ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 32
32
አሦራውያን በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል መዛታቸው
(2ነገ. 18፥13-37፤ 19፥14-19፤35-37፤ ኢሳ. 36፥1-22፤ 37፥8-38)
1ንጉሥ ሕዝቅያስ እግዚአብሔርን በታማኝነት በማገልገል ብዙ ነገሮችን ካከናወነ በኋላ፥ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ሰናክሬም ይሁዳን ወረረ፤ እንደሚያሸንፍ ተማምኖ የተመሸጉትን ከተሞች ከበበ 2ሰናክሬም በኢየሩሳሌምም ላይ አደጋ ለመጣል ያቀደ መሆኑን ንጉሥ ሕዝቅያስ በተገነዘበ ጊዜ፥ 3-4እርሱ ከባለሟሎቹ ባለሥልጣኖች ጋር ከከተማይቱ ውጪ ያሉትን ምንጮችና የውሃ መተላለፊያ ቦይ ለመድፈን ተማከረ፤ እነርሱም ረዱት፤ ይህንንም ያደረጉት አሦራውያን ወደ ኢየሩሳሌም ሲቃረቡ ምንም ውሃ እንዳያገኙ ለማድረግ ነው፤ ስለዚህ ባለሥልጣኖቹ ብዙ ሰዎችን ወደዚያ በመውሰድ ከምንጮቹ ውሃ እንዳይፈስስ ለማድረግ፥ እነዚያን ምንጮች ሁሉ ደፈኑአቸው። 5ንጉሥ ሕዝቅያስም ቅጽሮችን ጠግኖ በላያቸው ላይ የመቈጣጣሪያ ግንቦችን በመሥራትና ከውጪም በኩል ቅጽሮችን በመገንባት የከተማይቱን መከላከያዎች አጠናከረ፤ በተጨማሪም ከጥንታዊት ኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ በኩል በሚገኘው በተደለደለው ቦታ ላይ የተሠሩትን መከላከያዎች አደሰ፤ ብዙ ጦርና ጋሻም ሠራ። 6የከተማይቱ ነዋሪዎች የሆኑ ወንዶች ሁሉ፥ በጦር መኰንኖች ሥልጣን ሥር እንዲሆኑ አድርጎ፥ በከተማይቱ ቅጽር በር አጠገብ በሚገኘው ገላጣ አደባባይ ላይ ሰበሰባቸው፤ እንዲህም በማለት አበረታታቸው፤ 7“ብርቱዎች ልበ ሙሉዎች ሁኑ፤ የአሦርን ንጉሠ ነገሥትንም ሆነ በእርሱ የሚመራውን ሠራዊት አትፍሩ፤ ከእርሱ ጋር ካለው ኀይል ይልቅ ከእኛ ጋር ያለው ኀይል ይበልጣል፤ 8ከእርሱ ጋር ያለው ኀይል ሰብአዊ ኀይል ነው፤ ከእኛ ጋር ሆኖ የሚረዳንና የሚዋጋልን ግን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፤” ሕዝቡም ንጉሡ በተናገረው በዚህ ቃል ተበረታታ።
9ከዚህ በኋላ ትንሽ ቈይቶ፥ ንጉሥ ሰናክሬምና ሠራዊቱ ገና በላኪሽ ሳሉ ለሕዝቅያስና ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ለነበሩት ለይሁዳ ሕዝብ እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፤ 10“እኔ የአሦር ንጉሠ ነገሥት የሆንኩ ሰናክሬም፥ በእኔ ሠራዊት በተከበበችው በኢየሩሳሌም ለመቈየት ያሰባችሁት በማን ተማምናችሁ እንደ ሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ፤ 11ሕዝቅያስ ‘አምላካችን እግዚአብሔር ከአሦራውያን እጅ ያድነናል’ ይላችኋል፤ ነገር ግን እርሱ እንደዚህ ባለ አነጋገር እያታለለ፥ በራብና በውሃ ጥም እንድታልቁ ሊያደርጋችሁ ነው፤ 12ከዚህ ቀደም የተቀደሱትን የእግዚአብሔርን ማምለኪያ ስፍራዎችና መሠዊያዎችን ያፈራረሰ፥ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብም በአንድ መሠዊያ ላይ ብቻ ዕጣን እያጠነ እንዲሰግድ ያደረገ ሕዝቅያስ ነው፤ 13የቀድሞ አባቶቼና እኔ በሌሎች ሕዝቦች ላይ ምን እንዳደረግን አታውቁምን? ከሌሎች ሕዝቦች አማልእክት መካከል ሕዝቡን ከአሦር ንጉሠ ነገሥት ያዳነ አምላክ አንድ እንኳ ይገኛልን? 14አባቶቼ ካወደሙአቸው ከእነዚህ አገሮች አማልክት መካከል አንዱ እንኳ አገሩን ያዳነበት ጊዜ አለን? ታዲያ፥ የእናንተ አምላክ ከእጄ እንዴት ሊያድናችሁ ይችላል? 15ስለዚህ ሕዝቅያስ በዚህ መንገድ አያታላችሁ! ወደ ስሕተትም አይምራችሁ! ከቶ እርሱን አትመኑ! የማንም ሕዝብ አምላክ የራሱን ሕዝብ ከማንኛውም የአሦር ንጉሠ ነገሥት እጅ ሊያድን የቻለበት ጊዜ የለም፤ ይህም የእናንተ አምላክ እናንተን ሊያድን እንደማይችል የተረጋገጠ ነው።”
16የአሦር ባለሥልጣኖችም በእግዚአብሔርና በአገልጋዩ በሕዝቅያስ ላይ ከዚህ የከፋ ነገር ተናገሩ፤ 17የአሦር ንጉሠ ነገሥት የጻፈው ደብዳቤ “የሌሎች ሕዝቦች አማልክት ሕዝቦቻቸውን ከእኔ እጅ አላዳኑም፤ የሕዝቅያስም አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ሊያድናቸው ከቶ አይችልም” በማለት የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚዘልፍ ነበር፤ 18የአሦር ባለሥልጣኖች ይህን የዛቻ ቃል በዕብራይስጥ ቋንቋ በቅጽሮቹ ላይ ለነበሩት ለኢየሩሳሌም ሰዎች ከፍ ባለ ድምፅ ያሰሙ ነበር፤ ይህንንም ያደረጉበት ምክንያት ሕዝቡን አስፈራርተው ተስፋ በማስቈረጥ ከተማይቱን በቀላል ለመያዝ ዐቅደው ነው። 19በሰው እጅ በተሠሩ በሌሎች ሕዝቦች የጣዖት አማልክት ላይ በድፍረት በተናገሩት ዐይነት በኢየሩሳሌም አምላክ ላይም ይናገሩ ነበር።
20ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ፤ እንዲረዳቸውም ወደ እርሱ አጥብቀው ጮኹ፤ 21እግዚአብሔርም መልአክን ልኮ የአሦርን ወታደሮችና የጦር መኰንኖች እንዲገደሉ አደረገ፤ ስለዚህም የአሦር ንጉሠ ነገሥት ተዋርዶ ወደ አገሩ ተመለሰ፤ አንድ ቀን በአምላኩ መስገጃ ስፍራ በነበረበት ወቅት የገዛ ልጆቹ በሰይፍ ገደሉት።
22በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር ንጉሥ ሕዝቅያስንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ከአሦር ንጉሠ ነገሥት ከሰናክሬብና ከሌሎቹም ጠላቶቻቸው እጅ በመታደግ አዳናቸው፤ ጐረቤቶቻቸው ከሆኑትም ሕዝቦች ሁሉ ጋር በሰላም እንዲኖሩ ፈቀደ። 23ብዙ ሰዎች ለእግዚአብሔር መባን፥ ለንጉሥ ሕዝቅያስ ደግሞ ገጸ በረከትን ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ሕዝቦች ሁሉ ሕዝቅያስን ከፍ ባለ አክብሮት ተመለከቱት።
ሕዝቅያስ እግዚአብሔርን ባለማመስገኑ መወቀሱ
(2ነገ. 20፥1-3፤12-19፤ ኢሳ. 38፥1-3፤ 39፥1-8)
24በዚያኑ ጊዜ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ ሊሞት ተቃርቦ ነበር፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እግዚአብሔርም እንደሚያድነው የሚያረጋግጥ ምልክት አሳየው። 25ሕዝቅያስ ግን ልቡ በትዕቢት ተሞልቶ ስለ ነበር፥ እግዚአብሔር ስላደረገለት ቸርነት ሁሉ ተገቢ ምስጋና አላቀረበም፤ ከዚህም የተነሣ በእርሱ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ሕዝብ ብርቱ ሥቃይ ደረሰባቸው። 26ይሁን እንጂ በመጨረሻ ሕዝቅያስና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በትሕትና ራሳቸውን ስላዋረዱ ሕዝቅያስ ከዚህ ዓለም በሞት እስከ ተለየበት ጊዜ ድረስ እግዚአብሔር ሕዝቡን አልቀጣም።
የሕዝቅያስ ብልጽግናና ገናናነት
27ንጉሥ ሕዝቅያስ እጅግ በለጸገ፤ ሕዝቡም ሁሉ አከበሩት፤ ወርቁን፥ ብሩን፥ የከበረ ዕንቊውን፥ ቅመማ ቅመሙን፥ ጋሻዎቹንና ሌሎቹንም ውድ የሆኑ ዕቃዎቹን የሚያኖርባቸው ዕቃ ግምጃ ቤቶችን ሠራ፤ 28በተጨማሪም ለእህሉ፥ ለወይን ጠጁና ለወይራ ዘይቱ ማኖሪያ የሚሆኑ የዕቃ ግምጃ ቤቶችን፥ ለቀንድ ከብቶቹ በረት፥ ለበጎቹም ጒረኖ ሠርቶ ነበር፤ 29ከዚህም ሁሉ ሌላ እግዚአብሔር ብዙ የቀንድ ከብትና የበግ መንጋ እንዲሁም ሌላ እጅግ የበዛ ሀብት ስለ ሰጠው፥ ብዙ ከተሞችን ሠራ፤ 30በላይ በኩል ያለውን የግዮንን ምንጭ መውጫ ገድቦ ውሃውን ወደ ምዕራብ፥ ወደ ዳዊት ከተማ፥ በቦይ እንዲወርድ ያደረገ ራሱ ሕዝቅያስ ነው፤ ይህ ሕዝቅያስ ሊሠራ ባቀደው ነገር ሁሉ የተሳካለት ሰው ነበር፤ 31ነገር ግን የባቢሎን መልእክተኞች በአገሪቱ ስለ ተደረገው አስደናቂ ነገር ሊጠይቁት ወደ እርሱ መጥተው በነበረ ጊዜ እግዚአብሔር በሕዝቅያስ ልብ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ለማወቅ ይፈትነው ዘንድ ተወው።
የሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ
(2ነገ. 20፥20-21)
32ንጉሥ ሕዝቅያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ ለእግዚአብሔርም የነበረው መንፈሳዊ ቅናት በአሞጽ ልጅ በነቢዩ ኢሳይያስ ራእይ እንዲሁም በይሁዳና በእስራኤል የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግበው ይገኛሉ። 33ሕዝቅያስ ሞተ፤ በላይኛው ክፍል በሚገኘውም በዳዊት ልጆች መካነ መቃብር ተቀበረ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብም ሁሉ ታላቅ የቀብር ሥነ ሥርዓት አደረጉለት፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ምናሴ ነገሠ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 32: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997