ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 33

33
የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ
(2ነገ. 21፥1-9)
1ምናሴ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኀምሳ አምስት ዓመት ገዛ፤ 2እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ አገር በሚገቡበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ከፊታቸው ነቃቅሎ ያጠፋቸውን የአሕዛብን አሳፋሪ ልማድ በመከተል፥ ምናሴ የሠራው ኃጢአት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ #ኤር. 15፥4። 3ምናሴ አባቱ ሕዝቅያስ አፈራርሶአቸው የነበሩትን የአሕዛብ የማምለኪያ ስፍራዎች እንደገና ሠራ፤ ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ መሠዊያዎችን፥ አሼራ ተብላ ለምትጠራው ሴት አምላክ ምስሎችን አቆመ፤ የሰማይ ከዋክብትንም አመለከ፤ 4እግዚአብሔር ለዘለዓለም ስሙ ይጠራበታል ባለው ስፍራ፥ ማለትም በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ አረማዊ መሠዊያዎችን ተከለ፤ #2ዜ.መ. 6፥6። 5በሁለቱም የቤተ መቅደሱ አደባባዮች የሰማይ ከዋክብት የሚመለኩባቸውን መሠዊያዎች ሠራ፤ 6የገዛ ወንዶች ልጆቹንም በሂኖም ሸለቆ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ እርሱም ራሱ ሟርተኛና አስማተኛ ሆኖ፥ ከጠንቋዮችና ከሙታን ጠሪዎች ምክርን ይጠይቅ ነበር፤ በዚህም ሁሉ አድራጎቱ ታላቅ ኃጢአት ስለ ሠራ፥ እግዚአብሔርን አስቈጣ። 7በቤተ መቅደስም ውስጥ የጣዖት ምስልን አቆመ፤ ይህም ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን “ይህ በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ ስሜ እንዲጠራበት ከዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ግዛት ሁሉ የመረጥኩት የተቀደሰ ስፍራ ነው፤ 8እስራኤላውያን በሙሴ አማካይነት ያዘዝኳቸውን ሕጌን፥ ሥርዓቴንና ድንጋጌዬን ሁሉ በጥንቃቄ ቢጠብቁ ለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ምድር እንደገና እንዲፈናቀሉ አላደርግም። #1ነገ. 9፥3-5፤ 2ዜ.መ. 7፥12-18። 9ምናሴ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ፥ የእስራኤል ልጆች ወደ ተስፋይቱ አገር በሚገቡበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ከፊታቸው እንዲባረሩ ያደረጋቸው ሕዝቦች ካደረጉት ይበልጥ የከፋ ኃጢአት እንዲሠሩ አደረጋቸው።”
ምናሴ በሠራው ኃጢአት መጸጸቱ
10እግዚአብሔር ምናሴንና ሕዝቡን በብርቱ ያስጠነቀቃቸው ቢሆንም እንኳ እነርሱ መስማትን እምቢ አሉ፤ 11ስለዚህም የአሦር ሠራዊት ይሁዳን እንዲወር እግዚአብሔር ፈቀደ፤ ሠራዊቱም ምናሴን ማርኮ በአፍንጫው ሥናጋ በማግባት በሰንሰለት አስሮ ወደ ባቢሎን ወሰደው። 12ምናሴ ሥቃይ በበዛበት ጊዜ ራሱን በትሕትና በማዋረድ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ተመለሰ፤ የእግዚአብሔርንም ርዳታ ለመነ፤ 13እግዚአብሔርም የምናሴን ጸሎት ሰማ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመልሶ እንደገና እንዲገዛ ፈቀደለት፤ በዚህም ምናሴ እግዚአብሔር እውነተኛ አምላክ መሆኑን ተገነዘበ።
14ከዚህ በኋላ ምናሴ በዳዊት ከተማ በስተ ምሥራቅ በኩል የሚገኘውን የውጪ ቅጽር ቁመት ከፍ አድርጎ ሠራ፤ ይህም ቅጽር በሸለቆው ውስጥ ከግዮን ምንጭ በስተ ምዕራብ በኩል አንሥቶ፥ በስተ ሰሜን እስከ ዓሣ ቅጽር በር የሚደርስ ሲሆን፥ በከተማይቱ አጠገብ የሚገኘውን ዖፌል ተብሎ የሚጠራውን ስፍራ የሚያጠቃልል ነው፤ እንዲሁም ምናሴ በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሁሉ፥ ለእያንዳንዳቸው አንዳንድ የክፍለ ጦር አዛዥ መደበላቸው። 15ምናሴ ባዕዳን አማልክትንና እርሱ ራሱ በዚያ አቁሞት የነበረውን የጣዖት ምስል ከቤተ መቅደስ አወጣ፤ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደሱ በቆመበት ኰረብታና በሌሎችም ስፍራዎች ላይ የነበሩትን የጣዖቶች መሠዊያዎች ሁሉ አስወገደ፤ እነዚህንም ሁሉ አንሥቶ፥ ከከተማይቱ ውጪ ጣላቸው፤ 16የእግዚአብሔርንም መሠዊያ በማደስ በላዩ ላይ የኅብረት መሥዋዕትና የምስጋና መባን አቀረበ፤ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያመልኩም ዘንድ መላውን የይሁዳ ሕዝብ አዘዘ። 17ሕዝቡ በሌሎቹ ኰረብታማ የማምለኪያ ስፍራዎች ላይ መሥዋዕት ማቅረባቸውን ቢቀጥሉም እንኳ መሥዋዕቱን የሚያቀርቡት ለእግዚአብሔር ብቻ ነበር።
የምናሴ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ
(2ነገ. 21፥17-18)
18ምናሴ ያደረገው ሌላ ነገር ሁሉ፥ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር ያቀረበው ጸሎት፥ ነቢያት በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ለምናሴ የተናገሩአቸው ቃላት ጭምር፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግበው ይገኛሉ። 19ንጉሥ ምናሴ ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው ጸሎትና፥ እግዚአብሔርም ለጸሎቱ የሰጠው መልስ፥ ተጸጽቶ ንስሓ ከመግባቱ በፊት ያደረገው ኃጢአት ሁሉ፥ ማለትም የፈጸመው ልዩ ልዩ ክፋት፥ እርሱ ራሱ የሠራቸው የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችና አሼራ ተብላ የምትጠራው ሴት አምላክ ምስሎች፥ ያመልካቸው የነበሩ ጣዖቶች ሁሉ፥ በነቢያት የታሪክ መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ። 20ምናሴ ሞተ፤ በቤተ መንግሥቱም አጠገብ በሚገኘው ስፍራ ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አሞን ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ አሞን
(2ነገ. 21፥19-26)
21አሞን ዕድሜው ኻያ ሁለት ዓመት ሲሆነው በይሁዳ ላይ ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ፤ 22እርሱም እንደ አባቱ እንደ ምናሴ ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ አባቱ ያመልካቸው የነበሩትንም ጣዖቶች አመለከ፤ መሥዋዕትንም አቀረበላቸው። 23አባቱ እንዳደረገው ሁሉ ራሱን በትሕትና ዝቅ አድርጎ በማዋረድ ወደ እግዚአብሔር አልተመለሰም፤ እንዲያውም ከአባቱ ይበልጥ የከፋ ኃጢአት ሠራ።
24የአሞን ባለሟሎች የሆኑት ባለሥልጣኖች በእርሱ ላይ በማሤር በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ገደሉት፤ 25የይሁዳም ሕዝብ የአሞንን ገዳዮች ገድለው በእርሱ እግር ልጁን ኢዮስያስን አነገሡ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ