የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 16

16
1ዳዊትም ከተራራው ራስ ጥቂት ፈቀቅ ባለ ጊዜ የሜምፊቦስቴ ባሪያ ሲባ ሁለት መቶ እንጀራ፥ አንድ መቶም ዘለላ ዘቢብ፥ አንድ መቶም በለስ፥ አንድ አቁማዳም ወይን ጠጅ የተጫኑ ሁለት አህዮች እየነዳ ተገናኘው። 2ንጉሡም ሲባን፦ ይህ ምንድር ነው? አለው። ሲባም፦ አህዮቹ የንጉሥ ቤተ ሰቦች ይቀመጡባቸው ዘንድ፥ እንጀራውና በለሱ ብላቴኖቹ ይበሉት ዘንድ፥ የወይን ጠጅም በበረሀ የሚደክሙት ይጠጡት ዘንድ ነው አለ። 3ንጉሡም፦ የጌታህ ልጅ ወዴት ነው? አለ። ሲባም ንጉሡን፦ እነሆ፦ የእስራኤል ቤት ዛሬ የአባቴን መንግሥት ይመልስልኛል ብሎ በኢየሩሳሌም ተቀምጦአል አለው። 4ንጉሡም ሲባን፦ እነሆ፥ ለሜምፊቦስቴ የነበረው ሁሉ ለአንተ ይሁን አለው። ሲባም፦ እጅ እነሣለሁ፥ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ በፊትህ ሞገስ ላግኝ አለ።
5ንጉሡ ዳዊትም ወደ ብራቂም መጣ፥ እነሆም፥ ሳሚ የሚባል የጌራ ልጅ ከሳኦል ቤተ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው ከዚያ ወጣ፥ እየሄደም ይረግመው ነበር። 6ወደ ዳዊትና ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ባሪያዎች ድንጋይ ይወረውር ነበር፥ በንጉሡም ቀኝና ግራ ሕዝቡ ሁሉና ኃያላኑ ሁሉ ነበሩ። 7ሳሚም ሲረግም፦ ሂድ፥ አንተ የደም ሰው፥ ምናምንቴ፥ ሂድ። 8በፋንታው ነግሠሃልና እግዚአብሔር የሳኦልን ቤት ደም ሁሉ መለሰብህ፥ እግዚአብሔርም መንግሥትን ለልጅህ ለአቤሴሎም እጅ አሳልፎ ሰጥቶታል፥ እነሆም፥ አንተ የደም ሰው ነህና በመከራ ተይዘሃል አለ።
9የጽሩያም ልጅ አቢሳ ንጉሡን፦ ይህ የሞተ ውሻ ጌታዬን ንጉሡን ስለምን ይረግማል? ልሂድና ራሱን ልቁረጠው አለው። 10ንጉሡም፦ እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? እግዚአብሔር፦ ዳዊትን ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ፥ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው? አለ። 11ዳዊትም አቢሳንና ባሪያዎቹን ሁሉ፦ እነሆ፥ ከወገቤ የወጣው ልጄ ነፍሴን ይሻል፥ ይልቁንስ ይህ የብንያም ልጅ እንዴት ነዋ? እግዚአብሔር አዝዞታልና ተዉት፥ ይርገመኝ። 12ምናልባት በዚህ ቀን መከራዬን አይቶ ስለ እርግማኑ መልካም ይመልስልኛል አላቸው። 13ዳዊትና ሰዎቹም በመንገድ ይሄዱ ነበር፥ ሳሚም በተራራው አጠገብ በእርሱ ትይዩ እየሄደ ይራገም ድንጋይም ይወረውር፥ ትቢያም ይበትን ነበር። 14ንጉሡና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ሁሉ ደክመው ነበር፥ በዚያም ዐረፉ።
15አቤሴሎምና ሕዝቡ ሁሉ የእስራኤልም ሰዎች አኪጦፌልም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 16የዳዊትም ወዳጅ አርካዊው ኩሲ ወደ አቤሴሎም በመጣ ጊዜ ኩሲ፦ ሺህ ዓመት ያንግሥህ አለው። 17አቤሴሎምም ኩሲን፦ ስለ ወዳጅህ ያደረግኸው ቸርነት ይህ ነውን? ከወዳጅህ ጋር ያልሄድህ ስለ ምንድር ነው? አለው። 18ኩሲም አቤሴሎምን፦ እንዲህ አይደለም፥ ከእግዚአብሔር ከዚህም ሕዝብ ከእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ለተመረጠው ለእርሱ እሆናለሁ ከእርሱም ጋር እቀመጣለሁ። 19ዳግምም የማገለግል ለማን ነው? በንጉሥ ልጅ ፊት አይደለምን? በአባትህ ፊት እንዳገለገልሁ እንዲሁ በአንተ ፊት እሆናለሁ አለው።
20አቤሴሎምም አኪጦፌልን፦ ምከሩ፥ ምን እናድርግ? አለው። 21አኪጦፌልም አቤሴሎምን፦ ቤት ሊጠብቁ ወደ ተዋቸው ወደ አባትህ ቁባቶች ግባ፥ እስራኤልም ሁሉ አባትህን እንዳሳፈረኸው ይሰማሉ፥ ከአንተም ጋር ያሉት ሁሉ እጃቸው ይበረታል አለው። 22ለአቤሴሎምም በሰገነት ላይ ድንኳን ተከሉለት፥ አቤሴሎምም በእስራኤል ሁሉ ፊት ወደ አባቱ ቁባቶች ገባ። 23በዚያም ወራት የመከራት የአኪጦፌል ምክር የእግዚአብሔርን ቃል እንደ መጠየቅ ነበረች፥ የአኪጦፌልም ምክር ሁሉ ከዳዊትና ከአቤሴሎም ጋር እንዲህ ነበረች።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ