ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35

35
ኢዮስያስ የፋሲካን በዓል እንዳከበረ
(2ነገ. 23፥21-23)
1ኢዮስያስም ለእግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ፋሲካ አደረገ፤ በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አረዱ። 2ካህናቱንም በየሥርዓታቸው አቆመ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ያገለግሉ ዘንድ አጸናቸው። 3እስራኤልንም ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩት፥ ለእግዚአብሔርም ለተቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አለ “ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ አኑሩት፤ ከዚህም በኋላ በትከሻችሁ ላይ ሸክም አይሆንባችሁም፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ፤ 4የእስራኤልም ንጉሥ ዳዊትና ልጁም ሰሎሞን እንደ ጻፉት በየሰሞናችሁና በየአባቶቻችሁ ቤቶች ተዘጋጁ፤ 5እንደ ሕዝቡም ልጆች እንደ ወንድሞቻችሁ በየአባቶቻችሁ ቤቶች ሆናችሁ በመቅደሱ ቁሙ፤ የሌዋውያንም ነገድ በየወገናቸው እንደ ተከፈሉ እናንተም ተከፈሉ፤ ፋሲካውንም እረዱ፤ 6እናንተም ተቀደሱ፤ እግዚአብሔርም በሙሴ እጅ የተናገረውን ቃል ያደርጉ ዘንድ ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ።”
7ኢዮስያስም ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን በዚያ ለነበሩት ለሕዝቡ ልጆች ከመንጋው ሠላሳ ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶች፥ ሦስት ሺህም ወይፈኖች ሰጣቸው፤ እነዚህም ከንጉሡ ሀብት ነበሩ። 8መሳፍንቱም ለሕዝቡና ለካህናቱ ለሌዋውያኑም በፈቃዳቸው ሰጡ፤ የእግዚአብሔርም ቤት አለቆች፥ ኬልቂያስ፥ ዘካርያስ፥ ይሒኤል፥ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በጎችና ፍየሎች፥ ሦስት መቶም በሬዎች ለካህናቱ ሰጡ። 9የሌዋውያኑም አለቆች ኮናንያ፥ ወንድሞቹም ሸማያና ናትናኤል፥ ሐሸቢያ፥ ይዒኤል፥ ዮዛባት ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን አምስት ሺህ በጎችና ፍየሎች፥ አምስት መቶም በሬዎች ለሌዋውያን ሰጡ።
10አገልግሎቱም ተዘጋጀ፤ ካህናቱም በስፍራቸው፥ ሌዋውያኑም በየክፍላቸው እንደ ንጉሡ ትእዛዝ ቆሙ። 11ፋሲካውንም አረዱ፤ ሌዋውያኑም ቁርበቱን ገፈፉ፤ ካህናቱም ከእጃቸው የተቀበሉትን ደም ረጩ። 12በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ በየአባቶቻቸው ቤቶች ለሕዝቡ ልጆች እንዲሰጡ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ። እንዲሁም በበሬዎቹ አደረጉ። 13ፋሲካውንም እንደ ሥርዓቱ በእሳት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቍርባን በምንቸትና በሰታቴ፥ በድስትም ቀቀሉ፤ ለሕዝቡም ልጆች ሁሉ በፍጥነት አደረሱ። 14ከዚያም በኋላ ለራሳቸውና ለካህናቱ አዘጋጁ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን ለማቅረብ እስከ ሌሊት ድረስ ይሠሩ ነበርና ስለዚህ ሌዋውያን ለራሳቸውና ለአሮን ልጆች ለካህናቱ አዘጋጁ። 15የአሳፍም ልጆች መዘምራን እንደ ዳዊት፥ እንደ አሣፍ፥ እንደ ኤማን፥ የንጉሡም ባለ ራእይ እንደ ነበረው እንደ ኤዶታም ትእዛዝ በየስፍራቸው ነበሩ፤ በረኞቹም በሮቹን ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ ወንድሞቻቸውም ሌዋውያን ያዘጋጁላቸው ነበርና ከአገልግሎታቸው ይርቁ ዘንድ አያስፈልጋቸውም ነበር።
16እንደ ንጉሡም እንደ ኢዮስያስ ትእዛዝ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፥ ፋሲካውንም ያደርጉ ዘንድ የእግዚአብሔር አገልግሎት ሁሉ በዚያ ቀን ተዘጋጀ። 17የተገኙትም የእስራኤል ልጆች በዚያ ቀን ፋሲካውን፥ ሰባት ቀንም የቂጣ በዓልን አደረጉ። 18ከነቢዩ ከሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልተደረገም፤ ከእስራኤልም ነገሥታት ሁሉ ኢዮስያስና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ በዚያም የተገኙ የይሁዳና የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት እንዳደረጉት ያለ ፋሲካ ያደረገ የለም። 19ይህም ፋሲካ ኢዮስያስ በነገሠ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ተደረገ።
የኢዮስያስ ሽንፈትና ሞት
(2ነገ. 23፥28-30)
20ከዚህም ሁሉ በኋላ፥ ኢዮስያስም ቤተ መቅደሱን ካሰናዳ በኋላ፥ የግብጽ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ባለው በከርከሚሽ ላይ ይዋጋ ዘንድ ወጣ፤ ኢዮስያስም ሊጋጠመው ወጣ። 21እርሱም “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ! ከአንተ ጋር ምን አለኝ? በምዋጋበት በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም፤ እግዚአብሔርም እንድቸኵል አዝዞኛል፤ ከእኔ ጋር ያለው እግዚአብሔር እንዳያጠፋህ ይህን በእርሱ ላይ ከማድረግ ተመለስ” ብሎ መልእክተኞችን ላከበት። 22ኢዮስያስ ግን ይዋጋው ዘንድ ተጸናና እንጂ ፊቱን ከእርሱ አልመለሰም፤ በእግዚአብሔርም አፍ የተነገረውን የኒካዑን ቃል አልሰማም፥ በመጊዶም ሸለቆ ይዋጋ ዘንድ መጣ። 23ቀስተኞችም ንጉሡን ኢዮስያስን ወጉት፤ ንጉሡም ብላቴናዎቹን “አጥብቄ ቆስያለሁና ከሰልፉ ውስጥ አውጡኝ” አላቸው። 24ብላቴናዎቹም ከሠረገላው አውርደው ለእርሱ በነበረው በሁለተኛው ሠረገላ ውስጥ አስቀመጡት፤ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፤ እርሱም ሞተ፤ በአባቶቹም መቃብር ተቀበረ፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌምም ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱ። 25ኤርምያስም ለኢዮስያስ የልቅሶ ግጥም ገጠመለት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ሁሉ በልቅሶ ግጥማቸው ስለ ኢዮስያስ ይናገሩ ነበር፤ ይህም በእስራኤል ዘንድ ወግ ሆኖ በልቅሶ ግጥም ተጽፎአል። 26የቀረውም የኢዮስያስ ነገር፥ በእግዚአብሔርም ህግ እንደተጻፈ ያደረገው ቸርነት፥ 27የፊተኛውና የኋለኛውም ነገሩ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ