የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15

15
1ከዚህም በኋላ አቤሴሎም ሰረገላና ፈረሶች፥ በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ። 2አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ በበሩ አደበባይ ይቆም ነበር፥ አቤሴሎምም ከንጉሥ ለማስፈረድ ጉዳይ የነበረውን ሁሉ ወደ እርሱ እየጠራ፦ አንተ ከወዴት ከተማ ነህ? ብሎ ይጠይቅ ነበር። እርሱም፦ እኔ ባሪያህ ከእስራኤል ነገድ ከአንዲቱ ነኝ ብሎ ይመልስ ነበር። 3አቤሴሎምም፦ ነገርህ እውነትና ቅን ነው፥ ነገር ግን ከንጉሥ ታዝዞ የሚሰማህ የለም ይለው ነበር። 4አቤሴሎምም፦ ነገርና ክርክር ያለው ሁሉ ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ ቅንም ፍርድ እፈርድለት ዘንድ በአገር ላይ ፈራጅ አድርጎ ማን በሾመኝ? ይል ነበር። 5ሰውም እጅ ሊነሣው ወደ እርሱ በቀረበ ጊዜ እጁን ዘርግቶ ይይዝና ይስመው ነበር። 6እንዲሁም አቤሴሎም ከንጉሥ ፍርድ ሊሰማ ከእስራኤል ዘንድ በሚመጣ ሁሉ ያደርግ ነበር፥ አቤሴሎምም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ።
7እንዲህም ሆነ፥ ከአራት ዓመት በኋላ አቤሴሎም ንጉሡን፦ ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት ለመስጠት ወደ ኬብሮን፥ እባክህ፥ ልሂድ። 8እኔ ባሪያህ በሶርያ ጌሹር ሳለሁ፦ እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም ቢመልሰኝ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀርባለሁ ብዬ ስእለት ተስዬ ነበር አለው። 9ንጉሡም፦ በደኅና ሂድ አለው፥ ተነሥቶም ወደ ኬብሮን ሄደ። 10አቤሴሎምም በእስራኤል ነገድ ሁሉ፦ የቀንደ መለከት ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፦ አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ የሚሉ ጉበኞች ላከ። 11የተጠሩትም ሁለት መቶ ሰዎች ከአቤሴሎም ጋር በየዋህነት ከኢየሩሳሌም ሄዱ፥ የሚሆነውንም ነገር ከቶ አያውቁም ነበር። 12አቤሴሎምም የዳዊት መካር የነበረውን የጊሎ ሰው አኪጦፌልን ከከተማው ከጊሎ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ አስጠራው። ሴራውም ጽኑ ሆነ፥ ከአቤሴሎምም ጋር ያለውች ሕዝብ እየበዛ ሄደ።
13ለዳዊትም፦ የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኖአል የሚል ወሬኛ መጣለት። 14ዳዊትም ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ያሉትን ባሪያዎቹን ሁሉ፦ ተነሡ፥ እንሽሽ፥ ያለዚያ ከአቤሴሎም እጅ የሚድን ከእኛ የለምና፥ መጥቶም እንዳይዘን፥ ክፉም እንዳያመጣብን ከተማይቱንም በሰይፍ ስለት እንዳይመታ ፈጥናችሁ እንሂድ አላቸው። 15የንጉሡም ባሪያዎች ንጉሡን፦ እነሆ፥ ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ እኛ ባሪያዎችህ እሺ ብለን እናደርጋለን አሉት። 16ንጉሡም ከእርሱም በኋላ ቤተ ሰቡ ሁሉ ወጡ፥ ንጉሡም አሥሩን ሴቶች ቁባቶቹን ቤቱን ይጠብቁ ዘንድ ተወ። 17ንጉሡም ከእርሱም በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ወጡ፥ በቤትሜርሐቅም ቆሙ። 18ባሪያዎቹም ሁሉ በፊቱ አለፉ፥ ከሊታውያንና ፈሊታውያንም ሁሉ፥ ከእርሱም በኋላ ከጌት የመጡት ስድስት መቶው ጌታውያን ሁሉ በንጉሡ ፊት አለፉ።
19ንጉሡም የጌት ሰው ኢታይን፦ ከእኛ ጋር ለምን መጣህ? አንተ ከስፍራህ የመጣህ እንግዳና ስደተኛ ነህና ተመለስ፥ ከንጉሡም ጋር ተቀመጥ። 20የመጣኸው ትናንት ነው፥ ዛሬ ከእኛ ጋር ላዙርህን? እኔ ወደምሄድበት እሄዳለሁ፥ አንተ ግን ተመለስ፥ ወንድሞችህንም ከአንተ ጋር ውሰድ፥ እግዚአብሔርም ምሕረቱንና እውነቱን ያድርግልህ አለው። 21ኢታይም ለንጉሡ መልሶ፦ ሕያው እግዚአብሔርን! በጌታዬም በንጉሡ ሕይወት እምላለሁ! በእውነት ጌታዬ ባለበት ስፍራ ሁሉ፥ በሞትም ቢሆን በሕይወትም፥ በዚያ ደግሞ እኔ ባሪያህ እሆናለሁ አለው። 22ዳዊትም ኢታይን፦ ሂድ ተሻገር አለው፥ የጌት ሰው ኢታይና ሰዎቹም ሁሉ፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕፃናት ሁሉ ተሻገሩ። 23በአገርም የነበሩት ሁሉ በታላቅ ድምፅ አለቀሱ፥ ሕዝቡም ሁሉ ተሻገሩ፥ ንጉሡም ደግሞ የቄድሮንን ፈፋ ተሻገረ፥ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ምድረ በዳ መንገድ ተሻገሩ።
24እነሆም፥ ደግሞ ሳዶቅ ከእርሱም ጋር ሌዋውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው መጡ፥ የእግዚአብሔርንም ታቦት አስቀመጡ፥ ሕዝቡም ሁሉ ከከተማይቱ ፈጽሞ እስኪያልፉ ድረስ አብያታር ወጣ። 25ንጉሡም ሳዶቅን፦ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማ መልስ፥ በእግዚአብሔር ዓይን ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆንሁ፥ መልሶ እርሱንና ማደሪያውን ያሳየኛል፥ 26ነገር ግን፦ አልወድድህም ቢለኝ፥ እነሆኝ፥ ደስ የሚያሰኘውን ያድርግብኝ አለው። 27ንጉሡም ደግሞ ካህኑን ሳዶቅን፦ እነሆ አንተና ልጅህ አኪማአስ የአብያታርም ልጅ ዮናታን ሁለቱ ልጆቻችሁ በደኅና ወደ ከተማ ተመለሱ። 28እኔም፥ እነሆ፥ ከእናንተ ዘንድ ወሬ እስኪመጣልኝ ድረስ በምድረ በዳው መሻገርያ እቆያለሁ አለው። 29ሳዶቅም አብያታርም የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም መለሱት፥ በዚያም ተቀመጡ።
30ዳዊትም ተከናንቦ ያለ ጫማ እያለቀሰ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ወጣ፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተከናንበው እያለቀሱ ወጡ። 31አኪጦፌል ከአቤሴሎም ጋር በሴራ አንድ ነው ብለው ለዳዊት ነገሩት፥ ዳዊትም፦ አቤቱ፥ የአኪጦፌልን ምክር ስንፍና አድርገህ እንድትለውጥ እለምንሃለሁ አለ። 32ዳዊትም ለእግዚአብሔር ወደ ሰገደበት ወደ ተራራው ራስ በመጣ ጊዜ፥ አርካዊው ኩሲ ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ። 33ዳዊትም አለው፦ ከእኔ ጋር ብትመጣ ትከብደኛለህ፥ 34ወደ ከተማ ግን ተመልሰህ ለአቤሴሎም፦ ንጉሥ ሆይ፥ ባሪያ እሆንሃለሁ፥ አስቀድሞ ለአባትህ ባሪያ እንደ ነበርሁ እንዲሁ አሁን ለአንተ ባሪያ እሆንሃለሁ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር ከንቱ ታደርግለኛለህ። 35ካህናቱ ሳዶቅና አብያታርም በዚያ ከአንተ ጋር አይደሉምን? ከንጉሡ ቤትም የምትሰማውን ነገር ሁሉ ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ንገራቸው። 36እነሆ፥ የሳዶቅ ልጅ አኪማአስና የአብያታር ልጅ ዮናታን ልጆቻቸው በዚያ ከእነርሱ ጋር አሉ፥ የምትሰሙትን ሁሉ በእነርሱ እጅ ላኩልኝ። 37የዳዊትም ወዳጅ ኩሲ ወደ ከተማ መጣ፥ አቤሴሎምም ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ