የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1:3-11

2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1:3-11 አማ54

የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፥ ስለዚህም እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን። የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፥ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና። ዳሩ ግን መከራ ብንቀበል፥ ስለ መጽናናታችሁና ስለ መዳናችሁ ነው፤ ብንጽናናም፥ እኛ ደግሞ የምንሣቀይበት በዚያ ሥቃይ በመጽናት ስለሚደረግ ስለ መጽናናታችሁ ነው። ተስፋችንም ስለ እናንተ ጽኑ ነው፤ ሥቃያችንን እንደ ተካፈላችሁ እንዲሁም መጽናናታችንን ደግሞ እንድትካፈሉ እናውቃለንና። በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ አዎን፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር። እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፥ ያድነንማል፤ እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን፥ በብዙ ሰዎች በኩል ስለ ተሰጠን ስለ ጸጋ ስጦታ ብዙዎች ስለ እኛ ያመሰግኑ ዘንድ፥ ወደ ፊት ደግሞ እንዲያድን በእርሱ ተስፋ አድርገናል።