳው አመሩ። ሳዶቅም በዚያ ነበር፤ አብረውት የነበሩትም ሌዋውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው መጡ፥ የእግዚአብሔርንም ታቦት፥ ሕዝቡ በሙሉ ከከተማዪቱ ለቆ እስኪ ወጣ ድረስ፥ አብያታር አጠገብ አስቀመጡ። ከዚያም ንጉሡ ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማይቱ ይዘህ ተመለስ፤ በጌታ ፊት ሞገስ ያገኝሁ እንደሆነ፥ እርሱ እኔንም መልሶ ታቦቱንና ማደሪያውን ያሳየኛል፤ ነገር ግን እርሱ፥ ‘ባንተ አልተደሰትሁም’ የሚል ከሆነ፥ እነሆኝ፥ መልካም መስሎ የታየውን ነገር ያድርግብኝ።” እንዲሁም ንጉሡ ካህኑን ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ ነቢይ አይደለህምን? ይሄውልህ አንተም ልጅህን አሒማአስን፥ የአብያታርን ልጅ ዮናታንን ይዘህ በሰላም ወደ ከተማዪቱ ተመለስ። አንተና አብያታር ሁለቱን ልጆቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ። እኔም ከአንተ ዘንድ ወሬ እስካገኝ ድረስ በምድረ በዳው በሚገኘው በወንዙ መሻገሪያ እቆያለሁ” ስለዚህ ሳዶቅና አብያታር የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም መለሱት፥ በዚያም ተቀመጡ። ዳዊት ግን እያለቀሰ፥ ራሱን ተከናንቦ፥ ባዶ እግሩን የደብረ ዘይትን ተራራ ወጣ፤ አብሮት ያለውም ሕዝብ ሁሉ እንደዚሁ ራሱን ተከናንቦ እያለቀሰ ተራራውን ይወጣ ነበር። በዚህ ጊዜ፥ “ከአቤሴሎም ጋር ካሤሩት መካከል አንዱ አኪጦፌል ነው” ብለው ለዳዊት ነገሩት። ዳዊትም፥ “ጌታ ሆይ! እባክህን የአኪጦፌልን ምክር ወደ ከንቱነት ለውጠው” ሲል ጸለየ። ዳዊት ሕዝቡ እግዚአብሔርን ወደሚያመልክበት ወደ ተራራው ጫፍ በደረሰ ጊዜ፥ አርካዊው ሑሻይ ልብሱን ቀዶ ትቢያ በራሱ ላይ ነስንሶ ሊያገኘው መጣ። ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለው፤ “አብረኸኝ ብትሄድ ሸክም ትሆንብኛለህ፤ ነገር ግን ወደ ከተማዪቱ ተመልሰህ አቤሴሎምን፥ ‘ንጉሥ ሆይ፤ አገልጋይህ እሆናለሁ፤ ቀድሞ የአባትህ አገልጋይ እንደ ነበርሁ ሁሉ፥ ዛሬም አንተን አገለግልሃለሁ’ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር በማፍረስ ትረዳኛለህ። ካህናቱ ሳዶቅና አብያታር በዚያ ከአንተው ጋር አይደሉምን? ስለዚህ ከቤተ መንግሥቱ የምትሰማትን ሁሉ ለሳዶቅና ለአብያታር ንገራቸው። እነሆ፥ የሳዶቅ ልጅ አሒማአስና የአብያታር ልጅ ዮናታን፥ ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው እዚያው አብረዋቸው ይገኛሉ። የምትሰማትን ሁሉ በእነርሱ ላክልኝ።” ስለዚህ የዳዊት ወዳጅ ሑሻይ ልክ አቤሴሎም ኢየሩሳሌም በገባበት ሰዓት ወደ ከተማዋ ደረሰ።