2 ዜና መዋዕል 34:8-28
2 ዜና መዋዕል 34:8-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በነገሠም በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ምድሪቱንና የእግዚአብሔርን ቤት ካነጻ በኋላ፥ የሴልያ ልጅ ሳፋን፥ የከተማዪቱም አለቃ መዕሴያ፥ ታሪክ ጸሓፊውም የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአክ የእግዚአብሔርን የአምላኩን ቤት ይጠግኑ ዘንድ ሰደዳቸው። ወደ ታላቁም ካህን ወደ ኬልቅያስ መጡ፤ ሌዋውያኑም በረኞች ከምናሴና ከኤፍሬም፥ ከአለቆችም፥ ከቀረውም ከእስራኤል ሁሉ፥ ከይሁዳና ከብንያም ሁሉ በኢየሩሳሌምም ከሚኖሩት የሰበሰቡትን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት የቀረበውን ገንዘብ ሰጡት። የእግዚአብሔርንም ቤት በሚሠሩት ላይ ለተሾሙት ሰጡ፤ እነርሱም ይጠግኑና ያድሱ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቤት ለሚሠሩ ሠራተኞች ሰጡአቸው። የይሁዳ ነገሥታት ላፈረሱት ቤት ሰረገሎች ያደርጉ ዘንድ፥ ለማጋጠሚያም እንጨት፥ የተጠረበውንም ድንጋይ ይገዙ ዘንድ ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች ሰጡ። ሰዎቹም ሥራውን በመታመን አደረጉ፤ በእነርሱም ላይ የተሾሙት፥ ሥራውንም የሚያሠሩት ሌዋውያን ከሜራሪ ልጆች ይኤትና አብድያስ፥ ከቀዓትም ልጆች ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። ከሌዋውያንም ወገን በዜማ ዕቃ ዐዋቂዎች፥ የነበሩ ሁሉ፥ በተሸካሚዎችና ልዩ ልዩ ሥራ በሚሠሩ ላይ ተሾመው ነበር፤ ጸሓፊዎቹና አለቆቹም በረኞቹም ከሌዋውያን ወገን ነበሩ። ወደ እግዚአብሔርም ቤት የቀረበውን ገንዘብ ባመጡ ጊዜ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ እጅ የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ። ኬልቅያስም ጸሓፊውን ሳፋንን፥ “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቼአለሁ” ብሎ ነገረው። ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው። ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ አመጣ፤ ለንጉሡም ዳግመኛ እንዲህ አለው፥ “ወርቁንና ብሩን፥ መባውንም ሁሉ የቤተ እግዚአብሔርን ሥራ ለሚሠሩ ለአገልጋዮችህ በእጃቸው ሰጧቸው። በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን ገንዘብ አፈሰሱ፤ በሥራው ላይ ለተሾሙትና ለሠራተኞቹም በእጃቸው ሰጡ።” ጸሓፊውም ሳፋን ለንጉሡ፥ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጠኝ” ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው። ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። ንጉሡም ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ አብዶንን፥ ጸሓፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዔሴኢያን፦ “በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ፥ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ ተገኘው የመጽሐፍ ቃል ስለእኔ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ስለቀሩትም እግዚአብሔርን ጠይቁ” ብሎ አዘዛቸው። ኬልቅያስና እነዚያ ንጉሡ ያዘዛቸው ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቴቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርስዋም በኢየሩሳሌም በከተማዪቱ በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ይህንም ነገር ነገሩአት። እርስዋም አለቻቸው፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ የተጻፉትን ቃላት ሁሉ፥ ማለት ክፉ ነገርን አመጣለሁ፥ በእጃቸው ሥራ ሁሉ ሊያስቈጡኝ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት አጥነዋልና ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፤ አይጠፋምም። እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለ ሰማኸው ቃል ልብህ ደንግጦአልና፥ በፊቴም ራስህን አዋርደሃልና፥ በዚህም ስፍራ በሚኖሩበት ላይ ቃሌን በሰማህ ጊዜ ራስህን አዋርደሃልና፥ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። እነሆ፥ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም” ያለቻቸውንም ነገር ለንጉሡ አስረዱት።
2 ዜና መዋዕል 34:8-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣ ምድሪቱንና ቤተ መቅደሱን ካነጻ በኋላ፣ የኤዜልያስን ልጅ ሳፋንን፣ የከተማዪቱን ገዥ መዕሤያንና የጸሓፊውን የኢዮአካዝን ልጅ ኢዮአክን የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይጠግኑ ዘንድ ላካቸው። እነርሱም ወደ ሊቀ ካህኑ ወደ ኬልቅያስ ሄደው፣ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የመጣውን ገንዘብ ሰጡት፤ ገንዘቡም በር ጠባቂዎች የነበሩት ሌዋውያን፣ ከምናሴ፣ ከኤፍሬምና ከመላው የእስራኤል ቅሬታዎች እንደዚሁም ከመላው ይሁዳና ከብንያም፣ ከኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች የሰበሰቡት ነበር። እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ እንዲቈጣጠሩ ለተሾሙት ሰዎች ዐደራ ሰጡ፤ እነዚህም ሰዎች ገንዘቡን ቤተ መቅደሱን ለጠገኑትና ላደሱት ሰዎች ከፈሉ። እንዲሁም የይሁዳ ነገሥታት እንዲፈርሱ ላደረጓቸው ሕንጻዎች ጥርብ ድንጋዮችን፣ ሠረገላዎችንና ማገጣጠሚያ ዕንጨቶችን እንዲገዙ ለየእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ለግንበኞች ገንዘብ ሰጡ። ሰዎቹም ሥራውን በታማኝነት አከናወኑ። የበላይ ሆነው አመራር የሚሰጧቸውም ከሜራሪ ጐሣ የሆኑት ሌዋውያን፣ ኢኤትና አብድዩ፣ ከቀዓት ጐሣ ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። በዜማ ዕቃ የላቀ ችሎታ የነበራቸው ሌዋውያን ሁሉ፣ የጕልበት ሠራተኞች ኀላፊ በመሆን፣ በየሥራው ላይ የተመደቡትን ሠራተኞች ይቈጣጠሩ ነበር። ጥቂቶቹ ሌዋውያን ደግሞ ኀላፊዎች፣ ጸሓፊዎችና በር ጠባቂዎች ነበሩ። ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባውን ገንዘብ በሚያወጡበት ጊዜ፣ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ። ኬልቅያስም ጸሓፊውን ሳፋንን፣ “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አገኘሁት” አለው፤ ከዚያም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው። ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ ወስዶ እንዲህ አለው፤ “ሹማምትህ የታዘዙትን ሁሉ በመፈጸም ላይ ናቸው፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ አውጥተው ለተቈጣጣሪዎቹና ለሠራተኞቹ አስረክበዋል።” ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ንጉሡን፣ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” አለው። ሳፋንም መጽሐፉን ለንጉሡ አነበበለት። ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። ከዚያም ንጉሡ ኬልቅያስን፣ የሳፋን ልጅ አኪቃምን፣ የሚክያስን ልጅ ዓብዶንን፣ ጸሓፊውን ሳፋንንና የንጉሡን የቅርብ አገልጋይ ዓሳያን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ሄዳችሁ ስለ እኔ እንደዚሁም በእስራኤልና በይሁዳ ስላሉት ትሩፋን በተገኘው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ተጻፈው ነገር እግዚአብሔርን ጠይቁ። አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ በላያችን ላይ የፈሰሰው የእግዚአብሔር ቍጣ ታላቅ ነውና፤ በዚህ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት አልተመላለሱምና።” ኬልቅያስና ንጉሡ ከርሱ ጋራ የላካቸው ሰዎች የአልባሳት ጠባቂ የነበረው የሐስራ ልጅ፣ የቲቁዋ ልጅ የሴሌም ሚስት ወደሆነችው ወደ ነቢዪቱ ወደ ሕልዳና ሄደው ነገሯት። እርሷም በኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው የከተማው ክፍል ትኖር ነበር። ነቢዪቱም እንዲህ አለቻቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ በተጻፈው ርግማን ሁሉ መሠረት፣ በዚህ ስፍራና በነዋሪዎቹ ላይ ጥፋትን አመጣለሁ። እኔን ትተውኝ ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑና በእጆቻቸው ሥራ ሁሉ ለቍጣ ስላነሣሡኝ፣ ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፤ አይጠፋምም።’ እግዚአብሔርን እንድትጠይቁ ወደዚህ ቦታ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ ስለ ሰማኸው ነገር የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዚህ ስፍራና በሕዝቡ ላይ የተናገረውን በሰማህ ጊዜ፣ ልብህ ስለ ተነካና በእግዚአብሔር ፊት ራስህን ስላዋረድህ፣ ራስህን ዝቅ አድርገህ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ ስላለቀስህ፣ እኔም ሰምቼሃለሁ ይላል እግዚአብሔር። እነሆ፤ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላም ትቀበራለህ፤ በዚህ ቦታ እና በነዋሪዎቹ ላይ የማመጣውን መከራ ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም።’ ” ሰዎቹም መልሷን ይዘው ወደ ንጉሡ ሄዱ።
2 ዜና መዋዕል 34:8-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በነገሠም በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ምድሪቱንና የእግዚአብሔርን ቤት ካነጻ በኋላ፥ የኤዜልያስ ልጅ ሳፋን፥ የከተማይቱም አለቃ መዕሤያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአክ የእግዚአብሔርን የአምላኩን ቤት ይጠግኑ ዘንድ ሰደዳቸው። ወደ ታላቁም ካህን ወደ ኬልቅያስ መጡ፤ ሌዋውያኑም በረኞች ከምናሴና ከኤፍሬም ከቀረውም ከእስራኤል ሁሉ፥ ከይሁዳና ከብንያም ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም ከሚኖሩት የሰበሰቡትን፥ ወደ እግዚእብሔር ቤት የቀረበውን ገንዘብ ሰጡት። የእግዚአብሔርንም ቤት በሚሠሩት ላይ ለተሾሙት ሰጡ፤ እነርሱም ይጠግኑና ያድሱ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቤት ለሚሠሩ ሠራተኞች ሰጡ። የይሁዳ ነገሥታት ላፈረሱት ቤት ሠረገሎች ያደርጉ ዘንድ፥ ለማጋጠሚያም እንጨት የተጠረበውንም ድንጋይ ይገዙ ዘንድ ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች ሰጡ። ሰዎቹም ሥራውን በመታመን አደረጉ፤ በእነርሱም ላይ የተሾሙት፥ ሥራውንም የሚሠሩት ሌዋውያን ከሜራሪ ልጆች ኢኤትና አብድዩ፥ ከቀዓትም ልጆች ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። ከሌዋውያንም ወገን በዜማ ዕቃ አዋቂዎች የነበሩ ሁሉ በተሸካሚዎችና ልዩ ልዩ ሥራ በሚሠሩ ላይ ተሾመው ነበር፤ ጸሐፊዎቹና አለቆቹ፥ በረኞቹም ከሌዋውያን ወገን ነበሩ። ወደ እግዚአብሔርም ቤት የቀረበውን ገንዘብ ባመጡ ጊዜ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ እጅ የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ። ኬልቅያስም ጸሐፊውን ሳፋንን “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቼአለሁ” ብሎ ተናገረው። ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው። ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ አመጣ፤ ለንጉሡም “ባሪያዎችህ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ሁሉ ያደርጋሉ፤ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን ገንዘብ አፈሰሱ፤ በሥራውም ላይ ለተሾሙትና ለሠራተኞቹ ሰጡ” ብሎ አወራለት። ጸሐፊውም ሳፋን ለንጉሡ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጠኝ” ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው። ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። ንጉሡም ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ ዓብዶንን፥ ጸሐፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓሳያን “በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ፥ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ ተገኘው የመጽሐፍ ቃል ለእኔ፥ በእስራኤልና በይሁዳም ለቀሩት እግዚአብሔርን ጠይቁ” ብሎ አዘዛቸው። ኬልቅያስና እነዚያ ንጉሡ ያዘዛቸው ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ የልጅ ልጅ፥ ወደ ቲቁዋ ልጅ ወደ ሆነው ወደ ሴሌም ሚስት፥ ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርስዋም በኢየሩሳሌም በከተማይቱ በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ይህንንም ነገር ነገሩአት። እርስዋም አለቻቸው “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት’ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘እነሆ፥ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ የተጻፉትን ቃላት ሁሉ፥ ማለት ክፉ ነገርን፥ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ አመጣለሁ። በእጃቸው ሥራ ሁሉ ሊያስቈጡኝ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት ዐጥነዋልና፥ ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፤ አይጠፋምም።’ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ስለ ሰማኸው ቃል ልብህ ገር ሆኖአልና፥ በፊቴም ራስህን አዋርደሃልና፥ በዚህም ስፍራና በሚኖሩበት ላይ ቃሌን በሰማህ ጊዜ ራስህን አዋርደሃልና፥ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ’ ይላል እግዚአብሔር። ‘እነሆ፥ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ ዓይኖችህ አያዩም’።” ይህንም ለንጉሡ አወሩለት።
2 ዜና መዋዕል 34:8-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የአሕዛብን አምልኮ በማጥፋት ምድሪቱንና ቤተ መቅደሱን ካነጻ በኋላ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ያድሱ ዘንድ የአጻልያን ልጅ ሳፋንን፥ የኢየሩሳሌም አስተዳዳሪ የሆነውን ማዕሤያንና የኢዮአሐዝን ልጅ ጸሐፊውን ዮአሕን ላከ፤ ዘብ ጠባቂዎች የሆኑ ሌዋውያን በቤተ መቅደስ ውስጥ የሰበሰቡት ገንዘብ ሁሉ፥ ለሊቀ ካህናቱ ለሒልቂያ ተሰጠ፤ ገንዘቡም የተሰበሰበው ከኤፍሬም፥ ከምናሴና ከቀረውም የእስራኤል ሕዝብ፥ እንዲሁም ከይሁዳ፥ ከብንያምና ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ነበር፤ ይህም ገንዘብ ለቤተ መቅደሱ እድሳት ኀላፊዎች ለነበሩት ለነዚያ ሦስት ሰዎች ተሰጠ፤ እነርሱም በበኩላቸው ገንዘቡን ለሠራተኞችና የይሁዳ ነገሥታት እንዲፈራርሱ ያደረጉአቸውን ሕንጻዎች ማሠሪያ የሚሆን ድንጋይና እንጨት ይገዙበት ዘንድ ለአናጢዎችና ለግንበኞች ሰጡ፤ አናጢዎቹና ግንበኞቹም ሥራውን በታማኝነት አከናወኑ፤ የእነርሱም የበላይ ተቈጣጣሪዎች ከመራሪ ጐሣ ያሐትና አብድዩ፥ ከቀዓት ጐሣ ዘካርያስና መሹላም ተብለው የሚጠሩት አራት ሌዋውያን ነበሩ፤ (ሌዋውያን ሁሉ በዜማ መሣሪያ የመዘመር ከፍ ያለ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ነበሩ፤) ሌሎቹ ሌዋውያን ዕቃዎችን ለሚያጓጒዙና በልዩ ልዩ ሥራ ለተመደቡ ሠራተኞች የበላይ ኀላፊዎችና ተቈጣጣሪዎች ሲሆኑ፥ የቀሩት ሌዋውያን ደግሞ ጸሐፊዎች ወይም ዘብ ጠባቂዎች ነበሩ። የቀረበውን ገንዘብ ከግምጃ ቤት ያወጡ በነበሩበት ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ሒልቂያ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ፤ እርሱም ጸሐፊውን ሳፋንን “የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ በዚህ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አግኝቻለሁ” በማለት መጽሐፉን ሰጠው፤ ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ ወስዶ ንጉሡን “እነሆ፥ አንተ ያዘዝከንን ሁሉ አድርገናል፤ በቤተ መቅደሱ ተቀምጦ የነበረውን ገንዘብ ወስደን ለሠራተኞችና እነርሱን ለሚቈጣጠሩ ሰዎች አስረክበናል” አለው፤ ንግግሩንም በመቀጠል “ሒልቂያ የሰጠኝ መጽሐፍ እነሆ፥ በእጄ ይገኛል” አለው፤ መጽሐፉንም ለንጉሡ አነበበለት። ንጉሡም የሕጉ ቃላት ሲነበብለት በሰማ ጊዜ፥ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ ከዚህም በኋላ ንጉሡ ለሒልቂያ፥ ለሳፋን ልጅ ለአሒቃም፥ ለሚክያስ ልጅ ለዐብዶን፥ ለቤተ መንግሥቱ ጸሐፊ ለሳፋንና የንጉሡ የቅርብ አገልጋይ ለሆነው ለዓሳያ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጠ፥ “ሄዳችሁ ስለ እኔና እንዲሁም በእስራኤልና በይሁዳ ስለ ቀረው ሕዝብ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ በዚህ መጽሐፍ ስላለውም ትምህርት አረጋግጡ፤ የቀድሞ አባቶቻችን ለእግዚአብሔር ቃል ባለመታዘዛቸውና ይህ መጽሐፍ አድርጉ የሚላቸውን ሁሉ ባለመፈጸማቸው፥ እግዚአብሔር ቊጣውን በእኛ ላይ አውርዶአል።” ሒልቂያና የቀሩት ሰዎች ንጉሡ ባዘዛቸው መሠረት በኢየሩሳሌም ከተማ አዲሱ ክፍል ነዋሪ ወደሆነችው ሑልዳ ተብላ ወደምትጠራ ነቢይት ሄደው ስለ ተላኩበት ጉዳይ ጠየቁአት፤ የዚህች ነቢይት ባለቤት ሻሉም ተብሎ የሚጠራ የቲቅዋ ልጅ የሐርሐስ የልጅ ልጅ ሲሆን፥ እርሱም የቤተ መቅደሱ አልባሳት ኀላፊ ነበር፤ ሰዎቹም ለነቢይቱ ሁኔታውን በዝርዝር ገለጡላት፤ እርስዋም “ወደ እኔ ወደ ላካችሁ ሰው ተመልሳችሁ በመሄድ፥ ከዚህ የሚከተለውን የእግዚአብሔር ቃል ስጡት አለቻቸው።” ቃሉም እንዲህ የሚል ነበር፦ “እኔ እግዚአብሔር ለይሁዳ ንጉሥ በተነበበለት መጽሐፍ ውስጥ በሚገኙት እርግማኖች ኢየሩሳሌምንና ሕዝብዋን ሁሉ እቀጣለሁ፤ እነርሱ እኔን ትተው ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት አቅርበዋል፤ ይህም ያደረጉት በደል ቊጣዬን አነሣሥቶአል፤ በኢየሩሳሌም ላይ የተነሣሣው ቊጣዬም ይፈጸማል እንጂ አይበርድም፤ ስለ ንጉሡ የሆነ እንደ ሆነ፥ እኔ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ ‘አንተ በዚያ መጽሐፍ የተነገረውን ቃል ሰምተሃል፤ እኔ ኢየሩሳሌምንና ሕዝብዋን እንዴት እንደምቀጣ በሰማህ ጊዜ፥ ራስህን አዋርደኽ በሐዘን ልብስህን በመቅደድና በማልቀስ ንስሓ ገብተሃል፤ ስለዚህ ጸሎትህን ሰምቼአለሁ። አንተ በሕይወት እስካለህ ድረስ በኢየሩሳሌም ላይ ቅጣት አላመጣም፤ አንተ በሰላም እንድትሞት አደርጋለሁ።’ ” ሰዎቹም ይህን መልእክት ይዘው ወደ ንጉሥ ኢዮስያስ ተመለሱ።
2 ዜና መዋዕል 34:8-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በነገሠም በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት ምድሪቱንና የጌታን ቤት ካነጻ በኋላ፥ የኤዜልያስ ልጅ ሳፋን፥ የከተማይቱም አለቃ መዕሤያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአክ የጌታን የአምላኩን ቤት እንዲጠግኑ ላካቸው። ወደ ታላቁም ካህን ወደ ኬልቅያስ መጡ፤ ሌዋውያኑም የደጆቹም ጠባቂዎች ከምናሴና ከኤፍሬም ከቀረውም ከእስራኤል ሁሉ፥ ከይሁዳና ከብንያም ሁሉ በኢየሩሳሌምም ከሚኖሩት የሰበሰቡትን፥ ወደ ጌታ ቤት ያመጡትን ገንዘብ ሰጡት። የጌታንም ቤት በሚሠሩት ላይ ለተሾሙት ሰጡ፤ በጌታም ቤት የሚሠሩት ሠራተኞች ቤቱን ለሚጠግኑና ለሚያድሱ ሠራተኞች ሰጡ። እነርሱም የይሁዳ ነገሥታት ላፈረሱት ቤት ሰረገሎች እንዲሠሩ፥ ለማጋጠሚያም እንጨት የተጠረበውንም ድንጋይ እንዲገዙ ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች ሰጡ። ሰዎቹም ሥራውን በታማኝነት ሠሩ፤ በእነርሱም ላይ የተሾሙት፥ ሥራውንም የሚሠሩት ሌዋውያን ከሜራሪ ልጆች ኢኤትና አብድዩ፥ ከቀዓትም ልጆች ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። ከሌዋውያንም ወገን በዜማ ዕቃ አዋቂዎች የነበሩ ሁሉ በተሸካሚዎችና ልዩ ልዩ ሥራ በሚሠሩ ላይ ተሾመው ነበር፤ ጸሐፊዎቹና አለቆቹም የደጁም ጠባቂዎች ከሌዋውያን ወገን ነበሩ። ወደ ጌታም ቤት የቀረበውን ገንዘብ ባመጡ ጊዜ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ እጅ የተሰጠውን የጌታን የሕግ መጽሐፍ አገኘ። ኬልቅያስም ጸሐፊውን ሳፋንን፦ “የሕጉን መጽሐፍ በጌታ ቤት አግኝቼአለሁ” ብሎ ተናገረው። ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው። ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ አመጣ፤ ለንጉሡም እንዲህ ብሎ አወራለት፦ “ባርያዎችህ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ሁሉ እያደረጉ ነው፤ በጌታም ቤት የተገኘውን ገንዘብ አፈሰሱ፥ በሥራውም ላይ ለተሾሙትና ለሠራተኞቹ ሰጡ።” ጸሐፊውም ሳፋን ለንጉሡ፦ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጠኝ” ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው። ንጉሡም የሕጉን ቃላት በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። ንጉሡም ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ ዓብዶንን፥ ጸሐፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓሳያን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለማድረግ አባቶቻችን የጌታን ቃል ስላልጠበቁ፥ በእኛ ላይ የነደደው የጌታ ቁጣ እጅግ ታላቅ ነውና ሄዳችሁ ስለ ተገኘው የመጽሐፍ ቃል ለእኔ በእስራኤልና በይሁዳም ለቀሩት ጌታን ጠይቁ።” ኬልቅያስና እነዚያ ንጉሡ የላካቸው ሰዎች ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቲቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርሷም በኢየሩሳሌም በከተማይቱ በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ይህንንም ነገር ነገሩአት። እርሷም እንዲህ አለቻቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ የተጻፉትን ቃላት ሁሉ፥ ማለት ክፉ ነገርን፥ በዚህ ስፍራና በነዋሪዎችዋ ላይ አመጣለሁ። በእጃቸው ሥራ ሁሉ ሊያስቈጡኝ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት ዐጥነዋልና ቁጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፥ አይጠፋምም። ጌታን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፦ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለ ሰማኸው ቃላት፥ ልብህ ተጸጽቶአልና፥ በፊቴም ራስህን አዋርደሃልና፥ በዚህም ስፍራና በነዋሪዎችዋ ላይ የተናገርሁትን ቃላቴን በሰማህ ጊዜ ራስህን አዋርደሃልና፥ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ፥ ይላል ጌታ። እነሆ፥ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፥ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራና በሚኖሩባትም ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም።’ ” ይህንም ለንጉሡ አወሩለት።