2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 35

35
የፋሲካ በዓል መከበሩ
1ኢዮስያስም ለጌታ በኢየሩሳሌም ፋሲካን አከበረ፤ በመጀመሪያውም ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን መሥዋዕት አረዱ። 2ካህናቱንም በየሥርዓታቸው አቆመ፥ በጌታም ቤት እንዲያገለግሉ አጸናቸው። 3እስራኤልንም ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩት፥ ለጌታም ለተቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አለ፦ “ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ አኑሩት፤ ከዚህም በኋላ በትከሻችሁ ላይ ሸክም አይሆንባችሁም፤ አሁንም አምላካችሁን ጌታንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ፤ 4#2ዜ.መ. 8፥14።የእስራኤልም ንጉሥ ዳዊትና ልጁም ሰሎሞን እንደ ጻፉት በየሰሞናችሁና በየአባቶቻችሁ ቤቶች ራሳችሁን አዘጋጁ፤ 5እንደ ሕዝቡም እንደ ወንድሞቻችሁ በየአባቶቻችሁ ቤቶች ሆናችሁ በመቅደሱ ቁሙ፤ ለእያንዳንዱ ለተከፋፈሉትም ለአባቶች ቤቶች ሌዋውያን ይኑሯቸው፤ 6ፋሲካውንም እረዱ፥ እናንተም ተቀደሱ፥ ጌታም በሙሴ አንደበት የተናገረውን ቃል እንዲያደርጉ ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ።”
7ኢዮስያስም ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን በዚያ ለነበሩት ለሕዝቡ ልጆች ከመንጋው ሠላሳ ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶች፥ ሦስት ሺህም በሬዎች ሰጣቸው፤ እነዚህም ከንጉሡ ሀብት ነበሩ። 8መሳፍንቱም ለሕዝቡና ለካህናቱ ለሌዋውያኑም በፈቃዳቸው ሰጡ፤ የጌታም ቤት አለቆች፥ ኬልቂያስ፥ ዘካርያስ፥ ይሒኤል፥ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በጎችና ፍየሎች፥ ሦስት መቶም በሬዎች ለካህናቱ ሰጡ። 9የሌዋውያኑም አለቆች ኮናንያ፥ ወንድሞቹም ሸማያና ናትናኤል፥ ሐሸቢያ፥ ይዒኤል፥ ዮዛባት ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን አምስት ሺህ በጎችና ፍየሎች፥ አምስት መቶም በሬዎች ለሌዋውያን ሰጡ።
10አገልግሎቱም በተዘጋጀ ጊዜ ካህናቱም በስፍራቸው፥ ሌዋውያኑም በየክፍላቸው እንደ ንጉሡ ትእዛዝ ቆሙ። 11የፋሲካውንም መሥዋዕት አረዱ፥ ሌዋውያኑም ቁርበቱን ገፈፉ፥ ካህናቱም ከእጃቸው የተቀበሉትን ደም ረጩ። 12በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ለጌታ እንዲያቀርቡ በየአባቶቻቸው ቤቶች ለሕዝቡ ልጆች እንዲሰጡ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ። እንዲሁም በበሬዎቹ አደረጉ። 13#ዘፀ. 12፥8፤9።የፋሲካውንም መሥዋዕት እንደ ሥርዓቱ በእሳት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቁርባን በምንቸትና በሰታቴ በድስትም ቀቀሉ፥ ለሕዝቡም ሁሉ በፍጥነት አደረሱ። 14ከዚያም በኋላ ለራሳቸውና ለካህናቱ አዘጋጁ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን ለማቅረብ እስከ ሌሊት ድረስ ይሠሩ ነበርና ስለዚህ ሌዋውያን ለራሳቸውና ለአሮን ልጆች ለካህናቱ አዘጋጁ። 15#1ዜ.መ. 25፥1።የአሳፍም ልጆች መዘምራን እንደ ዳዊት፥ እንደ አሣፍም እንደ ኤማንም የንጉሡም ባለ ራእይ እንደነበረው እንደ ኤዶታም ትእዛዝ በየስፍራቸው ነበሩ፤ የደጁም ጠባቂዎች በሮቹን ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ ወንድሞቻቸውም ሌዋውያን ያዘጋጁላቸው ነበርና ከአገልግሎታቸው እንዲርቁ አያስፈልጋቸውም ነበር።
16እንደ ንጉሡም እንደ ኢዮስያስ ትእዛዝ በጌታ መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ ፋሲካውንም እንዲያከብሩ የጌታ አገልግሎት ሁሉ በዚያ ቀን ተዘጋጀ። 17#ዘፀ. 12፥1-20።የተገኙትም የእስራኤል ልጆች በዚያ ቀን ፋሲካውን፥ ሰባት ቀንም የቂጣ በዓልን አከበሩ። 18ከነቢዩ ከሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ከቶ ተከብሮ አያውቅም፤ ከእስራኤልም ነገሥታት ሁሉ ኢዮስያስና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ በዚያም የተገኙ የይሁዳና የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት እንዳከበሩት ያለ ፋሲካ ያከበረ የለም። 19ይህም ፋሲካ ኢዮስያስ በነገሠ በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት ተከበረ።
ንጉሥ ኒካዑ ማሸነፍና ንጉሥ ኢዮሲያስ መሞቱ
20ከዚህም ሁሉ በኋላ፥ ኢዮስያስም ቤተ መቅደሱን ባሰናዳ ጊዜ የግብጽ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ባለው በከርከሚሽ ላይ ለመዋጋት ወጣ፤ ኢዮስያስም ሊጋጠመው ሄደ። 21ኒካዑም እንዲህ ብሎ መልእክተኞችን ላከበት፦ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ! እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ውግያ የማደርገው በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም፤ ጌታም እንድቸኩል አዝዞኛል፤ ከእኔ ጋር ያለው ጌታ እንዳያጠፋህ ይህን በእርሱ ላይ ከማድረግ ተመለስ።” 22ኢዮስያስ ግን ማንነቱን ሸሽጎ ለመዋጋት ወጣ እንጂ ፊቱን ከእርሱ አልመለሰም፤ በጌታም አፍ የተነገረውን የኒካዑን ቃል አልሰማም፥ በመጊዶም ሸለቆ ለመዋጋት መጣ። 23ቀስተኞችም ንጉሡን ኢዮስያስን ወጉት፤ ንጉሡም አገልጋዮቹን፦ “ክፉኛ ቆስያለሁና ከሰልፉ ውስጥ አውጡኝ” አላቸው። 24አገልጋዮቹም ከሠረገላው አውርደው ለእርሱ በነበረው በሁለተኛው ሠረገላ ውስጥ አስቀመጡት፥ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፤ እርሱም ሞተ፥ በአባቶቹም መቃብር ተቀበረ፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌምም ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱ። 25ኤርምያስም ለኢዮስያስ የልቅሶ ግጥም ገጠመለት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ሁሉ በልቅሶ ግጥማቸው ስለ ኢዮስያስ ይናገሩ ነበር፤ ይህም በእስራኤል ዘንድ ወግ ሆኖ በልቅሶ ግጥም ተጽፎአል። 26የቀረውም የኢዮስያስ ነገር፥ በጌታም ሕግ እንደ ተጻፈ ያደረገው ቸርነት፥ 27የፊተኛውና የኋለኛውም ነገሩ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ