የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 33

33
ምናሴ መንገሡ
1ምናሴም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ኀምሳ አምስት ዓመት ነገሠ። 2#ኤር. 15፥4።ጌታም ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳወጣቸው እንደ አሕዛብ ያለ ርኩሰት በጌታ ፊት ክፉ ነገር አደረገ። 3አባቱም ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታውን መስገጃዎች መልሶ ሠራ፤ ለበኣሊምም መሠዊያ ሠራ፥ የማምለኪያ ዐፀዶችንም ተከለ፥ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገደ፥ አገለገላቸውም። 4#2ዜ.መ. 6፥6።ጌታም፦ “ስሜ በኢየሩሳሌም ለዘለዓለም ይኖራል” ባለው በጌታ ቤት መሠዊያዎችን ሠራ። 5በጌታም ቤት በሁለቱ አደባባዮች ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ። 6በሄኖምም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ልጆቹን በእሳት በማቃጠል እንደ መሥዋዕት አቀረበ፤ ሞራ ገላጭም ሆነ፥ አስማትም አደረገ፥ መተተኛም ነበረ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም ሰበሰበ፤ ጌታንም ለማስቈጣት በጌታ ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ። 7#1ነገ. 9፥3-5፤ 2ዜ.መ. 7፥12-18።ጌታ ለዳዊትና ለልጁ ለሰለሞን፦ “በዚህ ቤት ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘለዓለም አኖራለሁ፤” ባለበት በጌታ ቤት የሠራውን ጣዖት የቀረጸውን ምስል አቆመ። 8እንዲሁም ጌታ ለዳዊትና ለልጁ ለሰለሞን፦ “እኔ ያዘዝኋቸውን ሁሉ፥ በሙሴም በኩል የተሰጠውን ሕግና ሥርዓት ፍርድንም ሁሉ ቢያደርጉ ቢጠብቁም፥ ለአባቶቻችሁ ከሰጠኋት ምድር እስራኤል እንደገና እንዲሰደዱ አላደርግም” ብሎ ነበር። 9ምናሴም ጌታ ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ እንዲሠሩ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን አሳተ።
ምናሴ በንስሐ መመለሱ
10ጌታም ምናሴንና ሕዝቡን ተናገራቸው፤ ግን አልሰሙትም። 11ስለዚህም ጌታ የአሦርን ንጉሥ ሠራዊት አለቆች አመጣባቸው፤ ምናሴንም በዛንጅር#33፥11 በኩላብ፤ መንጠቆ መሳይ ዕቃ ነው። ያዙት፥ በሰንሰለትም አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት። 12በተጨነቀም ጊዜ አምላኩን ጌታን ፈለገ፥ በአባቶቹም አምላክ ፊት ራሱን እጅግ አዋረደ፥ 13ወደ እርሱም ጸለየ፤ እርሱም ተለመነው፥ ጸሎቱንም ሰማው፥ ወደ መንግሥቱም ወደ ኢየሩሳሌም መለሰው፤ ምናሴም እርሱ ጌታ አምላክ እንደሆነ አወቀ።
14ከዚህ በኋላ በዳዊት ከተማ በስተ ውጭው ከግዮን ምዕራብ በሸለቆው ውስጥ እስከ ዓሳ በር መግቢያ ድረስ ቅጥር ሠራ። በዖፌልም አዞረበት፥ እጅግም ከፍ አደረገው፤ በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ የጭፍራ አለቆችን አኖረ። 15እንግዶችንም አማልክትና ጣዖቱንም ከጌታ ቤት አራቀ፥ የጌታም ቤት ባለበት ተራራ ላይና በኢየሩሳሌም የሠራቸውን መሠዊያዎች ሁሉ ወስዶ ከከተማይቱ በስተ ውጭ ጣላቸው። 16የጌታንም መሠዊያ ደግሞ አደሰ፥ የአንድነትንና የምስጋናንም መሥዋዕት ሠዋበት፤ ይሁዳም የእስራኤልን አምላክ ጌታን እንዲያገለግሉ አዘዘ። 17ሕዝቡ ግን ገና በኮረብታው መስገጃዎች ይሠዋ ነበር፤ ቢሆንም ግን እንዲህ የሚያደርገው ለአምላኩ ለጌታ ብቻ ነበረ።
ምናሴ መሞቱ
18የምናሴም የቀረው ነገር፥ ወደ አምላኩም የጸለየው ጸሎት፥ በእስራኤልም አምላክ በጌታ ስም የነገሩት የነቢያት ቃላት፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። 19ደግሞም ጸሎቱ፥ ጌታም እንደ ተለመነው፥ ኃጢአቱና መተላለፉ ሁሉ፥ ራሱንም ሳያዋርድ የኮረብታው መስገጃዎችን የሠራበት የማምለኪያ ዐፀዱንና የተቀረጹትንም ምስሎች የተከለበት ስፍራ፥ እነሆ፥ በባለ ራእዮቹ ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 20ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቤቱም ቀበሩት፤ ልጁም አሞጽ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
አሞጽ መንገሡና መሞቱ
21አሞጽ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ ሁለት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሁለት ዓመት ነገሠ። 22አባቱም ምናሴ እንዳደረገ በጌታ ፊት ክፉ አደረገ፤ አሞጽም አባቱ ምናሴ ለሠራቸው ለተቀረጹት ምስሎች ሁሉ ሠዋ፥ አገለገላቸውም። 23አባቱም ምናሴ በጌታ ፊት ራሱን እንዳዋረደ እንዲሁ እርሱ ራሱን አላዋረደም፤ ነገር ግን አሞጽ መተላለፉን እጅግ አበዛ። 24ባርያዎቹም አሤሩበት፥ በቤቱም ውስጥ ሳለ ገደሉት። 25የአገሩ ሕዝብ ግን በንጉሡ በአሞጽ ላይ ያሤሩበትን ሁሉ ገደሉ፤ የአገሩም ሕዝብ ልጁን ኢዮስያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ