2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15:1-37

2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15:1-37 መቅካእኤ

ከዚህ በኋላ አቤሴሎም ሠረገላና ፈረሶች፥ ፊት ፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ። አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ይቆም ነበር። ማናቸውም ባለ ጉዳይ አቤቱታውን ለንጉሡ አቅርቦ ለማስወሰን በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ፥ አቤሴሎም ወደ እርሱ እየጠራ፥ “አንተ ከየትኛው ከተማ ነው የመጣኸው?” በማለት ይጠይቀዋል፤ ያም ሰው፥ “አገልጋይህ ከእስራኤል ነገዶች ከአንዱ ነው” ብሎ ይመልስለታል። ከዚያም አቤሴሎም፥ “ተመልከት! ጉዳይህማ ትክክልና ተገቢም ነው፤ ነገር ግን ከንጉሥ ተወክሎ የሚሰማህ የለም” ይለው ነበር። ከዚህም ሌላ አቤሴሎም፥ “በምድሪቱ ላይ ዳኛ እኔ በሆንኩ ኖሮ! አቤቱታ ወይም ክስ ያለበት ሁሉ ወደ እኔ ሲመጣ፥ ፍትሕ እንዲያገኝ ባደረግሁ ነበር” ይል ነበር። እንዲሁም ማናቸውም ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ እጅ በሚነሣው ጊዜ፥ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር። አቤሴሎም ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ ለሚመጣ እስራኤላዊ ሁሉ አቀራረቡ እንዲህ ነበር፤ ስለዚህ አቤሴሎም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ። ከአራት ዓመት በኋላም አቤሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “በኬብሮን ለጌታ የተሳልሁትን ስእለት ለማድረስ እንድሄድ ፍቀድልኝ፤ እኔ አገልጋይህ በሶርያ ምድር በገሹር ሳለሁ ‘ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም የመለሰኝ እንደሆነ፥ በኬብሮን ለጌታ እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስያለሁ።” ንጉሡም፥ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ተነሥቶም ወደ ኬብሮን ሄደ። ነገር ግን አቤሴሎም፥ በመላው የእስራኤል ነገዶች መሀል “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ፥ ‘አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ’ ” የሚሉ የምስጢር መልእክተኞችን ላከ። ከአቤሴሎም ጋር ከኢየሩሳሌምም ሁለት መቶ ሰዎች አብረውት ሄደው ነበር፤ በእንግድነት ተጋብዘው በቅንነት ከመሄዳቸው በስተቀር፥ ስለጉዳዩ ምንም ነገር አያውቁም ነበር። አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ የሆነው ጊሎአዊው አኪጦፌል ከአገሩ ከጊሎ ወደ እርሱ እንዲመጣ ላከበት፤ ስለዚህ ሤራው ጥንካሬ አገኘ፤ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቍጥር እየበዛ ሄደ። መልእክተኛም መጥቶ፥ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኖአል” ብሎ ለዳዊት ነገረው። ከዚያም ዳዊት በኢየሩሳሌም ላሉት አገልጋዮቹ ሁሉ፥ “ተነሡ እንሽሽ፤ ያለበለዚያ ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ አንችልም፤ ፈጥኖ እንዳይዘን፥ ክፉም እንዳያመጣብን፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ስለት እንዳይመታ ፈጥናችሁ እንሂድ” አላቸው። የንጉሡ አገልጋዮቹም፥ “ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ ለማድረግ እኛ አገልጋዮችህ ዝግጁ ነን” ብለው መለሱለት። ስለዚህ ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ ካስቀራቸው ዐሥር ዕቁባቶች በቀር፥ ንጉሡም እርሱንም ተከትለው መላው ቤተሰቡ ሸሹ፤ ንጉሡም እርሱንም ተከትለው ሕዝቡ ሁሉ ወጣ፤ ርቀው ከሄዱ በኋላም በአንዲት ቤት ቆሙ። አገልጋዮቹ ሁሉ፥ ከሊታውያን፥ ፈሊታውያን እንዲሁም ከጌት አብረውት የመጡትን ስድስት መቶ ጌታውያን ሁሉን ጨምሮ ተሰልፈው በንጉሡ ፊት ዐለፉ። ንጉሡም የጌታዊውን ሰው ኢታይን እንዲህ አለው፤ “አንተም ከእኛ ጋር አብረህ የመጣኸው ለምንድን ነው? ተመለስና ከንጉሥ አቤሴሎም ጋር ተቀመጥ፤ አንተ እኮ ከስፍራህ በግዞት የመጣህ መጻተኛ ነህ፤ የመጣኸውም ገና ትናንት ነው፤ ታዲያ የት እንደምሄድ የማላውቅ ሰው እንዴት ዛሬ ከእኛ ጋር እንድትንከራተት ላድርግ? ተነሥ ሰዎችህን ይዘህ ተመለስ፤ ታማኝነትና እውነተኛነትም ከአንተ ጋር ይሁን” አለው። ኢታይ ግን፥ “በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ! እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ እምላለሁ፤ ሕይወትም ይሁን ሞት በየትም ቦታ ንጉሥ ጌታዬ የሚሆነውን ሁሉ አገልጋይህም እንደዚያው እሆናለሁ” ብሎ መለሰለት። ዳዊትም ኢታይን፥ “እንግዲያውስ ቅደምና ሂድ” አለው። ስለዚህ ጌታዊው ኢታይ ሰዎቹን ሁሉና አብረውት የነበሩትን ቤተሰቦቹን ይዞ ሄደ። ሕዝቡ ሁሉ በሚያልፍበትም ጊዜ ባላገሩ በሙሉ እየጮኸ አለቀሰ፤ ንጉሡም የቄድሮንን ወንዝ ተሻገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሻግሮ ወደ ምድረ በዳው አመሩ። ሳዶቅም በዚያ ነበር፤ አብረውት የነበሩትም ሌዋውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው መጡ፥ የእግዚአብሔርንም ታቦት፥ ሕዝቡ በሙሉ ከከተማዪቱ ለቆ እስኪ ወጣ ድረስ፥ አብያታር አጠገብ አስቀመጡ። ከዚያም ንጉሡ ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማይቱ ይዘህ ተመለስ፤ በጌታ ፊት ሞገስ ያገኝሁ እንደሆነ፥ እርሱ እኔንም መልሶ ታቦቱንና ማደሪያውን ያሳየኛል፤ ነገር ግን እርሱ፥ ‘ባንተ አልተደሰትሁም’ የሚል ከሆነ፥ እነሆኝ፥ መልካም መስሎ የታየውን ነገር ያድርግብኝ።” እንዲሁም ንጉሡ ካህኑን ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ ነቢይ አይደለህምን? ይሄውልህ አንተም ልጅህን አሒማአስን፥ የአብያታርን ልጅ ዮናታንን ይዘህ በሰላም ወደ ከተማዪቱ ተመለስ። አንተና አብያታር ሁለቱን ልጆቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ። እኔም ከአንተ ዘንድ ወሬ እስካገኝ ድረስ በምድረ በዳው በሚገኘው በወንዙ መሻገሪያ እቆያለሁ” ስለዚህ ሳዶቅና አብያታር የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም መለሱት፥ በዚያም ተቀመጡ። ዳዊት ግን እያለቀሰ፥ ራሱን ተከናንቦ፥ ባዶ እግሩን የደብረ ዘይትን ተራራ ወጣ፤ አብሮት ያለውም ሕዝብ ሁሉ እንደዚሁ ራሱን ተከናንቦ እያለቀሰ ተራራውን ይወጣ ነበር። በዚህ ጊዜ፥ “ከአቤሴሎም ጋር ካሤሩት መካከል አንዱ አኪጦፌል ነው” ብለው ለዳዊት ነገሩት። ዳዊትም፥ “ጌታ ሆይ! እባክህን የአኪጦፌልን ምክር ወደ ከንቱነት ለውጠው” ሲል ጸለየ። ዳዊት ሕዝቡ እግዚአብሔርን ወደሚያመልክበት ወደ ተራራው ጫፍ በደረሰ ጊዜ፥ አርካዊው ሑሻይ ልብሱን ቀዶ ትቢያ በራሱ ላይ ነስንሶ ሊያገኘው መጣ። ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለው፤ “አብረኸኝ ብትሄድ ሸክም ትሆንብኛለህ፤ ነገር ግን ወደ ከተማዪቱ ተመልሰህ አቤሴሎምን፥ ‘ንጉሥ ሆይ፤ አገልጋይህ እሆናለሁ፤ ቀድሞ የአባትህ አገልጋይ እንደ ነበርሁ ሁሉ፥ ዛሬም አንተን አገለግልሃለሁ’ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር በማፍረስ ትረዳኛለህ። ካህናቱ ሳዶቅና አብያታር በዚያ ከአንተው ጋር አይደሉምን? ስለዚህ ከቤተ መንግሥቱ የምትሰማትን ሁሉ ለሳዶቅና ለአብያታር ንገራቸው። እነሆ፥ የሳዶቅ ልጅ አሒማአስና የአብያታር ልጅ ዮናታን፥ ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው እዚያው አብረዋቸው ይገኛሉ። የምትሰማትን ሁሉ በእነርሱ ላክልኝ።” ስለዚህ የዳዊት ወዳጅ ሑሻይ ልክ አቤሴሎም ኢየሩሳሌም በገባበት ሰዓት ወደ ከተማዋ ደረሰ።