ከዚህ በኋላ አቤሴሎም ሠረገላና ፈረሶች እንዲሁም ፊት ፊቱ የሚሮጡ ዐምሳ ሰዎች ለራሱ አዘጋጀ። አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ሆነ ብሎ ይቆም ነበር። ማንኛውም ባለጕዳይ አቤቱታውን ለንጉሡ አቅርቦ ለማስወሰን በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ፣ አቤሴሎም ወደ እርሱ እየጠራ፣ “አንተ ከየትኛው ከተማ ነው የመጣኸው?” በማለት ይጠይቀዋል፤ ያም ሰው፣ “አገልጋይህ ከአንዱ የእስራኤል ነገዶች ነው” ብሎ ይመልስለታል። ከዚያም አቤሴሎም፣ “ተመልከት! ጕዳይህማ ትክክልና ተገቢም ነው፤ የትኛው የንጉሥ እንደራሴ ነው ታዲያ የሚያይልህ?” ይለዋል። ቀጠል አድርጎም፣ “ምነው ዳኛ ሆኜ በምድሪቱ ላይ በተሾምሁ አቤቱታ ወይም ክስ ያለበት ሁሉ ወደ እኔ እየመጣ ፍትሕ እንዲያገኝ አደርገው ነበር” ይል ነበር። እንዲሁም ማንኛውም ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ እጅ በሚነሣው ጊዜ፣ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር። አቤሴሎም ፍትሕ ለማግኘት ወደ ንጉሡ የሚመጣውን እስራኤላዊ ሁሉ የሚቀርበው በዚህ መንገድ ስለ ነበር፣ የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ። ከአራት ዓመት በኋላም አቤሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት ለማድረስ ወደ ኬብሮን እንድሄድ ፍቀድልኝ፤ እኔ አገልጋይህ በሶርያ ምድር በጌሹር ሳለሁ ‘እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም የመለሰኝ እንደ ሆነ፣ በኬብሮን ለእግዚአብሔር እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስያለሁ።” ንጉሡም፣ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ስለዚህ አቤሴሎም ወደ ኬብሮን ሄደ። ከዚያም አቤሴሎም፣ “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ፣ ‘አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ’ ” የሚሉ የምስጢር ሠራተኞችን በመላው የእስራኤል ነገዶች አሰማራ። ከኢየሩሳሌምም ሁለት መቶ ሰዎች አቤሴሎም ሄዱ፤ በእንግድነት ተጋብዘው በየዋህነት ከመሄዳቸው በቀር፣ ስለ ጕዳዩ የሚያውቁት አንዳችም ነገር አልነበረም። አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ የሆነው የጊሎን ሰው አኪጦፌል ከአገሩ ከጊሎ ወደ እርሱ እንዲመጣ ላከበት፤ ስለዚህ ሤራው ጥንካሬ አገኘ፤ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቍጥር እየጨመረ መጣ። መልእክተኛም መጥቶ፣ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋራ ሆኗል” ብሎ ለዳዊት ነገረው። ከዚያም ዳዊት በኢየሩሳሌም ላሉት ሹማምቱ ሁሉ፣ “ተነሡ እንሽሽ፤ አለዚያ አንዳችንም ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ አንችልም፤ አሁኑኑ ከዚህ መውጣት አለብን፤ ካልሆነ ገሥግሦ መጥቶ ከያዘን እኛን ያጠፋናል፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ይመታታል” አላቸው። የንጉሡ ሹማምትም፣ “ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ ለማድረግ እኛ አገልጋዮችህ ዝግጁ ነን” ብለው መለሱለት። ንጉሡ ከመላው ቤተ ሰቡ ጋራ ወጣ፤ ቤተ መንግሥቱንም እንዲጠብቁ ዐሥር ቁባቶች አስቀረ። ስለዚህ ንጉሡ መላውን ሕዝብ አስከትሎ ወጣ፤ ጥቂት ርቀው ከሄዱ በኋላም በአንዲት ቦታ ቆሙ። ሰዎቹ ሁሉ፣ ከሊታውያን፣ ፈሊታውያን እንዲሁም ከጋት ዐብረውት የመጡትን ስድስት መቶ ጋታውያንን ሁሉ ጨምሮ ተሰልፈው በንጉሡ ፊት ዐለፉ። ንጉሡም ጋታዊውን ኢታይን እንዲህ አለው፤ “ከእኛ ጋራ የመጣኸው ለምንድን ነው? ተመለስና ከንጉሡ ከአቤሴሎም ጋራ ተቀመጥ፤ አንተ ለራስህ ከአገርህ ተወስደህ የመጣህ እንግዳ ነህ፤ የመጣኸውም ገና ትናንት ነው፤ ታዲያ የት እንደምሄድ የማላውቅ ሰው እንዴት ዛሬ ከእኛ ጋራ እንድትንከራተት ላድርግ? በል አሁንም ሰዎችህን ይዘህ ተመለስ፤ በጎነትና ታማኝነትም ከአንተ ጋራ ይሁን” አለው። ኢታይ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ እምላለሁ፤ ሕይወትም ይሁን ሞት በየትም ቦታ ንጉሥ ጌታዬ የሚሆነውን ሁሉ አገልጋይህም እንደዚያው ይሆናል” ብሎ መለሰለት። ዳዊትም ኢታይን፣ “በል እንግዲያው ቅደምና ሂድ” አለው። ስለዚህ ጋታዊው ኢታይን ሰዎቹን ሁሉና ዐብረውት የነበሩትን ቤተ ሰቦቹን ይዞ ሄደ። ሕዝቡ ሁሉ በሚያልፍበትም ጊዜ ባላገሩ በሙሉ እየጮኸ አለቀሰ፤ ንጉሡም የቄድሮንን ሸለቆ ተሻገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሻግሮ ወደ ምድረ በዳው ተጓዘ። ሳዶቅም በዚያ ነበር፤ ዐብረውት የነበሩትም ሌዋውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ነበር። እነርሱም የእግዚአብሔርን ታቦት ዐሳረፉ፤ አብያታርም ሕዝቡ በሙሉ ከከተማዪቱ ለቅቆ እስኪወጣ ድረስ መሥዋዕት አቀረበ። ከዚያም ንጉሡ ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማዪቱ ይዘህ ተመለስ፤ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፣ እርሱ እኔንም መልሶ ታቦቱንና ማደሪያውን እንደ ገና ለማየት ያበቃኛል፤ ነገር ግን እርሱ፣ ‘ባንተ አልተደሰትሁም’ የሚል ከሆነ፣ መልካም መስሎ የታየውን ነገር ያድርግብኝ፤ እኔም ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።” እንዲሁም ንጉሡ ካህኑን ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ ነቢይ አይደለህምን? እንግዲህ አንተም ልጅህን አኪማአስን፣ የአብያታርን ልጅ ዮናታንን ይዘህ በሰላም ወደ ከተማዪቱ ተመለስ። አንተና አብያታር ሁለቱን ልጆቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ። እኔም ከአንተ ዘንድ ወሬ እስካገኝ ድረስ በምድረ በዳው በሚገኘው በወንዙ መሻገሪያ እቈያለሁ” ስለዚህ ሳዶቅና አብያታር የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም በመመለስ እዚያው ቈዩ። ዳዊት ግን እያለቀሰ የደብረ ዘይትን ተራራ ሽቅብ ወጣ፤ ራሱን ተከናንቦ፣ ባዶ እግሩን ነበር፤ ዐብሮት ያለውም ሕዝብ ሁሉ እንደዚሁ ራሱን ተከናንቦ እያለቀሰ ሽቅብ ይወጣ ነበር። በዚህ ጊዜ፣ “ከአቤሴሎም ጋራ ካሤሩት መካከል አንዱ አኪጦፌል ነው” ብለው ለዳዊት ነገሩት። ስለዚህ ዳዊት፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህን የአኪጦፌልን ምክር ወደ ከንቱነት ለውጠው” ብሎ ጸለየ። ዳዊትም ሕዝቡ እግዚአብሔርን ወደሚያመልክበት ወደ ተራራው ጫፍ ሲደርስ፣ አርካዊው ኩሲ ልብሱን ቀድዶ ትቢያ በራሱ ላይ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ። ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለው፤ “ዐብረኸኝ ብትሄድ ሸክም ትሆንብኛለህ፤ ነገር ግን ወደ ከተማዪቱ ተመልሰህ አቤሴሎምን፣ ‘ንጉሥ ሆይ፤ አገልጋይህ እሆናለሁ፤ ቀድሞ የአባትህ አገልጋይ እንደ ነበርሁ ሁሉ፣ ዛሬም አንተን አገለግልሃለሁ’ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር በማፍረስ ትረዳኛለህ። ካህናቱ ሳዶቅና አብያታር እዚያው ከአንተው ጋራ ይሆኑ የለምን? ከንጉሡ ቤትም የምትሰማትን ሁሉ ንገራቸው። የሳዶቅ ልጅ አኪማአስና የአብያታር ልጅ ዮናታን፣ ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው እዚያው ዐብረዋቸው ይገኛሉ። የምትሰማትን ሁሉ በእነርሱ ላክልኝ።” ስለዚህ የዳዊት ወዳጅ ኩሲ ልክ አቤሴሎም ኢየሩሳሌም በገባበት ሰዓት እዚያው ከተማ ደረሰ።
2 ሳሙኤል 15 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ሳሙኤል 15
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ሳሙኤል 15:1-37
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች