ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 34
34
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ
(2ነገ. 22፥1-2)
1ኢዮስያስ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ስምንት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ። #ኤር. 3፥6። 2ኢዮስያስ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ፤ የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም ምሳሌነት ከመከተል ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም።
ኢዮስያስ የአሕዛብ የማምለኪያ ስፍራዎችን ማስወገዱ
3ኢዮስያስ በነገሠ በስምንተኛ ዓመቱ፥ ገና ወጣት ሳለ የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን አምላክ እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመረ፤ ከአራት ዓመት በኋላም የአሕዛብ የማምለኪያ ስፍራዎችን፥ አሼራ ተብላ የምትጠራ የሴት አምላክ ምስሎችንና ሌሎችን ጣዖቶች ሁሉ ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ማስወገድ ጀመረ፤ 4በእርሱም ትእዛዝ የእርሱ ሰዎች ባዓል ተብሎ የሚጠራው ጣዖት ይመለክባቸው የነበሩትን መሠዊያዎችንና በእነርሱም አጠገብ የነበሩትን ዕጣን የሚታጠንባቸውን መሠዊያዎች ሰባበሩ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስሎችንና ሌሎችንም ጣዖቶች ሁሉ ትቢያ እስኪሆኑ ድረስ አደቀቁአቸው፤ ትቢያውንም ወስደው ለእነዚያ ጣዖቶች መሥዋዕት ያቀርቡ በነበሩ ሰዎች መቃብር ላይ በተኑት፤ #2ነገ. 21፥3፤ 2ዜ.መ. 33፥3። 5ኢዮስያስ የአሕዛብን ካህናት ዐፅም ሁሉ እነርሱ ራሳቸው ይሰግዱላቸው በነበሩት መሠዊያዎች ላይ አቃጠላቸው፤ ይህን ሁሉ በማድረጉም ይሁዳና ኢየሩሳሌም በሥርዓት እንደገና እንዲነጹ አደረገ፤ #1ነገ. 13፥2። 6እስከ ሰሜን ንፍታሌም ድረስ ባሉ በምናሴ፥ በኤፍሬምና በስምዖን ግዛቶች በሚገኙ ከተሞች እንዲሁም በተደመሰሱት አካባቢዎቻቸው ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸመ። 7የሰሜን የእስራኤል ግዛት የነበሩትን የጣዖቶች መሠዊያዎችንና የአሼራ ምስሎችን ሁሉ ሰባበራቸው፤ ጣዖቶቹንም ትቢያ እስኪሆኑ አደቀቃቸው፤ ዕጣን የሚታጠንባቸውንም የጣዖት መሠዊያዎች አንከታክቶ ጣለ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
የእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ መገኘት
(2ነገ. 22፥3-20)
8ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የአሕዛብን አምልኮ በማጥፋት ምድሪቱንና ቤተ መቅደሱን ካነጻ በኋላ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ያድሱ ዘንድ የአጻልያን ልጅ ሳፋንን፥ የኢየሩሳሌም አስተዳዳሪ የሆነውን ማዕሤያንና የኢዮአሐዝን ልጅ ጸሐፊውን ዮአሕን ላከ፤ 9ዘብ ጠባቂዎች የሆኑ ሌዋውያን በቤተ መቅደስ ውስጥ የሰበሰቡት ገንዘብ ሁሉ፥ ለሊቀ ካህናቱ ለሒልቂያ ተሰጠ፤ ገንዘቡም የተሰበሰበው ከኤፍሬም፥ ከምናሴና ከቀረውም የእስራኤል ሕዝብ፥ እንዲሁም ከይሁዳ፥ ከብንያምና ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ነበር፤ 10ይህም ገንዘብ ለቤተ መቅደሱ እድሳት ኀላፊዎች ለነበሩት ለነዚያ ሦስት ሰዎች ተሰጠ፤ እነርሱም በበኩላቸው ገንዘቡን ለሠራተኞችና 11የይሁዳ ነገሥታት እንዲፈራርሱ ያደረጉአቸውን ሕንጻዎች ማሠሪያ የሚሆን ድንጋይና እንጨት ይገዙበት ዘንድ ለአናጢዎችና ለግንበኞች ሰጡ፤ 12አናጢዎቹና ግንበኞቹም ሥራውን በታማኝነት አከናወኑ፤ የእነርሱም የበላይ ተቈጣጣሪዎች ከመራሪ ጐሣ ያሐትና አብድዩ፥ ከቀዓት ጐሣ ዘካርያስና መሹላም ተብለው የሚጠሩት አራት ሌዋውያን ነበሩ፤ (ሌዋውያን ሁሉ በዜማ መሣሪያ የመዘመር ከፍ ያለ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ነበሩ፤) 13ሌሎቹ ሌዋውያን ዕቃዎችን ለሚያጓጒዙና በልዩ ልዩ ሥራ ለተመደቡ ሠራተኞች የበላይ ኀላፊዎችና ተቈጣጣሪዎች ሲሆኑ፥ የቀሩት ሌዋውያን ደግሞ ጸሐፊዎች ወይም ዘብ ጠባቂዎች ነበሩ።
14የቀረበውን ገንዘብ ከግምጃ ቤት ያወጡ በነበሩበት ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ሒልቂያ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ፤ 15እርሱም ጸሐፊውን ሳፋንን “የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ በዚህ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አግኝቻለሁ” በማለት መጽሐፉን ሰጠው፤ 16ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ ወስዶ ንጉሡን “እነሆ፥ አንተ ያዘዝከንን ሁሉ አድርገናል፤ 17በቤተ መቅደሱ ተቀምጦ የነበረውን ገንዘብ ወስደን ለሠራተኞችና እነርሱን ለሚቈጣጠሩ ሰዎች አስረክበናል” አለው፤ 18ንግግሩንም በመቀጠል “ሒልቂያ የሰጠኝ መጽሐፍ እነሆ፥ በእጄ ይገኛል” አለው፤ መጽሐፉንም ለንጉሡ አነበበለት።
19ንጉሡም የሕጉ ቃላት ሲነበብለት በሰማ ጊዜ፥ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ 20ከዚህም በኋላ ንጉሡ ለሒልቂያ፥ ለሳፋን ልጅ ለአሒቃም፥ ለሚክያስ ልጅ ለዐብዶን፥ ለቤተ መንግሥቱ ጸሐፊ ለሳፋንና የንጉሡ የቅርብ አገልጋይ ለሆነው ለዓሳያ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጠ፥ 21“ሄዳችሁ ስለ እኔና እንዲሁም በእስራኤልና በይሁዳ ስለ ቀረው ሕዝብ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ በዚህ መጽሐፍ ስላለውም ትምህርት አረጋግጡ፤ የቀድሞ አባቶቻችን ለእግዚአብሔር ቃል ባለመታዘዛቸውና ይህ መጽሐፍ አድርጉ የሚላቸውን ሁሉ ባለመፈጸማቸው፥ እግዚአብሔር ቊጣውን በእኛ ላይ አውርዶአል።”
22ሒልቂያና የቀሩት ሰዎች ንጉሡ ባዘዛቸው መሠረት በኢየሩሳሌም ከተማ አዲሱ ክፍል ነዋሪ ወደሆነችው ሑልዳ ተብላ ወደምትጠራ ነቢይት ሄደው ስለ ተላኩበት ጉዳይ ጠየቁአት፤ የዚህች ነቢይት ባለቤት ሻሉም ተብሎ የሚጠራ የቲቅዋ ልጅ የሐርሐስ የልጅ ልጅ ሲሆን፥ እርሱም የቤተ መቅደሱ አልባሳት ኀላፊ ነበር፤ ሰዎቹም ለነቢይቱ ሁኔታውን በዝርዝር ገለጡላት፤ 23እርስዋም “ወደ እኔ ወደ ላካችሁ ሰው ተመልሳችሁ በመሄድ፥ ከዚህ የሚከተለውን የእግዚአብሔር ቃል ስጡት አለቻቸው።” 24ቃሉም እንዲህ የሚል ነበር፦ “እኔ እግዚአብሔር ለይሁዳ ንጉሥ በተነበበለት መጽሐፍ ውስጥ በሚገኙት እርግማኖች ኢየሩሳሌምንና ሕዝብዋን ሁሉ እቀጣለሁ፤ 25እነርሱ እኔን ትተው ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት አቅርበዋል፤ ይህም ያደረጉት በደል ቊጣዬን አነሣሥቶአል፤ በኢየሩሳሌም ላይ የተነሣሣው ቊጣዬም ይፈጸማል እንጂ አይበርድም፤ 26ስለ ንጉሡ የሆነ እንደ ሆነ፥ እኔ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ ‘አንተ በዚያ መጽሐፍ የተነገረውን ቃል ሰምተሃል፤ 27እኔ ኢየሩሳሌምንና ሕዝብዋን እንዴት እንደምቀጣ በሰማህ ጊዜ፥ ራስህን አዋርደኽ በሐዘን ልብስህን በመቅደድና በማልቀስ ንስሓ ገብተሃል፤ ስለዚህ ጸሎትህን ሰምቼአለሁ። 28አንተ በሕይወት እስካለህ ድረስ በኢየሩሳሌም ላይ ቅጣት አላመጣም፤ አንተ በሰላም እንድትሞት አደርጋለሁ።’ ”
ሰዎቹም ይህን መልእክት ይዘው ወደ ንጉሥ ኢዮስያስ ተመለሱ።
ኢዮስያስ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ ቃል ኪዳን መግባቱ
(2ነገ. 23፥1-20)
29ንጉሥ ኢዮስያስ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን የታወቁ ሽማግሌዎች ሁሉ በማስጠራት በአንድነት እንዲሰበሰቡ አደረገ፤ 30እነርሱም ከንጉሡ ጋር ካህናትንና ሌዋውያንን፥ ሌሎችንም ሰዎች ማለትም ባለጸጎችንም ድኾችንም ሁሉ አስከትለው ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፤ ንጉሡም በዚያ ጠፍቶ በነበረውና በቤተ መቅደስ በተገኘው የቃል ኪዳን መጽሐፍ የሰፈረውን ቃል በሙሉ ለሕዝቡ አነበበ፤ 31ንጉሡ በዐምዱ አጠገብ ቆሞ በሙሉ ልቡና ሐሳቡ እግዚአብሔርን ለመከተልና ትእዛዞቹን፥ ደንቦቹንና ድንጋጌዎቹን ለመጠበቅ በእርሱ ፊት ቃል ኪዳኑን አደሰ፤ ስለዚህም በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ቃል ኪዳን አረጋገጠ። 32ከዚህ በኋላ መላው የብንያም ሕዝብና በኢየሩሳሌም የተገኙ ሌሎች ሰዎች ሁሉ ቃል ኪዳኑን ይጠብቁ ዘንድ ቃል እንዲገቡ አደረገ፤ በዚህም መሠረት የኢየሩሳሌም ሕዝብ ከቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር የገቡት ቃል ኪዳን የሚጠይቀውን ግዴታ ሁሉ ፈጸሙ፤ 33ንጉሥ ኢዮስያስ በእስራኤል ግዛት ውስጥ የነበሩትን አጸያፊ ጣዖቶች ሁሉ አስወግዶ፥ ሕዝቡ አምላኩን እግዚአብሔርን እንዲያገለግል አደረገ፤ በዘመነ መንግሥቱም ሁሉ ሕዝቡ ከቀድሞ አባቶቹ አምላክ ከእግዚአብሔር ፈቀቅ አላሉም።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 34: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997