ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 14
14
1የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ የንጉሡ ልብ ወደ አቤሴሎም እንዳዘነበለ አወቀ። 2ኢዮአብም ወደ ቴቁሔ ልኮ ከዚያ ብልሃተኛ ሴት አስመጣና፦ አልቅሺ፥ የኅዘንም ልብስ ልበሺ፥ ዘይትም አትቀቢ፥ ስለ ሞተ ሰውም ብዙ ዘመን እንደምታለቅሺ ሁኚ፥ 3ወደ ንጉሡም ገብተሽ እንዲህ ያለውን ቃል ንገሪው አላት፥ ኢዮአብም ቃሉን በእርስዋ አፍ አደረገ።
4እንዲሁም የቴቁሔይቱ ሴት ወደ ንጉሥ ገብታ በግምባርዋ በምድር ላይ ወደቀች፥ እጅ ነሥታም፦ ንጉሥ ሆይ፥ አድነኝ አለች። 5ንጉሡም፦ ምን ሆነሻል? አላት። እርስዋም መልሳ አለች፦ ክ በእውነት እኔ ባሌ የሞተብኝ ባልቴት ሴት ነኝ። 6ለእኔም ለባሪያህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፥ በሜዳም ተጣሉ፥ የሚገላግላቸውም አልነበረም፥ አንዱም ሌላውን መትቶ ገደለው። 7እነሆም፥ ዘመዶች ሁሉ በባሪያህ ላይ ተነሥተው፦ ስለ ገደለው ስለ ወንድሙ ነፍስ እንገድለው ዘንድ ወንድሙን የገደለውን አውጪ አሉኝ፥ እንዲሁም ደግሞ ወራሹን የቀረውን መብራቴን ያጠፋሉ፥ የባሌን ስምና ዘርም ከምድር ላይ አያስቀሩም።
8ንጉሡም ሴቲቱን፦ ወደ ቤትሽ ሂጂ፥ እኔም ስለ አንቺ አዝዛለሁ አላት። 9የቴቁሔይቱም ሴት ንጉሡን፦ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ኃጢአቱ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ይሁን፥ ንጉሡና ዙፋኑ ንጹሕ ይሁን አለችው። 10ንጉሡም፦ የሚናገርሽን አምጪልኝ፥ ከዚያም በኋላ ደግሞ አይነካሽም አለ። 11እርስዋም፦ ደም ተበቃዮችም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይጠፉ ልጄንም እንዳይገድሉ፥ ንጉሡ አምላኩን እግዚአብሔርን ያስብ አለች። እርሱም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ከልጅሽ አንድ ጠጕር በምድር ላይ አይወድቅም አለ።
12ሴቲቱም፦ እኔ ባሪያህ ለጌታዬ ለንጉሥ አንድ ቃል ልናገር አለች፥ እርሱም፦ ተናገሪ አለ። 13ሴቲቱም አለች፦ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ስለምን አሰብህ? ንጉሡ ይህን ነገር ተናግሮአልና ያሳደደውን ስላላስመለሰ በደለኛ ነው። 14ሁላችን እንሞታለን፥ በምድርም ላይ እንደ ፈሰሰና እንደማይመለስ ውኃ ነን፥ እግዚአብሔርም የነፍስን ጥፋት አይወድድም፥ ነገር ግን የተጣለ ሰው ፈጽሞ እንዳይጠፋ በምክሩ ያስባል። 15አሁንም ሕዝቡ ስለሚያስፈራኝ ይህን ነገር ለጌታዬ ለንጉሥ እነግረው ዘንድ መጥቻለሁ፥ እኔም ባሪያህ፦ ምናልባት የእኔን የባሪያውን ልመና ንጉሡ ያደርግልኝ እንደሆነ ለንጉሡ ልናገር፥ 16እርስዋንና ልጅዋን ከእግዚአብሔር ርስት ያጠፋቸው ዘንድ ከሚሻ ሰው እጅ ያድን ዘንድ ንጉሡ ባሪያውን ይሰማል አልሁ። 17እኔም ባሪያህ፦ መልካሙንና ክፉውን ነገር ለመስማት ንጉሡ ጌታዬ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነውና የጌታዬ የንጉሡ ቃል ያጽናናኛል፥ አምላክህም እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን አልሁ።
18ንጉሡም ለሴቲቱ መልሶ፦ የምጠይቅሽን ነገር አትሰውሪኝ አላት። ሴቲቱም፦ ጌታዬ ንጉሥ ይናገር አለች። 19ንጉሡም፦ በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ ከአንቺ ጋር ነውን? አላት። ሴቲቱም መልሳ፦ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ጌታዬ ንጉሥ ከተናገረው ነገር ሁሉ ወደ ቀኝ ወደ ግራም ሊል የሚችል የለም፥ ባሪያህ ኢዮአብ አዝዞኛል፥ ይህንም ቃል ሁሉ በባሪያህ አፍ አደረገው። 20ባሪያህ ኢዮአብ የዚህ ነገር መልክ እንዲለውጥ አደረገ፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ጠቢብ እንደ ሆነ፥ አንተም ጌታዬ በምድር ላይ ያለውን ነገር ሁሉ ታውቅ ዘንድ ጠቢብ ነህ አለች።
21ንጉሡም ኢዮአብን፦ እነሆ፥ ይህን ነገር አድርጌአለሁ፥ እንግዲህ ሂድና ብላቴናውን አቤሴሎምን መልሰው አለው። 22ኢዮአብም በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ እጅ ነሣ፥ ንጉሡንም ባረከ፥ ኢዮአብም፦ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የባሪያህን ነገር አድርገሃልና በዓይንህ ፊት ሞገስ እንዳገኘ ባሪያህ ዛሬ አወቀ አለ። 23ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ ጌሹር ሄደ፥ አቤሴሎምንም ወደ ኢየሩሳሌም ይዞ መጣ። 24ንጉሡም፦ ወደ ቤቱ ይሂድ እንጂ ፊቴን እንዳያይ አለ፥ አቤሴሎምም ወደ ቤቱ ሄደ፥ የንጉሡንም ፊት አላየም።
25በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ እንደ አቤሴሎም በውበቱ የተመሰገነ ሰው አልነበረም፥ ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር አልነበረበትም። 26ጠጕሩም ይከብደው ነበርና በዓመት አንድ ጊዜ ይቆርጠው ነበር፥ ሲቆርጥም የራሱ ጠጕር በንጉሥ ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ያህል ይመዘን ነበር። 27ለአቤሴሎምም ሦስት ወንዶች ልጆችና አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት፥ የሴቲቱም ልጅ ስም ትዕማር ነበረ፥ እርስዋም የተዋበች ሴት ነበረች።
28አቤሴሎምም በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ሙሉ የንጉሡን ፊት ሳያይ ተቀመጠ። 29አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ ይልከው ዘንድ ወደ ኢዮአብ ላከ፥ ወደ እርሱም ሊመጣ አልወደደም፥ ሁለተኛም ላከበት፥ ሊመጣ ግን አልወደደም። 30ባሪያዎቹንም፦ በእርሻዬ አጠገብ ያለውን የኢዮአብን እርሻ እዩ፥ በዚያም ገብስ አለው፥ ሂዳችሁ በእሳት አቃጥሉት አላቸው። የአቤሴሎምም ባሪያዎች እርሻውን አቃጠሉት። 31ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ አቤሴሎም ወደ ቤቱ መጣና፦ ባሪያዎችህ እርሻዬን ስለምን አቃጠሉት? አለው። 32አቤሴሎምም ኢዮአብን መልሶ፦ ከጌሹር ለምን መጣሁ? በዚያም ተቀምጩ ብሆን ይሻለኝ ነበር ብለህ እንድትነግረው ወደ ንጉሡ እልክህ ዘንድ ወደ እኔ ጠራሁህ፥ አሁንም የንጉሡን ፊት ልይ፥ ኃጢአት ቢሆንብኝ ይግደለኝ አለው። 33ኢዮአብም ወደ ንጉሥ መጥቶ ነገረው፥ አቤሴሎምንም ጠራው፥ ወደ ንጉሡም ገብቶ በንጉሥ ፊት ወደ ምድር በግምባሩ ተደፋ፥ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 14: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ