2 ቆሮንቶስ 1
1
1በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፣ ከወንድማችንም ከጢሞቴዎስ፤
በቆሮንቶስ ላለችው ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በመላው አካይያ ለሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ፤
2ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
የመጽናናት አምላክ
3የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። 4እኛ ራሳችን ከእግዚአብሔር በተቀበልነው መጽናናት፣ በመከራ ያሉትን ማጽናናት እንድንችል፣ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል። 5የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ የመብዛቱን ያህል መጽናናታችንም በክርስቶስ በኩል ይበዛልናል። 6መከራ ብንቀበል ስለ እናንተ መጽናናትና መዳን ነው። ብንጽናናም እኛ የተቀበልነውን መከራ በመቀበል በትዕግሥት እንድትጸኑ ስለ እናንተ መጽናናት ነው። 7ስለ እናንተ ያለን ተስፋ ጽኑ ነው፤ ምክንያቱም በመከራችን እንደ ተካፈላችሁ ሁሉ በመጽናናታችንም እንደምትካፈሉ እናውቃለን።
8ወንድሞች ሆይ፤ በእስያ ስለ ደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንወድዳለን፤ በሕይወት ለመኖር እንኳ ተስፋ እስከምንቈርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ የሆነ ጽኑ መከራ ደርሶብን ነበር። 9በርግጥም የሞት ፍርድ እንደ ተፈረደብን ይሰማን ነበር፤ ይህም የሆነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንድንታመን እንጂ፣ በራሳችን እንዳንታመን ነው። 10እርሱ እንዲህ ካለው የሞት አደጋ አድኖናል፤ ያድነናልም፤ ወደ ፊትም ደግሞ እንደሚያድነን ተስፋችንን በእርሱ ላይ ጥለናል። 11እናንተም በጸሎታችሁ ደግፉን፤ በብዙዎች ጸሎት ስለ ተሰጠን ስጦታ ብዙ ሰዎች ስለ እኛ#1፥11 ብዙ ቅጆች እናንተ ይላሉ። ምስጋና ያቀርባሉ።
ጳውሎስ ዕቅዱን ለወጠ
12እንግዲህ ትምክሕታችን ይህ ነው፤ በዚህ ዓለም በተለይም ከእናንተ ጋር ባለን ግንኙነት፣ ከእግዚአብሔር በሆነ ቅድስናና ቅንነት እንደ ኖርን ኅሊናችን ይመሰክራል፤ ይህም በሰው ጥበብ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ጸጋ ነው። 13ልታነብቡት ወይም ልትረዱት የማትችሉትን ነገር አንጽፍላችሁም፤ ሁሉንም እንደምትረዱ ተስፋ አደርጋለሁ። 14እናንተ በእኛ እንደምትመኩ ሁሉ እኛም በእናንተ እንደምንመካ አሁን የተረዳችሁን በከፊል ቢሆንም፣ በጌታ ኢየሱስ ቀን ሁሉን ትረዳላችሁ።
15በዚህ ርግጠኛ ስለ ነበርሁ በዕጥፍ እንድትጠቀሙ፣ በመጀመሪያ ልጐበኛችሁ ዐቅጄ ነበር። 16ወደ መቄዶንያ ስሄድ እግረ መንገዴን ልጐበኛችሁና ከመቄዶንያም በእናንተ በኩል ተመልሼ ወደ ይሁዳ ስሄድ በጕዞዬ እንድትረዱኝ ዐቅጄ ነበር። 17ይህን ሳቅድ በሚገባ ሳላስብ ያደረግሁት ይመስላችኋልን? ወይስ በዓለማዊ ልማድ አንዴ፣ “አዎን፣ አዎን” ወዲያው ደግሞ፣ “አይደለም፣ አይደለም” የምል ይመስላችኋልን?
18እግዚአብሔር ታማኝ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ለእናንተ የምንናገረው ቃላችን፣ “አዎን” እና “አይደለም” ሊሆን አይችልም፤ 19ምክንያቱም እኔም ሆንሁ ሲላስና#1፥19 ግሪኩ ሲልዋኑስ ይላል። ጢሞቴዎስ፣ እኛ የሰበክንላችሁ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ “አዎን” እና “አይደለም” አልነበረም፤ ነገር ግን በእርሱ ዘወትር፣ “አዎን” ነው። 20በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ “አዎን” የሚሆኑት በእርሱ ነውና፤ እኛም በእርሱ አማካይነት ለእግዚአብሔር ክብር፣ “አሜን” የምንለው በዚህ ምክንያት ነው። 21እንግዲህ፣ እኛንም እናንተንም በክርስቶስ ጸንተን እንድንቆም የሚያደርገን እግዚአብሔር ነው፤ የቀባንም እርሱ ነው፤ 22የእርሱ ለመሆናችን ማኅተሙን ያተመብን ደግሞም ወደ ፊት ለምናገኘው ነገር የመንፈሱን ዋስትና በልባችን ያኖረ እርሱ ነው።
23ወደ ቆሮንቶስ ተመልሼ ያልመጣሁት እንዳላሳዝናችሁ ብዬ ነው፤ ይህ እውነት ካልሆነ እግዚአብሔር ይመስክርብኝ። 24ጸንታችሁ የምትቆሙት በእምነት ስለሆነ፣ ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ጋር እንሠራለን እንጂ በእምነታችሁ ላይ ለመሠልጠን አይደለም።
Currently Selected:
2 ቆሮንቶስ 1: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.