ከዚህም በኋላ አቤሴሎም ሰረገላና ፈረሶች፥ በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ። አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ በበሩ ጎዳና ይቆም ነበር፤ አቤሴሎምም ከንጉሥ ለማስፈረድ ጉዳይ የነበረውን ሁሉ ወደ እርሱ እየጠራ፥ “አንተ ከወዴት ከተማ ነህ?” ብሎ ይጠይቅ ነበር። እርሱም፥ “እኔ አገልጋይህ ከእስራኤል ወገን ከአንዲቱ ነኝ” ይለው ነበር። አቤሴሎምም፥ “ነገርህ መልካም ነው፤ ቀላልም ነው፤ ነገር ግን ከንጉሥ ዘንድ የሚሰማህ የለም” ይለው ነበር። አቤሴሎምም፥ “ነገርና ክርክር ያለው ሁሉ ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ፥ ቅንም ፍርድ እፈርድለት ዘንድ በሀገር ላይ ፈራጅ አድርጎ ማን በሾመኝ?” ይል ነበር። ሰውም እጅ ለመንሣት ወደ እርሱ በቀረበ ጊዜ እጁን ዘርግቶ አቅፎ ይስመው ነበር። በንጉሡ ዘንድ ሊፋረዱ ለሚመጡ ለእስራኤል ሁሉ አቤሴሎም እንዲህ ያደርግ ነበር፤ አቤሴሎምም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ማረከ። እንዲህም ሆነ፤ ከአራት ዓመት በኋላ አቤሴሎም አባቱን፥ “ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት በኬብሮን አደርግ ዘንድ ልሂድ። እኔ አገልጋይህ በሶርያ ጌድሶር ሳለሁ፦ እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም ቢመልሰኝ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀርባለሁ ብዬ ስእለት ተስዬ ነበርና” አለው። ንጉሡም፥ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ተነሥቶም ወደ ኬብሮን ሄደ። አቤሴሎምም፥ “የመለከት ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፥ አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ” በሉ የሚሉ ጕበኞችን ወደ እስራኤል ነገድ ሁሉ ላከ። የተጠሩትም ሁለት መቶ ሰዎች ከአቤሴሎም ጋር ከኢየሩሳሌም ሄዱ፤ እነርሱም በየዋህነት ሄዱ፤ ነገሩንም ሁሉ ከቶ አያውቁም ነበር። አቤሴሎምም መሥዋዕት በሚሠዋበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ ወደ ነበረው ጌሎናዊው አኪጦፌል ወደ ከተማው ጊሎ ላከ። ሴራውም ጽኑ ሆነ፤ ከአቤሴሎምም ጋር ያለው ሕዝብ እጅግ በዛ። የእስራኤልም ሰዎች ልብ ወደ አቤሴሎም ተመልሶአል የሚል መልእክተኛ ወደ ዳዊት ሄደ። ዳዊትም ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ያሉትን አገልጋዮቹን ሁሉ፥ “ተነሡ እንሽሽ፤ ከአቤሴሎም እጅ የምንድንበት የለንምና፤ ፈጥኖ እንዳይዘን፥ ክፉም እንዳያመጣብን፤ ከተማዪቱንም በሰልፍ ስለት እንዳይመታ ፈጥናችሁ እንሂድ” አላቸው። የንጉሡም ብላቴኖች ንጉሡን፥ “እነሆ፥ ጌታችን ንጉሥ የመረጠውን ሁሉ እኛ አገልጋዮችህ እናደርጋለን” አሉት። ንጉሡና ከእርሱም በኋላ ቤተ ሰቡ ሁሉ በእግራቸው ወጡ፤ ንጉሡም ቁባቶቹ የነበሩ ዐሥሩን ሴቶች ቤቱን ይጠብቁ ዘንድ ተወ። ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ በእግር ወጡ፤ በሩቅም ቦታ ቆሙ። ብላቴኖቹም ሁሉ ተከተሉት፤ ኬልቲያውያንና ፌልታውያንም ሁሉ በምድረ በዳ በወይራ ሥር ቆሙ። ሕዝቡም ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሄዱ ነበር። ከእርሱ ጋር ያሉ ሰዎችም ሁሉ ስድስት መቶ ነበሩ። ከእርሱ ጋር ፌልታውያንና ኬልቲያውያን፥ በእግራቸው ከጌት የመጡ ስድስት መቶ ጌታውያንም ነበሩ። በንጉሡም ፊት ይሄዱ ነበር። ንጉሡም ጌታዊውን ኤቲን፥ “ከእኛ ጋር ለምን መጣህ? አንተ ከስፍራህ የመጣህ ስደተኛና እንግዳ ነህና ተመለስ፤ ከንጉሡም ጋር ተቀመጥ፤ የመጣኸው ትናንት ነው፤ ዛሬ ከእኛ ጋር ላዙርህን? እኔ ወደምሄድበት እሄዳለሁ፤ አንተ ግን ተመለስ፤ ወንድሞችህንም ከአንተ ጋር መልሳቸው፤ እግዚአብሔርም ምሕረቱንና እውነቱን ያድርግልህ” አለው። ኤቲም ለንጉሡ መልሶ፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! በጌታዬም በንጉሡ ሕይወት እምላለሁ! ጌታዬ ባለበት ስፍራ ሁሉ፥ በሞትም ቢሆን በሕይወትም፥ በዚያ ደግሞ እኔ አገልጋይህ እሆናለሁ” አለው። ንጉሡም ኤቲን፥ “ና ከእኔ ጋር ተሻገር” አለው፤ ጌታዊው ኤቲና ንጉሡም፥ አገልጋዮቹም፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝቡ ሁሉ ተሻገሩ። ሀገሪቱም ሁላ በታላቅ ድምፅ አለቀሰች። ሕዝቡም ሁሉ በቄድሮን ወንዝ ተሻገሩ፤ ንጉሡም ደግሞ የቄድሮንን ወንዝ ተሻገረ፤ ንጉሡና ሕዝቡም ሁሉ ወደ ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ተሻገሩ። እነሆም፥ ደግሞ፥ ሳዶቅና ከእርሱም ጋር ሌዋውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት አመጡ፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት አስቀመጡ፤ ሕዝቡም ሁሉ ከከተማዪቱ ፈጽሞ እስኪያልፉ ድረስ አብያታር ወጣ። ንጉሡም ሳዶቅን፥ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማ መልስ፤ በእግዚአብሔር ዐይን ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆንሁ፥ መልሶ እርሷንና ክብሯን ያሳየኛል፤ ነገር ግን አልወድድህም ቢለኝ፥ እነሆኝ በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን ያድርግብኝ” አለው። ንጉሡም ደግሞ ካህኑን ሳዶቅን፥ “እነሆ፥ አንተና ልጅህ አኪማኦስ፥ የአብያታርም ልጅ ዮናታን፥ ሁለቱ ልጆቻችሁ ከእናንተ ጋር በሰላም ወደ ከተማ ተመለሱ። እዩ፤ እኔም እነሆ፥ ከእናንተ ዘንድ ወሬ እስኪመጣልኝ ድረስ በምድረ በዳው ውስጥ በሜዳው እቈያለሁ” አለው። ሳዶቅና አብያታርም የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም መለሷት፤ በዚያም ተቀመጡ። ዳዊትም ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ወጣ፤ ሲወጣም ያለቅስ ነበር፤ ራሱንም ተከናንቦ ነበር፤ ያለጫማም ይሄድ ነበር፤ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተከናንበው ነበር፤ እያለቀሱም ይወጡ ነበር። አኪጦፌል ከአቤሴሎም ጋር በሴራ አንድ ነው ብለው ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም፥ “አቤቱ የአኪጦፌልን ምክር ለውጥ” አለ። ዳዊትም ለእግዚአብሔር ወደ ሰገደበት ወደ ተራራው ራስ መጣ፤ ወዳጁ ኵሲም ልብሱን ቀደደ፤ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ። ዳዊትም አለው፥ “ከእኔ ጋር ብትሻገር ሸክም ትሆንብኛለህ፤ ወደ ከተማ ግን ተመልሰህ ለአቤሴሎም፦ ወንድሞችህ፥ ንጉሡም መጡ። እነሆ፥ በኋላዬ ናቸው። ንጉሥ ሆይ፥ አገልጋይህ ነኝ፤ አስቀድሞ ለአባትህ አገልጋይ ነበርሁ፥ እንዲሁ አሁንም ለአንተ አገልጋይ ነኝ፥ ተወኝ ልኑር ብትለው የአኪጦፌልን ምክር ትለውጥልኛለህ። እነሆ፥ ካህናቱ ሳዶቅና አብያታርም በዚያ ከአንተ ጋር ናቸው። ከንጉሡ ቤትም የምትሰማውን ነገር ሁሉ ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ንገራቸው። እነሆ፥ የሳዶቅ ልጅ አኪማኦስና የአብያታር ልጅ ዮናታን፥ ልጆቻቸው በዚያ ከእነርሱ ጋር አሉ፤ የምትሰሙትን ሁሉ በእነርሱ እጅ ላኩልኝ።” የዳዊትም ወዳጅ ኩሲ ወደ ከተማ መጣ፤ አቤሴሎምም ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ።
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 15 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 15:1-37
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች