የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1

1
1በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፥ #ሐ.ሥ. 18፥1።
በቆሮንቶስ ለምትገኘው የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንና እንዲሁም በመላው አካይያ ለሚገኙ ሕዝበ ክርስቲያን ሁሉ፥
2ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
ጳውሎስ ለእግዚአብሔር ያቀረበው ምስጋና
3ለምሕረት አባትና መጽናናትን ሁሉ ለሚሰጥ እንዲሁም ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አባት ለእግዚአብሔር፥ ምስጋና ይሁን። 4እኛ ከእግዚአብሔር በምናገኘው መጽናናት በመከራ ላይ ያሉትን ሁሉ ማጽናናት እንድንችል እግዚአብሔር እኛን በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል። 5የክርስቶስን መከራ በብዛት እንደ መካፈላችን መጠን እንዲሁም በክርስቶስ መጽናናትን በብዛት እናገኛለን። 6እኛ መከራ ስንቀበል እናንተ መጽናናትንና መዳንን ታገኛላችሁ፤ እኛ ስንጽናና ደግሞ እናንተም እኛ የምንቀበለውን ዐይነት መከራ በትዕግሥት ተቀብላችሁ ትጽናናላችሁ፤ 7መከራችንን በምትካፈሉበት መጠን መጽናናታችንንም እንደምትካፈሉ ስለምናውቅ በእናንተ ላይ ያለን ተስፋ ጽኑ ነው።
8ወንድሞች ሆይ! በእስያ ክፍለ ሀገር በነበርንበት ጊዜ የደረሰብንን መከራ እንድታውቁ እንወዳለን፤ ይህም የደረሰብን መከራ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ወድቆብን ስለ ነበር በሕይወት ለመኖር የነበረን ተስፋ እንኳ ተቋርጦ ነበር። #1ቆሮ. 15፥3። 9እንዲያውም ሞት እንደ ተፈረደብን ያኽል ተሰምቶን ነበር፤ ይህም ሁሉ የደረሰብን፥ የምንተማመነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን ኀይል አለመሆኑን እንድንገነዘብ ነው። 10ስለዚህ እርሱ ለሞት ከሚያደርስ አደጋ አድኖናል፤ ያድነናልም፤ ደግሞም እንደሚያድነን ተስፋችን በእርሱ ነው። 11እናንተም እኛን በጸሎት ልትረዱን ይገባል፤ በብዙ ጸሎት እኛ የእግዚአብሔርን ርዳታ ስናገኝ ብዙ ሰዎች ደግሞ በእኛ ምክንያት እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ።
የጳውሎስ ጒብኝት ዕቅድ መለወጥ
12የምንመካበት ነገር ይህ ነው፤ ይህም እውነት መሆኑን ኅሊናችን ይመሰክርልናል፤ ከሌሎች ሰዎችና በተለይም ከእናንተ ጋር የነበረን ግንኙነት ከእግዚአብሔር ባገኘነው ቅድስናና ቅንነት የተመሠረተ ነው፤ ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ጸጋ ነበር እንጂ በሰው ጥበብ አልነበረም። 13አንብባችሁ ማስተዋል የምትችሉትን ነገር ካልሆነ ሌላ ምንም አንጽፍላችሁም፤ በሙሉ ማስተዋል እንደምትችሉ ተስፋ አደርጋለሁ፤ 14አሁን ስለ እኛ የምታውቁት በከፊል ነው፤ በኋላ ግን በሙላት እንደምታስተውሉት ተስፋ አደርጋለሁ፤ በዚህም ምክንያት ጌታ ኢየሱስ በሚመጣበት ቀን እኛ በእናንተ እንደምንመካ እናንተም በእኛ ትመካላችሁ።
15በዚህ ነገር እርግጠኛ ስለ ነበርኩ ሁለት ጊዜ እንድትጠቀሙ ብዬ እናንተን በመጀመሪያ ለመጐብኘት ዐቅጄ ነበር፤ 16ልጐበኛችሁ ያቀድኩትም ወደ መቄዶንያ ሳልፍና ከዚያም በምመለስበት ጊዜ ነበር፤ በዚህም ሁኔታ ወደ ይሁዳ ምድር በማደርገው ጒዞዬ ትረዱኛላችሁ ብዬ አስቤ ነበር። #ሐ.ሥ. 19፥21። 17ይህን ባቀድኩ ጊዜ የማደርገውን የማላውቅ ወላዋይ የሆንኩ ይመስላችኋል? ወይስ ይህን በማቀዴ በአንድ ጊዜ “አዎንና አይደለም” እያልኩ በማወላወል በሰው አስተሳሰብ ያደረግኹት ይመስላችኋልን? 18እግዚአብሔር ታማኝ ስለ ሆነ እኛም የምንነግራችሁ “አዎን ወይም አይደለም” የሚል የማወላወል ቃል አይደለም። 19እኔና ሲላስ፥ ጢሞቴዎስም የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን የሰበክንላችሁ ሁልጊዜ “አዎን” በሚል ቃል ብቻ እንጂ፥ “አዎን ወይም አይደለም” በሚል አወላዋይ ቃል አልነበረም። #ሐ.ሥ. 18፥5። 20እግዚአብሔር የሰጠን ተስፋ ሁሉ “አዎን” የሚሆነው በክርስቶስ ነው፤ ስለዚህ ነው ለእግዚአብሔር ክብር በክርስቶስ “አሜን” የምንለው። 21እኛን ከእናንተ ጋር በክርስቶስ እንድንጸና ያደረገን እግዚአብሔር ነው፤ ለሥራ የለየንም እርሱ ነው፤ 22የእርሱ ለመሆናችን ማስረጃ የሚሆን ማኅተሙን በእኛ ላይ ያደረገና ወደ ፊት ለእኛ ስለሚሰጠን ሀብት በልባችን መንፈስ ቅዱስን እንደ ዋስትና አድርጎ የሰጠን እርሱ ነው።
23እኔ ወደ ቆሮንቶስ ተመልሼ ያልመጣሁበት ምክንያት እናንተን እንዳላሳዝናችሁ ለእናንተ በመራራት ነው፤ ለዚሁም እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፤ 24እናንተ በእምነታችሁ የጸናችሁ ስለ ሆናችሁ እናንተን ደስ እንዲላችሁ አብረናችሁ እንሠራለን እንጂ በእምነታችሁስ አናዛችሁም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ