2 ቆሮንቶስ 1:3-10
2 ቆሮንቶስ 1:3-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የምሕረት አባት፥ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን። እግዚአብሔር በአጽናናን በዚያ መጽናናት በመከራ ያሉትን ሁሉ ማጽናናት እንችል ዘንድ ከመከራችን ሁሉ ያጽናናን እርሱ ይመስገን። የክርስቶስ መከራ በእኛ ላይ እንደ በዛ መጠን እንዲሁ መጽናናታችንም በክርስቶስ ይበዛልና። መከራ ብንቀበልም እናንተ እንድትድኑና እንድትጽናኑ ነው፤ ብንጽናናም እኛ የተቀበልነውን ያን መከራ በመታገሥ ስለሚደረግ መጽናናታችሁ ነው። ስለ እናንተ ያለን ተስፋም የጸና ነው፤ መከራችንን እንደ ተካፈላችሁ መጠን፥ እንዲሁ በመጽናናታችንም እንደምትተባበሩ እናውቃለን። ወንድሞቻችን ሆይ፥ በእስያ መከራ እንደ ተቀበልን ልታውቁ እወዳለሁ፤ ለሕይወታችን ተስፋ እስክንቈርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ እጅግ መከራ ጸንቶብን ነበርና። ሙታንን በሚያስነሣቸው በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን በውስጣችን ለመሞት ቈርጠን ነበር። እርሱም እንዲህ ካለ ሞት አዳነን፤ ያድነንማል፤ አሁንም እንደሚያድነን እርሱን እንታመናለን።
2 ቆሮንቶስ 1:3-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እኛ ራሳችን ከእግዚአብሔር በተቀበልነው መጽናናት፣ በመከራ ያሉትን ማጽናናት እንድንችል፣ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል። የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ የመብዛቱን ያህል መጽናናታችንም በክርስቶስ በኩል ይበዛልናል። መከራ ብንቀበል ስለ እናንተ መጽናናትና መዳን ነው። ብንጽናናም እኛ የተቀበልነውን መከራ በመቀበል በትዕግሥት እንድትጸኑ ስለ እናንተ መጽናናት ነው። ስለ እናንተ ያለን ተስፋ ጽኑ ነው፤ ምክንያቱም በመከራችን እንደ ተካፈላችሁ ሁሉ በመጽናናታችንም እንደምትካፈሉ እናውቃለን። ወንድሞች ሆይ፤ በእስያ ስለ ደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንወድዳለን፤ በሕይወት ለመኖር እንኳ ተስፋ እስከምንቈርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ የሆነ ጽኑ መከራ ደርሶብን ነበር። በርግጥም የሞት ፍርድ እንደ ተፈረደብን ይሰማን ነበር፤ ይህም የሆነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንድንታመን እንጂ፣ በራሳችን እንዳንታመን ነው። እርሱ እንዲህ ካለው የሞት አደጋ አድኖናል፤ ያድነናልም፤ ወደ ፊትም ደግሞ እንደሚያድነን ተስፋችንን በእርሱ ላይ ጥለናል።
2 ቆሮንቶስ 1:3-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፥ ስለዚህም እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን። የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፥ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና። ዳሩ ግን መከራ ብንቀበል፥ ስለ መጽናናታችሁና ስለ መዳናችሁ ነው፤ ብንጽናናም፥ እኛ ደግሞ የምንሣቀይበት በዚያ ሥቃይ በመጽናት ስለሚደረግ ስለ መጽናናታችሁ ነው። ተስፋችንም ስለ እናንተ ጽኑ ነው፤ ሥቃያችንን እንደ ተካፈላችሁ እንዲሁም መጽናናታችንን ደግሞ እንድትካፈሉ እናውቃለንና። በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ አዎን፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር። እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፥ ያድነንማል፤ እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን፥ በብዙ ሰዎች በኩል ስለ ተሰጠን ስለ ጸጋ ስጦታ ብዙዎች ስለ እኛ ያመሰግኑ ዘንድ፥ ወደ ፊት ደግሞ እንዲያድን በእርሱ ተስፋ አድርገናል።
2 ቆሮንቶስ 1:3-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ለምሕረት አባትና መጽናናትን ሁሉ ለሚሰጥ እንዲሁም ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አባት ለእግዚአብሔር፥ ምስጋና ይሁን። እኛ ከእግዚአብሔር በምናገኘው መጽናናት በመከራ ላይ ያሉትን ሁሉ ማጽናናት እንድንችል እግዚአብሔር እኛን በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል። የክርስቶስን መከራ በብዛት እንደ መካፈላችን መጠን እንዲሁም በክርስቶስ መጽናናትን በብዛት እናገኛለን። እኛ መከራ ስንቀበል እናንተ መጽናናትንና መዳንን ታገኛላችሁ፤ እኛ ስንጽናና ደግሞ እናንተም እኛ የምንቀበለውን ዐይነት መከራ በትዕግሥት ተቀብላችሁ ትጽናናላችሁ፤ መከራችንን በምትካፈሉበት መጠን መጽናናታችንንም እንደምትካፈሉ ስለምናውቅ በእናንተ ላይ ያለን ተስፋ ጽኑ ነው። ወንድሞች ሆይ! በእስያ ክፍለ ሀገር በነበርንበት ጊዜ የደረሰብንን መከራ እንድታውቁ እንወዳለን፤ ይህም የደረሰብን መከራ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ወድቆብን ስለ ነበር በሕይወት ለመኖር የነበረን ተስፋ እንኳ ተቋርጦ ነበር። እንዲያውም ሞት እንደ ተፈረደብን ያኽል ተሰምቶን ነበር፤ ይህም ሁሉ የደረሰብን፥ የምንተማመነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን ኀይል አለመሆኑን እንድንገነዘብ ነው። ስለዚህ እርሱ ለሞት ከሚያደርስ አደጋ አድኖናል፤ ያድነናልም፤ ደግሞም እንደሚያድነን ተስፋችን በእርሱ ነው።
2 ቆሮንቶስ 1:3-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይባረክ። እኛ በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ያሉትን ሁሉ ማጽናናት እንድንችል፥ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል። የክርስቶስ ሥቃይ ስለ እኛ እንደ መብዛቱ፥ መጽናናታችንም በክርስቶስ በኩል ይበዛልናል። መከራ ብንቀበል፥ ስለ መጽናናታችሁና ስለ መዳናችሁ ነው፤ ብንጽናናም፥ እኛ የተቀበልነውን መከራ በመቀበል እናንተም በትዕግሥት መታገስ በመቻላችሁ፥ ስለ መጽናናታችሁ ነው። ሥቃያችንን እንደ ተካፈላችሁ እንዲሁም መጽናናታችንን ደግሞ እንደምትካፈሉ እናውቃለንና፥ ተስፋችን ስለ እናንተ ጽኑ ነው። ወንድሞች ሆይ! በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን ብታውቁት እንወዳለን፤ በሕይወታችን ተስፋ እስክመቁረጥ የሚያደርስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር። በእርግጥም፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ የሞት ፍርድ እንደተላለፈብን በውስጣችን ተሰምቶን ነበር። እርሱ እንዲህ ካለው የሞት አደጋ አድኖናል፤ ያድነናልም፤ ወደፊትም ደግሞ እንደሚያድነን ተስፋችንን በእርሱ ላይ ጥለናል።