ከዚህ በኋላ አቤሴሎም አንድ ሠረገላና ፈረሶች ለራሱ አደራጀ፤ እንዲሁም ኀምሳ ጋሻ ጃግሬዎች እንዲኖሩት አደረገ፤ በማለዳ እየተነሣ በመሄድ ወደ ከተማይቱ ቅጽር በር በሚያስገባው መንገድ ዳር ይቆም ነበር፤ ንጉሡ ጉዳዩን እንዲያይለት የሚፈልግ ጠብ ክርክር ያለበት ሰው ሁሉ ወደዚያ ሲመጣ አቤሴሎም ጠርቶ ከወዴት እንደ መጣ ይጠይቀዋል፤ ሰውየው ከየትኛው ነገድ መሆኑን ከነገረው በኋላ፥ አቤሴሎም፥ “ተመልከት፤ ሕግ አንተን ይደግፍሃል፤ ነገር ግን በንጉሡ ተወክሎ ጉዳይህን በትክክል የሚያይልህ የለም” ይለዋል፤ ንግግሩንም በመቀጠል “እኔ ዳኛ ብሆን እንዴት በወደድሁ ነበር! ክርክር ወይም አቤቱታ ያለበት ሰው ወደ እኔ ሲመጣ እኔ ትክክለኛውን ፍርድ እሰጠው ነበር” ይለዋል። ሰውየው በፊቱ ለጥ ብሎ እጅ ለመንሣት በሚቀርብበት ጊዜ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ በማቀፍ ይስመዋል። አቤሴሎም ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ ለሚመጡት ሁሉ እንደዚህ ያደርግ ስለ ነበር የእነርሱን ልብ ለመማረክ ቻለ። ከአራት ዓመት በኋላ አቤሴሎም ንጉሥ ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ ሆይ! ለእግዚአብሔር የተሳልኩትን ስእለት ለመፈጸም ወደ ኬብሮን እንድሄድ ፍቀድልኝ! እኔ አገልጋይህ በሶርያ በምትገኘው በገሹር በኖርኩበት ጊዜ ‘ወደ ኢየሩሳሌም ብትመልሰኝ መሥዋዕት አቀርብልሃለሁ’ ብዬ ለእግዚአብሔር ስእለት ተስዬ ነበር።” ንጉሡም “በሰላም ሂድ!” አለው፤ ስለዚህም አቤሴሎም ወደ ኬብሮን ሄደ፤ “ነገር ግን ወደ እስራኤል ነገዶች ሁሉ መልእክተኞችን ልኮ የእምቢልታ ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ ድምፃችሁን ከፍ በማድረግ ‘አቤሴሎም የኬብሮን ንጉሥ ሆኗል!’ ብላችሁ ጩኹ” ብለው እንዲነግሩአቸው አደረገ። በአቤሴሎም ጋባዥነት ከእርሱ ጋር ከኢየሩሳሌም የሄዱ ሁለት መቶ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ተከትለውት የሄዱት ስለ ሤራው ምንም ነገር ሳያውቁ በቅንነት ነበር። አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ከንጉሥ ዳዊት አማካሪዎች አንዱ የሆነውን አኪጦፌል ተብሎ የሚጠራውን ሰው መልእክተኛ በመላክ ከጊሎ ከተማ አስጠራ፤ በንጉሡ ላይ የተጠነሰሰው ሤራ እየጠነከረ፥ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቊጥር እየጨመረ ሄደ። አንድ መልእክተኛ ዳዊትን “እስራኤላውያን ታማኝነታቸውን ለአቤሴሎም በመግለጥ ላይ ናቸው” አለው። ስለዚህም ዳዊት ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ለሚገኙት መኳንንቱ ሁሉ “ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ ከፈለግን በፍጥነት ከዚህ ሸሽተን እንውጣ! እንግዲህ ፍጠኑ! አለበለዚያ በፍጥነት መጥቶ ድል ይመታናል፤ በከተማይቱ ያገኘውንም ሁሉ ይገድላል!” አላቸው። እነርሱም “እሺ ንጉሥ ሆይ! አንተ ያልከውን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁዎች ነን” ሲሉ መለሱለት። ስለዚህ ንጉሡ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቁለት ዘንድ ካስቀራቸው ዐሥር ቊባቶች በቀር ቤተሰቡንና መኳንንቱን ሁሉ በማስከተል ሸሽቶ ሄደ። ንጉሡና ተከታዮቹ ሁሉ ከከተማይቱ ወጥተው በሚሄዱበት ጊዜ በከተማይቱ መጨረሻ ላይ በሚገኘው አንድ ቤት አጠገብ ቆሙ፤ ባለሟሎቹ ሁሉ በእርሱ በኩል አለፉ፤ የዳዊት ክብር ዘበኞች የነበሩት ከሪታውያንና ፈሊታውያን፥ እንዲሁም ከጋት የመጡ ስድስት መቶ ጌታውያን በንጉሡ ፊት አለፉ፤ ንጉሡም ኢታይ ተብሎ የሚጠራውን የጌት ሰው እንዲህ አለው፤ “ከእኛ ጋር ለምን ትሄዳለህ? ተመልሰህ ከአዲሱ ንጉሥ ጋር ቈይ፤ አንተ ከአገርህ ወጥተህ በመጻተኛነት እዚህ የምትኖር የውጪ አገር ሰው ነህ፤ በዚህ አገር የኖርከውም ለአጭር ጊዜ ነው፤ ታዲያ አንተ ከእኔ ጋር የምትንከራተተው ስለምንድን ነው? እኔ የት እንደምሄድ እንኳ አላውቅም፤ ስለዚህ የአገርህን ሰዎች ይዘህ ተመለስ፤ እግዚአብሔር ቸርነቱንና እውነተኛነቱን ይግለጥልህ።” ኢታይ ግን ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ጌታዬ በሚኖርበት ቦታ ሁሉ፥ በሞትም ሆነ በሕይወት እኔ አገልጋይህ በዚያ እንደምገኝ በእግዚአብሔር ስም እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ ሕይወት እምላለሁ።” ዳዊትም “መልካም ነው! እንግዲህ ጒዞህን ቀጥል!” አለው፤ ስለዚህም ኢታይ ከወታደሮቹ ሁሉና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጒዞውን ቀጠለ፤ የዳዊት ተከታዮች ወጥተው በሄዱ ጊዜ ሕዝቡ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ንጉሡ ከተከታዮቹ ጋር የቄድሮንን ወንዝ ተሻገረ፤ በአንድነትም ሆነው ወደ በረሓው አመሩ። ካህኑ ሳዶቅም እዚያው ነበር፤ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ሌዋውያን ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ የቃል ኪዳኑን ታቦት፥ ሕዝቡ ሁሉ ከተማውን ለቆ እስኪወጣ ድረስ በአብያታር አጠገብ አስቀመጡት። ከዚህ በኋላ ንጉሡ ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ከተማይቱ መልሰህ ውሰድ፤ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያገኘሁ እንደ ሆነ አንድ ቀን ታቦቱንና ማደሪያውን እንዳይ ይፈቅድልኝ ይሆናል፤ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ባላገኝ ግን በእኔ ላይ የወደደውን ያድርግ።” ንግግሩንም በመቀጠል ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “ተመልከት፤ ልጅህን አሒማዓጽንና የአብያታርንም ልጅ ዮናታንን ይዘህ ወደ ከተማይቱ በሰላም ሂድ፤ እኔም ከአንተ ወሬ እስከማገኝ ድረስ በበረሓው ውስጥ በሚገኘው በወንዙ መሸጋገሪያ ላይ እጠባበቃለሁ።” ስለዚህም ሳዶቅና አብያታር የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም መልሰው ወሰዱ፤ በዚያም ቈዩ። ዳዊትም ሐዘኑን በመግለጥ ጫማ ሳያደርግ ራሱን ተከናንቦ የደብረ ዘይትን አቀበት እያለቀሰ ወጣ፤ የተከተሉትም ሁሉ ደግሞ ራሳቸውን ተከናንበው ያለቅሱ ነበር። ዳዊት፥ አኪጦፌል ከአቤሴሎም ጋር በዐመፅ መተባበሩን በሰማ ጊዜ “እግዚአብሔር ሆይ! የአኪጦፌልን ምክር ወደ ከንቱነት እንድትለውጥበት እለምንሃለሁ!” ሲል ጸለየ። ዳዊት የማምለኪያ ስፍራ ወዳለበት ወደ ኮረብታው ጫፍ በደረሰ ጊዜ ታማኝ ጓደኛው የሆነው አርካዊው ሑሻይ ልብሱን ቀዶና በራሱ ላይ ትቢያ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ። ዳዊትም እንዲህ አለው፦ “አንተ እኔን ተከትለህ ብትሄድ ወደ ኋላ ትጐትተናለህ፤ አንተ እኔን ልትረዳኝ የምትችለው ግን ወደ ከተማይቱ ተመልሰህ አቤሴሎምን፥ አባትህን እንዳገለገልኩ አንተንም በታማኝነት አገለግላለሁ ብለህ ብትነግረው እንዲሁም አኪጦፌል የሚሰጠውን ምክር ሁሉ ብትቃወምልኝ ነው፤ ካህናቱ ሳዶቅና አብያታርም በዚያው ይገኛሉ፤ በቤተ መንግሥት የምትሰማውን ነገር ሁሉ ለእነርሱ ትነግራቸዋለህ፤ ከእነርሱም ጋር ልጆቻቸው አሒማዓጽና ዮናታን ይገኛሉ፤ የምታገኘውንም ወሬ ሁሉ በእነርሱ በኩል ልትልክብኝ ትችላለህ።” ስለዚህም የዳዊት ወዳጅ ሑሻይ ወደ ከተማይቱ ተመለሰ፤ አቤሴሎምም ወዲያውኑ እዚያ ደረሰ።
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15:1-37
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች