የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ነገሥት 8:1-21

1 ነገሥት 8:1-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሰሎ​ሞ​ንም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቤትና የራ​ሱን ቤተ መን​ግ​ሥት ሠርቶ ከፈ​ጸመ ከሃያ ዓመት በኋላ ያን​ጊዜ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቃል ኪዳን ታቦት ከዳ​ዊት ከተማ ከጽ​ዮን ያወጡ ዘንድ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ሽማ​ግ​ሌ​ዎ​ችና የነ​ገድ አለ​ቆ​ችን ሁሉ፥ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ልጆች የአ​ባ​ቶ​ቻ​ቸ​ውን ቤቶች መሳ​ፍ​ንት ንጉሡ ሰሎ​ሞን በጽ​ዮን ሰበ​ሰ​ባ​ቸው። ይኸ​ውም አታ​ሚን በሚ​ባል በሰ​ባ​ተ​ኛው ወር ነበር። ካህ​ና​ቱም ታቦ​ቷን አነሡ፤ የም​ስ​ክ​ሩ​ንም ድን​ኳን፥ በድ​ን​ኳ​ኑም ውስጥ የነ​በ​ረ​ውን የተ​ቀ​ደ​ሰ​ውን ዕቃ ሁሉ አመጡ። ንጉ​ሡም ሰሎ​ሞን ከእ​ርሱ ጋር የተ​ሰ​በ​ሰቡ የእ​ስ​ራ​ኤል ማኅ​በር ሁሉ ከእ​ርሱ ጋር በታ​ቦቷ ፊት ሆነው፥ ከብ​ዛ​ታ​ቸው የተ​ነሣ የማ​ይ​ቈ​ጠ​ሩ​ት​ንና የማ​ይ​መ​ጠ​ኑ​ትን በጎ​ችና በሬ​ዎች ይሠዉ ነበር። ካህ​ና​ቱም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቃል ኪዳን ታቦት በቤቱ በቅ​ድ​ስተ ቅዱ​ሳን ውስጥ ከኪ​ሩ​ቤል ክንፍ በታች ወደ ነበ​ረው ወደ ስፍ​ራዋ አገቧት። ኪሩ​ቤ​ልም በታ​ቦቷ ስፍራ ላይ ክን​ፎ​ቻ​ቸ​ውን ዘር​ግ​ተው ነበር፤ ኪሩ​ቤ​ልም ታቦቷ​ንና የተ​ቀ​ደሱ ዕቃ​ዎ​ችን በስ​ተ​ላይ በኩል ሸፍ​ነው ነበር። መሎ​ጊ​ያ​ዎ​ቹም ረጃ​ጅ​ሞች ነበሩ፤ በቅ​ድ​ስተ ቅዱ​ሳኑ ፊት ከመ​ቅ​ደሱ ውስጥ ጫፎ​ቻ​ቸው ይታዩ ነበር፤ በውጭ ግን አይ​ታ​ዩም ነበር፤ በታ​ቦ​ቷም ውስጥ የእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ከግ​ብፅ ምድር በወጡ ጊዜ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ከእ​ነ​ርሱ ጋር ቃል ኪዳን ባደ​ረገ ጊዜ ሙሴ በኮ​ሬብ ካስ​ቀ​መ​ጣ​ቸው የቃል ኪዳን ጽላት ከሚ​ባ​ሉት ከሁ​ለቱ የድ​ን​ጋይ ጽላት በቀር ምንም አል​ነ​በ​ረ​ባ​ትም። ካህ​ና​ቱም ከመ​ቅ​ደሱ በወጡ ጊዜ ደመ​ናው የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቤት ሞላው። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ክብር ቤቱን ሞል​ቶት ነበ​ርና ካህ​ናቱ ከደ​መ​ናው የተ​ነሣ ለማ​ገ​ል​ገል ይቆሙ ዘንድ አል​ቻ​ሉም። ያን​ጊ​ዜም ሰሎ​ሞን እን​ዲህ አለ፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፦ በደ​መ​ናው ውስጥ እኖ​ራ​ለሁ ብሎ​አል፤ እኔም ለዘ​ለ​ዓ​ለም የም​ት​ኖ​ር​በ​ትን ማደ​ሪያ ቤት በእ​ው​ነት ሠራ​ሁ​ልህ።” ንጉ​ሡም ፊቱን ዘወር አድ​ርጎ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ጉባኤ ሁሉ መረ​ቃ​ቸው፤ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ጉባኤ ሁሉ ቆመው ነበር። እር​ሱም አለ፥ “ለአ​ባቴ ለዳ​ዊት በአፉ የተ​ና​ገረ፥ በእ​ጁም የፈ​ጸመ የእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይመ​ስ​ገን። ሕዝ​ቤን እስ​ራ​ኤ​ልን ከግ​ብፅ ካወ​ጣ​ሁ​በት ቀን ጀምሮ ስሜ በዚያ ይሆን ዘንድ በእ​ር​ስ​ዋም ቤት ይሠ​ራ​ልኝ ዘንድ፥ ከእ​ስ​ራ​ኤል ነገድ ሁሉ ከተ​ማን አል​መ​ረ​ጥ​ሁም፤ አሁን ግን ስሜ በዚያ ይሆን ዘንድ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌ​ምን መር​ጫ​ለሁ፤ በሕ​ዝ​ቤም በእ​ስ​ራ​ኤል ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ዳዊ​ትን መር​ጫ​ለሁ።” አባ​ቴም ዳዊት ለእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስም ቤት ይሠራ ዘንድ በልቡ አሰበ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም አባ​ቴን ዳዊ​ትን፥ “ለስሜ ቤት ትሠራ ዘንድ በል​ብህ አስ​በ​ሃ​ልና ይህን በል​ብህ ማሰ​ብህ መል​ካም አደ​ረ​ግህ። ነገር ግን ከወ​ገ​ብህ የሚ​ወ​ጣው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠ​ራል እንጂ ቤት የም​ት​ሠ​ራ​ልኝ አንተ አይ​ደ​ለ​ህም” አለው። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የተ​ና​ገ​ረ​ውን ቃል አጸና፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ተስፋ እንደ ሰጠ በአ​ባቴ በዳ​ዊት ፋንታ ተነ​ሣሁ፤ በእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ዙፋን ላይ ተቀ​መ​ጥሁ፤ ለእ​ስ​ራ​ኤ​ልም አም​ላክ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስም ቤት ሠራሁ። ከግ​ብ​ፅም ምድር ባወ​ጣ​ቸው ጊዜ ከአ​ባ​ቶ​ቻ​ችን ጋር ያደ​ረ​ገው የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል ኪዳን ላለ​ባት ታቦት ስፍ​ራን በዚያ አደ​ር​ግ​ሁ​ላት።

1 ነገሥት 8:1-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚያም ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ለማምጣት፣ የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የእስራኤልን ነገድ አለቆችና የእስራኤልን ጐሣዎች ሹማምት ሁሉ እርሱ ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ጠራቸው። በዓሉ በሚከበርበት ኤታኒም በተባለው በሰባተኛው ወር፣ የእስራኤል ወንዶች ሁሉ ንጉሥ ሰሎሞን ወዳለበት ተሰበሰቡ። የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በመጡ ጊዜም ካህናቱ ታቦቱን አነሡ፤ የእግዚአብሔርን ታቦት፣ የመገናኛውን ድንኳንና በውስጡ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ አመጡ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም ይህን ሁሉ ተሸከሙ። ንጉሥ ሰሎሞንና አብሮት በዚያ የተሰበሰበው መላው የእስራኤል ጉባኤም በታቦቱ ፊት በመሆን ስፍር ቍጥር የሌለው በግና በሬ ሠዋ። ከዚያም ካህናቱ የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት አምጥተው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ወዳለው ማደሪያው፣ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ በማስገባት ከኪሩቤል ክንፍ በታች አኖሩት። ኪሩቤልም ታቦቱ ባለበት ቦታ ላይ ክንፋቸውን ዘርግተው፣ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን ጋረዱ። መሎጊያዎቹ ከመርዘማቸው የተነሣ ጫፎቻቸው ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ካለው ከመቅደሱ ሆኖ ይታዩ ነበር፤ ከመቅደሱ ወዲያ ላለ ሰው ግን አይታዩም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ እዚያው ይገኛሉ። የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር በወጡ ጊዜ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ኪዳን በገባበት በኮሬብ፣ ሙሴ በታቦቱ ውስጥ ካስቀመጣቸው ሁለት የድንጋይ ጽላቶች በቀር በታቦቱ ውስጥ ምንም አልነበረም። ካህናቱ ከቤተ መቅደሱ በወጡ ጊዜ፣ ደመና የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሞላው። የእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ስለ ነበር፣ ካህናቱ በደመናው ምክንያት አገልግሎታቸውን ማከናወን አልቻሉም ነበር። ከዚያም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ጥቅጥቅ ባለ ደመና ውስጥ እንደሚኖር ተናግሯል፤ እነሆ፣ እኔም ለዘላለም የምትኖርበትን ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርቼልሃለሁ።” መላው የእስራኤል ጉባኤ በዚያ ቆሞ ሳለ፣ ንጉሡ ፊቱን ወደ እነርሱ መልሶ ጉባኤውን ባረከ። ከዚያም እንዲህ አለ፤ “ለአባቴ ለዳዊት በገዛ አፉ ተናግሮ የሰጠውን ተስፋ፣ እርሱ ራሱ በእጁ የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ እርሱም እንዲህ ብሎ ነበርና፤ ‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ዕለት አንሥቶ፣ ስሜ በዚያ እንዲጠራና ቤተ መቅደስ እንዲሠራበት ከመላው የእስራኤል ነገድ አንድም ከተማ አልመረጥሁም፤ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲመራ ግን ዳዊትን መረጥሁት።’ “አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልቡ ዐስቦ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ ‘ለስሜ ቤተ መቅደስ ለመሥራት አስበሃልና፣ ይህን በልብህ ማሰብህ መልካም ነው፤ ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱን የምትሠራው አንተ ሳትሆን፣ ከአንተ የሚወለደው ልጅህ ነው፤ አዎን ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራው እርሱ ነው።’ “እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ፈጽሟል፤ እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት፣ በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቻለሁ፤ በእስራኤል ዙፋን ተቀምጫለሁ፤ እንዲሁም ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ሠርቻለሁ። ከግብፅ ባወጣቸው ጊዜ ከአባቶቻችን ጋር የገባው የእግዚአብሔር ኪዳን በውስጡ ላለበት ታቦት መኖሪያ ስፍራ በዚያ አዘጋጅቻለሁ።”

1 ነገሥት 8:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ያወጡ ዘንድ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆችን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች የአባቶቻቸውን ቤቶች መሳፍንት፥ ንጉሡ ሰሎሞን ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰባቸው። የእስራኤልም ሰዎች ኤታኒም በሚባል በሰባተኛው ወር በበዓሉ ጊዜ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ተከማቹ። የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ፤ ካህናቱም ታቦቱን አነሡ። የእግዚአብሔርንም ታቦት፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ በድንኳኑም ውስጥ የነበረውን የተቀደሰውን ዕቃ ሁሉ አመጡ፤ እነዚህንም ሁሉ ካህናቱና ሌዋውያኑ አመጡ። ንጉሡም ሰሎሞን ከእርሱም ጋር የተሰበሰቡ የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ከእርሱ ጋር በታቦቱ ፊት ሆነው፥ ከብዛታቸው የተነሣ የማይቈጠሩትንና የማይመጠኑትን በጎችና በሬዎች ይሠዉ ነበር። ካህናቱም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት በቤቱ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች ወደ ነበረው ወደ ስፍራው አመጡት። ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ነበር፤ ኪሩቤልም ታቦቱንና መሎጊያዎቹን በስተላይ በኩል ሸፍነው ነበር። መሎጊያዎቹም ረጃጅሞች ነበሩ፤ በቅድስተ ቅዱሳን ፊት ከመቅደሱ ውስጥ ጫፎቻቸው ይታዩ ነበር፤ በውጭ ያለ ግን አያያቸውም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ። በታቦቱም ውስጥ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ፥ ሙሴ በኮሬብ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች በቀር ምንም አልነበረበትም። ካህናቱም ከመቅደሱ በመጡ ጊዜ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው። የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶ ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ ለማገልገል ይቆሙ ዘንድ አልቻሉም። ሰሎሞንም “እግዚአብሔር ‘በጨለማው ውስጥ እኖራለሁ፤’ ብሎአል፤ እኔም ለዘላለም የምትኖርበት ማደሪያ ቤት በእውነት ሠራሁልህ፤” አለ። ንጉሡም ፊቱን ዘወር አድርጎ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መረቀ፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ቆመው ነበር። እርሱም አለ “‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብጽ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ ስሜ በዚያ ይሆን ዘንድ፥ በእርስዋም ቤት ይሠራልኝ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከተማ አልመረጥሁም፤ አሁን ግን ስሜ በዚያ ይሆን ዘንድ ኢየሩሳሌምን መርጫለሁ፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ይሆን ዘንድ ዳዊትን መርጫለሁ፤’ ብሎ ለአባቴ ለዳዊት በአፉ የተናገረ፥ በእጁም የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። አባቴም ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ይሠራ ዘንድ በልቡ አሰበ። እግዚአብሔርም አባቴን ዳዊትን ‘ለስሜ ቤት ትሠራ ዘንድ በልብህ አስበሃልና ይህን በልብህ ማሰብህ መልካም አደረግህ። ነገር ግን ከወገብህ የሚወጣው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል እንጂ ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም፤’ አለው። እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል አጸና፤ እግዚአብሔርም ተስፋ እንደ ሰጠ በአባቴ በዳዊት ፋንታ ተነሣሁ፤ በእስራኤልም ዙፋን ላይ ተቀመጥሁ፤ ለእስራኤልም አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ሠራሁ። ከግብጽም ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ላለበት ታቦት ስፍራ በዚያ አደረግሁለት።”

1 ነገሥት 8:1-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የዳዊት ከተማ ከሆነችው ከጽዮን ለማምጣትና ወደ ቤተ መቅደሱ ለማስገባት የእስራኤል የነገድ መሪዎችና የጐሣ አለቆች ሁሉ እርሱ ወደሚገኝበት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ ጠራ፤ የእስራኤልም ወንዶች ሁሉ የዳስ በዓል በሚከበርበት ኢታኒም ተብሎ በሚጠራው በሰባተኛው ወር ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ተሰበሰቡ። መሪዎቹ ሁሉ በተሰበሰቡ ጊዜም ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አንሥተው ተሸክሙ። ወደ ቤተ መቅደስ አገቡት፤ እንዲሁም ሌዋውያንና ካህናት የእግዚአብሔር መገኛ ድንኳንና በድንኳኑም ውስጥ የነበሩትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ አምጥተው ወደ ቤተ መቅደስ አገቡ። ንጉሥ ሰሎሞንና መላው የእስራኤል ሕዝብ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ተሰበሰቡ፤ ከብዛቱም የተነሣ ሊቈጠር የማይቻል ብዙ በግና የቀንድ ከብት መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። ከዚህም በኋላ ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ወደ ቤተ መቅደስ በማግባት በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ወደ ቦታው አምጥተው በኪሩቤል ክንፍ ሥር አኖሩት። የተዘረጉ የኪሩቤል ክንፎችም ታቦቱንና የታቦቱ መሸከሚያ መሎጊያዎችን ሸፍነው ነበር። መሎጊያዎቹ ረጃጅሞች ስለ ሆኑ ጫፎቻቸው በቤተ መቅደሱ ውስጥ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ለሚቆም ሰው ሁሉ በግልጥ ይታዩ ነበር፤ በሌላ አቅጣጫ የሚቆም ግን አያያቸውም፤ መሎጊያዎቹም እስከ ዛሬ በዚያው ይገኛሉ፤ የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር እንደ ወጡ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በገባ ጊዜ ሙሴ በሲና ተራራ በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ካኖራቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች በቀር በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ሌላ ምንም ነገር አልነበረም። ካህናቱ ከቤተ መቅደሱ እንደ ወጡ ቤተ መቅደሱ ድንገት በደመና ተሞላ፤ በደመናውም ውስጥ የነበረው የእግዚአብሔር ክብር ቤቱን ስለ ሞላ ካህናቱ ተመልሰው ለመግባትና አገልግሎታቸውን ለማከናወን አልቻሉም። በዚህ ጊዜ ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጸለየ፥ “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! አንተ በደመናው ጨለማ ውስጥ እኖራለሁ ብለሃል፤ እነሆ አሁን ግርማ ሞገስ ያለው ቤተ መቅደስ ለአንተ ሠርቻለሁ፤ እርሱም አንተ ለዘለዓለም የምትኖርበት ቦታ ይሆናል።” በዚያ ቆመው ሳሉ፥ ንጉሥ ሰሎሞን ፊቱን ወደ እነርሱ መልሶ የእግዚአብሔር በረከት በእነርሱ ላይ እንዲወርድ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን! ለአባቴ ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን አጽንቶ ጠብቆአል፤ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፦ ‘ሕዝቤን ከግብጽ ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ የሚሠራበት በመላው እስራኤል ምንም ዐይነት ከተማ አልመረጥኩም፤ አሁን ግን በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን መርጬአለሁ።’ ” ቀጥሎም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን ለመሥራት ዐቅዶ ነበር፤ እግዚአብሔርም አባቴን ዳዊትን ‘ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ ትሠራ ዘንድ በልብህ ማሰብህ መልካም ነው። ነገር ግን እርሱን የሚሠራልኝ ልጅህ ነው እንጂ አንተ አይደለህም፤ ከአንተ የሚወለደው ልጅ ቤተ መቅደሴን ይሠራል’ አለው። “እነሆ እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቆአል፤ ስለዚህም እኔ በአባቴ እግር ተተክቼ የእስራኤል ንጉሥ ሆኜአለሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ቤተ መቅደስንም ሠርቼአለሁ፤ እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከቀድሞ አባቶቻችን ጋር ቃል ኪዳን የገባበት የድንጋይ ጽላት ለሚገኝበትም ታቦት ማኖሪያ የሚሆን ቦታ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አዘጋጅቼአለሁ።”

1 ነገሥት 8:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከዚህ በኋላ ሰሎሞን የዳዊት ከተማ ከሆነችው ከጽዮን የጌታን የቃል ኪዳን ታቦት ለማምጣት፥ ወደ ቤተ መቅደሱም ለማስገባት፥ የእስራኤል የነገድ መሪዎችና የጐሣ አለቆች ሁሉ እርሱ ወደሚገኝበት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ ጠራ። የእስራኤልም ወንዶች ሁሉ የዳስ በዓል በሚከበርበት ኢታኒም ተብሎ በሚጠራው በሰባተኛው ወር ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ተሰበሰቡ። መሪዎቹ ሁሉ በተሰበሰቡ ጊዜም ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አንሥተው ተሸክሙ። የጌታን ታቦት፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ እንዲሁም በድንኳኑም ውስጥ የነበሩትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ፥ ሌዋውያንና ካህናት አመጡ። ንጉሥ ሰሎሞንና በፊቱ የተሰበሰበው መላው የእስራኤል ሕዝብ፥ ከእርሱ ጋር በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ሆነው፥ ከብዛቱም የተነሣ የማይቆጠር ብዙ በግና የቀንድ ከብት መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር። ካህናቱም የጌታን የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ወደ ቤተ መቅደስ በማስገባት፥ በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች ወደነበረው ወደ ስፍራው አመጡት። ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ስለ ነበር ታቦቱንና የታቦቱ መሸከሚያ መሎጊያዎችን በኪሩቤል ተሸፍነው ነበር። መሎጊያዎቹ ረጃጅሞች ስለ ሆኑ ጫፎቻቸው በቤተ መቅደሱ ውስጥ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ይታይ ነበር፤ በውጭ በኩል ግን አይታዩም፤ እስከ ዛሬ ድረስም በዚያው ይገኛሉ። የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር እንደ ወጡ፥ ጌታ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በገባ ጊዜ፥ ሙሴ በኮሬብ ተራራ በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ካኖራቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች በቀር ሌላ ምንም ነገር አልነበረም። ካህናቱ ከቤተ መቅደሱ እንደ ወጡ ደመና የጌታን ቤት ሞላው። በደመናውም ውስጥ የነበረው የጌታ ክብር የጌታን ቤት ስለ ሞላው ካህናቱ ተመልሰው ለመግባትና አገልግሎታቸውን ለማከናወን አልቻሉም። በዚህ ጊዜ ሰሎሞን እንዲህ አለ፥ “ጌታ በደመናው ጨለማ ውስጥ እኖራለሁ ብሏል። እኔም ለዘለዓለም የምትኖርበት ማደሪያ ቤት በእውነት ሠራሁልህ አለ። እኔም አሁን ግርማ ሞገስ ያለው ማደሪያ ቤት ሠርቼልሀለሁ፤ ለዘለዓለም ማደሪያህ ቦታም ይሆናል።” ንጉሥ ሰሎሞንም የእስራኤል ጉባኤ በዚያ ቆመው ሳሉ፥ ወደ እነርሱ ፊቱን ዞር አድርጎ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ ባረከ። እንዲህም አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ ጌታ ይባረክ! ለአባቴ ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን በአፉ እንደ ተናገረ፥ በእጁም ፈጽሙአል፤ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፦ ‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብጽ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ፥ ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ የሚሠራበት በመላው እስራኤል ምንም ዓይነት ከተማ አልመረጥኩም፤ አሁን ግን በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን መርጫለሁ።’ “አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለጌታ ቤተ መቅደስን ለመሥራት ዐቅዶ ነበር። ጌታም አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፥ ‘ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ ለመስራት በልብህ ማሰብህ መልካም ነው። ነገር ግን ለስሜ ቤት የሚሠራው ከአንተ የሚወለደው ልጅ እንጂ አንተ አይደለህም’። “እነሆ ጌታ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቆአል፤ ስለዚህም እኔ በአባቴ ቦታ ተተክቼ፥ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀመጥኩ፤ ጌታም ቃል እንደገባው፥ ለእስራኤል አምላክ ለጌታ ለስሙ ቤት ሠራሁ። ከግብጽ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከቀድሞ አባቶቻችን ጋር ጌታ ያደረገው ቃል ኪዳን ላለበት ታቦት ማኖሪያ አዘጋጅቼአለሁ።”