ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 34

34
የኢዮስያስ በይሁዳ መንገሥና ያደረገዉ ተሃድሶ
(2ነገ. 22፥1-223፥4-20)
1ኢዮስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ አንድ ዓመት ነገሠ። 2በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሄደ፤ ወደ ቀኝም፥ ወደ ግራም አላለም። 3በነገሠም በስምንተኛው ዓመት ገና ብላቴና ሳለ የአባቱን የዳዊትን አምላክ ይፈልግ ጀመር፤ በአሥራ ሁለተኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኮረብታው መስገጃዎችና ከማምለኪያ ዐፀዶቹ፥ ከተቀረጹትና ቀልጠው ከተሰሩት ምስሎች ያነጻ ጀመር። 4የበኣሊምንም መሠዊያዎች በፊቱ አፈረሱ፤ በላዩም የነበሩትን የፀሐዩን ምስሎች የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የተቀረጹትንና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች ሰባበረ፤ አደቀቃቸውም፤ ይሠዉላቸው በነበሩት ሰዎች መቃብርም ላይ በተናቸው። 5የካህናቶቻቸውንም አጥንት በመሠዊያቸው ላይ አቃጠለ፤ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አነጻ። 6የምናሴንና የኤፍሬምንም፥ የስምዖንና የንፍታሌምንም ከተሞች፥ በዙሪያቸውም ያለውን ቦታ እንዲሁ አነጻ። 7መሥዊያዎቹንም አፈረሰ፤ የማምለኪያ ዐፀዶቹንና የተቀረፁትን ምስሎች አደቀቀ፤ በእስራኤልም አገር ሁሉ የፀሐይን ምስሎች ሁሉ ቈራረጠ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ።
ኬልቅያስ የእግዚእብሔርን ሕግ መጽሐፍ እንዳገኘ
(2ነገ. 22፥3-20)
8በነገሠም በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ምድሪቱንና የእግዚአብሔርን ቤት ካነጻ በኋላ፥ የኤዜልያስ ልጅ ሳፋን፥ የከተማይቱም አለቃ መዕሤያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአክ የእግዚአብሔርን የአምላኩን ቤት ይጠግኑ ዘንድ ሰደዳቸው። 9ወደ ታላቁም ካህን ወደ ኬልቅያስ መጡ፤ ሌዋውያኑም በረኞች ከምናሴና ከኤፍሬም ከቀረውም ከእስራኤል ሁሉ፥ ከይሁዳና ከብንያም ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም ከሚኖሩት የሰበሰቡትን፥ ወደ እግዚእብሔር ቤት የቀረበውን ገንዘብ ሰጡት። 10የእግዚአብሔርንም ቤት በሚሠሩት ላይ ለተሾሙት ሰጡ፤ እነርሱም ይጠግኑና ያድሱ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቤት ለሚሠሩ ሠራተኞች ሰጡ። 11የይሁዳ ነገሥታት ላፈረሱት ቤት ሠረገሎች ያደርጉ ዘንድ፥ ለማጋጠሚያም እንጨት የተጠረበውንም ድንጋይ ይገዙ ዘንድ ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች ሰጡ።
12ሰዎቹም ሥራውን በመታመን አደረጉ፤ በእነርሱም ላይ የተሾሙት፥ ሥራውንም የሚሠሩት ሌዋውያን ከሜራሪ ልጆች ኢኤትና አብድዩ፥ ከቀዓትም ልጆች ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። ከሌዋውያንም ወገን በዜማ ዕቃ አዋቂዎች የነበሩ ሁሉ 13በተሸካሚዎችና ልዩ ልዩ ሥራ በሚሠሩ ላይ ተሾመው ነበር፤ ጸሐፊዎቹና አለቆቹ፥ በረኞቹም ከሌዋውያን ወገን ነበሩ።
14ወደ እግዚአብሔርም ቤት የቀረበውን ገንዘብ ባመጡ ጊዜ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ እጅ የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ። 15ኬልቅያስም ጸሐፊውን ሳፋንን “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቼአለሁ” ብሎ ተናገረው። ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው። 16ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ አመጣ፤ ለንጉሡም “ባሪያዎችህ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ሁሉ ያደርጋሉ፤ 17በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን ገንዘብ አፈሰሱ፤ በሥራውም ላይ ለተሾሙትና ለሠራተኞቹ ሰጡ” ብሎ አወራለት። 18ጸሐፊውም ሳፋን ለንጉሡ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጠኝ” ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው። 19ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። 20ንጉሡም ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ ዓብዶንን፥ ጸሐፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓሳያን 21“በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ፥ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ ተገኘው የመጽሐፍ ቃል ለእኔ፥ በእስራኤልና በይሁዳም ለቀሩት እግዚአብሔርን ጠይቁ” ብሎ አዘዛቸው።
22ኬልቅያስና እነዚያ ንጉሡ ያዘዛቸው ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ የልጅ ልጅ፥ ወደ ቲቁዋ ልጅ ወደ ሆነው ወደ ሴሌም ሚስት፥ ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርስዋም በኢየሩሳሌም በከተማይቱ በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ይህንንም ነገር ነገሩአት። 23እርስዋም አለቻቸው “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት’ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል 24‘እነሆ፥ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ የተጻፉትን ቃላት ሁሉ፥ ማለት ክፉ ነገርን፥ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ አመጣለሁ። 25በእጃቸው ሥራ ሁሉ ሊያስቈጡኝ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት ዐጥነዋልና፥ ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፤ አይጠፋምም።’ 26እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ስለ ሰማኸው ቃል ልብህ ገር ሆኖአልና፥ 27በፊቴም ራስህን አዋርደሃልና፥ በዚህም ስፍራና በሚኖሩበት ላይ ቃሌን በሰማህ ጊዜ ራስህን አዋርደሃልና፥ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ’ ይላል እግዚአብሔር። 28‘እነሆ፥ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ ዓይኖችህ አያዩም’።” ይህንም ለንጉሡ አወሩለት።
ኢዮስያስና ሕዝቡለእግዚአብሔር ለመታዘዝ ቃል ኪዳን እንደገቡ
(2ነገ. 23፥1-3)
29ንጉሡም ላከ፤ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰበ። 30ንጉሡም፥ የይሁዳም ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሹ ጀመሮ እስከ ታላቁ ድረስ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጡ፤ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ በጆሮአቸው አነበበ። 31ንጉሡም በስፍራው ቆሞ እግዚአብሔርን ተከትሎ እንዲሄድ፥ ትእዛዙንና ምስክሩን፥ ሥርዓቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ እንዲጠብቅ፥ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል እንዲያደርግ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረገ። 32በኢየሩሳሌምና በብንያምም የተገኙትን ሁሉ በዚህ ነገር አማለ፤ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት የአባቶቻቸው አምላክ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን እንዳዘዘ አደረጉ። 33ኢዮስያስም ከእስራኤል ልጆች ምድር ሁሉ ርኩሱን ሁሉ አስወገደ፤ በእስራኤልም የተገኙትን ሁሉ አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አደረገ። በዘመኑ ሁሉ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ከመከተል አልራቁም።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ