2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 34

34
ኢዮስያስ መንገሡ
1 # ኤር. 3፥6። ኢዮስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ አንድ ዓመት ነገሠ። 2በጌታም ፊት ቅን ነገር አደረገ፥ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሄደ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም። 3በነገሠም በስምንተኛው ዓመት ገና ብላቴና ሳለ የአባቱን የዳዊትን አምላክ ይፈልግ ጀመር፤ በዓሥራ ሁለተኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኮረብታው መስገጃዎችና ከማምለኪያ ዐፀዶቹ፥ ከተቀረፁትና ቀልጠው ከተሰሩት ምስሎች ያነጻ ጀመር። 4#2ነገ. 21፥3፤ 2ዜ.መ. 33፥3።የበኣሊምንም መሠዊያዎች በእርሱ ፊት አፈረሱ፤ በእነርሱም ላይ የነበሩትን የዕጣን መሠዊያዎቹን የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የተቀረፁትንና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች ሰባበረ፥ አደቀቃቸውም፥ ይሠዉላቸው በነበሩት ሰዎች መቃብርም ላይ በተናቸው። 5#1ነገ. 13፥2።የካህናቶቻቸውንም አጥንት በመሠዊያቸው ላይ አቃጠለ፤ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አነጻ። 6የምናሴንና የኤፍሬምንም የስምዖንና የንፍታሌምንም ከተሞች፥ በዙሪያቸውም ያለውን ቦታ እንዲሁ አነጻ። 7መሠዊያዎቹንም አፈረሰ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንና የተቀረፁትን ምስሎች አደቀቀ፥ በእስራኤልም አገር ሁሉ የዕጣን መሠዊያዎቹን ሁሉ ቈራረጠ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ።
የሕጉ መጽሐፍ መገኘቱ
8በነገሠም በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት ምድሪቱንና የጌታን ቤት ካነጻ በኋላ፥ የኤዜልያስ ልጅ ሳፋን፥ የከተማይቱም አለቃ መዕሤያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአክ የጌታን የአምላኩን ቤት እንዲጠግኑ ላካቸው። 9ወደ ታላቁም ካህን ወደ ኬልቅያስ መጡ፤ ሌዋውያኑም የደጆቹም ጠባቂዎች ከምናሴና ከኤፍሬም ከቀረውም ከእስራኤል ሁሉ፥ ከይሁዳና ከብንያም ሁሉ በኢየሩሳሌምም ከሚኖሩት የሰበሰቡትን፥ ወደ ጌታ ቤት ያመጡትን ገንዘብ ሰጡት። 10የጌታንም ቤት በሚሠሩት ላይ ለተሾሙት ሰጡ፤ በጌታም ቤት የሚሠሩት ሠራተኞች ቤቱን ለሚጠግኑና ለሚያድሱ ሠራተኞች ሰጡ። 11እነርሱም የይሁዳ ነገሥታት ላፈረሱት ቤት ሰረገሎች እንዲሠሩ፥ ለማጋጠሚያም እንጨት የተጠረበውንም ድንጋይ እንዲገዙ ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች ሰጡ።
12ሰዎቹም ሥራውን በታማኝነት ሠሩ፤ በእነርሱም ላይ የተሾሙት፥ ሥራውንም የሚሠሩት ሌዋውያን ከሜራሪ ልጆች ኢኤትና አብድዩ፥ ከቀዓትም ልጆች ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። ከሌዋውያንም ወገን በዜማ ዕቃ አዋቂዎች የነበሩ ሁሉ 13በተሸካሚዎችና ልዩ ልዩ ሥራ በሚሠሩ ላይ ተሾመው ነበር፤ ጸሐፊዎቹና አለቆቹም የደጁም ጠባቂዎች ከሌዋውያን ወገን ነበሩ። 14ወደ ጌታም ቤት የቀረበውን ገንዘብ ባመጡ ጊዜ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ እጅ የተሰጠውን የጌታን የሕግ መጽሐፍ አገኘ። 15ኬልቅያስም ጸሐፊውን ሳፋንን፦ “የሕጉን መጽሐፍ በጌታ ቤት አግኝቼአለሁ” ብሎ ተናገረው። ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው። 16ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ አመጣ፤ ለንጉሡም እንዲህ ብሎ አወራለት፦ “ባርያዎችህ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ሁሉ እያደረጉ ነው፤ 17በጌታም ቤት የተገኘውን ገንዘብ አፈሰሱ፥ በሥራውም ላይ ለተሾሙትና ለሠራተኞቹ ሰጡ።” 18ጸሐፊውም ሳፋን ለንጉሡ፦ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጠኝ” ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው። 19ንጉሡም የሕጉን ቃላት በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። 20ንጉሡም ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ ዓብዶንን፥ ጸሐፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓሳያን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ 21“በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለማድረግ አባቶቻችን የጌታን ቃል ስላልጠበቁ፥ በእኛ ላይ የነደደው የጌታ ቁጣ እጅግ ታላቅ ነውና ሄዳችሁ ስለ ተገኘው የመጽሐፍ ቃል ለእኔ በእስራኤልና በይሁዳም ለቀሩት ጌታን ጠይቁ።”
ነቢይቱ ሕልዳና ምክር እንድትሰጥ መጠየቅዋ
22ኬልቅያስና እነዚያ ንጉሡ የላካቸው ሰዎች ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቲቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርሷም በኢየሩሳሌም በከተማይቱ በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ይህንንም ነገር ነገሩአት። 23እርሷም እንዲህ አለቻቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ 24ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ የተጻፉትን ቃላት ሁሉ፥ ማለት ክፉ ነገርን፥ በዚህ ስፍራና በነዋሪዎችዋ ላይ አመጣለሁ። 25በእጃቸው ሥራ ሁሉ ሊያስቈጡኝ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት ዐጥነዋልና ቁጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፥ አይጠፋምም። 26ጌታን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፦ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለ ሰማኸው ቃላት፥ 27ልብህ ተጸጽቶአልና፥ በፊቴም ራስህን አዋርደሃልና፥ በዚህም ስፍራና በነዋሪዎችዋ ላይ የተናገርሁትን ቃላቴን በሰማህ ጊዜ ራስህን አዋርደሃልና፥ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ፥ ይላል ጌታ። 28እነሆ፥ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፥ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራና በሚኖሩባትም ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም።’ ” ይህንም ለንጉሡ አወሩለት።
ቃል ኪዳኑ መታደሱ
29ንጉሡም ላከ፥ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰበ። 30ንጉሡም፥ የይሁዳም ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሹ ጀመሮ እስከ ታላቁ ድረስ ወደ ጌታ ቤት ወጡ፤ በጌታም ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ እየሰሙት አነበበ። 31ንጉሡም በስፍራው ቆሞ ጌታን ተከትሎ እንዲሄድ፥ ትእዛዛቱንና ምስክሩን ሥርዓቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ እንዲጠብቅ፥ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል እንዲያደርግ በጌታ ፊት ቃል ኪዳን አደረገ። 32በኢየሩሳሌምና በብንያምም የተገኙትን ሁሉ በዚህ ነገር አማለ፤ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት የአባቶቻቸው አምላክ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን እንደሚያዝዘው አደረጉ። 33ኢዮስያስም ከእስራኤል ልጆች ምድር ሁሉ ርኩስ የሆነውን ነገር ሁሉ አስወገደ፥ በእስራኤልም የተገኙትን ሁሉ አምላካቸውን ጌታን እንዲያመልኩ አደረገ። በዘመኑ ሁሉ የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን ከመከተል አልራቁም።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ