1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 8
8
የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ቤተ መቅደስ መግባት
(2ዜ.መ. 5፥2—6፥2)
1 #
2ሳሙ. 6፥12-16፤ 1ዜ.መ. 15፥25-29። ከዚህ በኋላ ሰሎሞን የዳዊት ከተማ ከሆነችው ከጽዮን የጌታን የቃል ኪዳን ታቦት ለማምጣት፥ ወደ ቤተ መቅደሱም ለማስገባት፥ የእስራኤል የነገድ መሪዎችና የጐሣ አለቆች ሁሉ እርሱ ወደሚገኝበት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ ጠራ። 2#ዘሌ. 23፥34።የእስራኤልም ወንዶች ሁሉ የዳስ በዓል በሚከበርበት ኢታኒም ተብሎ በሚጠራው በሰባተኛው ወር ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ተሰበሰቡ። 3መሪዎቹ ሁሉ በተሰበሰቡ ጊዜም ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አንሥተው ተሸክሙ። 4የጌታን ታቦት፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ እንዲሁም በድንኳኑም ውስጥ የነበሩትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ፥ ሌዋውያንና ካህናት አመጡ። 5ንጉሥ ሰሎሞንና በፊቱ የተሰበሰበው መላው የእስራኤል ሕዝብ፥ ከእርሱ ጋር በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ሆነው፥ ከብዛቱም የተነሣ የማይቆጠር ብዙ በግና የቀንድ ከብት መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር። 6ካህናቱም የጌታን የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ወደ ቤተ መቅደስ በማስገባት፥ በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች ወደነበረው ወደ ስፍራው አመጡት። 7ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ስለ ነበር ታቦቱንና የታቦቱ መሸከሚያ መሎጊያዎችን#8፥7 ዋልቶች። በኪሩቤል ተሸፍነው ነበር። 8መሎጊያዎቹ ረጃጅሞች ስለ ሆኑ ጫፎቻቸው በቤተ መቅደሱ ውስጥ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ይታይ ነበር፤ በውጭ በኩል ግን አይታዩም፤ እስከ ዛሬ ድረስም በዚያው ይገኛሉ። 9#ዘዳ. 10፥5።የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር እንደ ወጡ፥ ጌታ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በገባ ጊዜ፥ ሙሴ በኮሬብ ተራራ በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ካኖራቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች በቀር ሌላ ምንም ነገር አልነበረም።
10 #
ዘፀ. 40፥34፤35። ካህናቱ ከቤተ መቅደሱ እንደ ወጡ ደመና የጌታን ቤት ሞላው። 11በደመናውም ውስጥ የነበረው የጌታ ክብር የጌታን ቤት ስለ ሞላው ካህናቱ ተመልሰው ለመግባትና አገልግሎታቸውን ለማከናወን አልቻሉም። 12#መዝ. 18፥11፤ 97፥2።በዚህ ጊዜ ሰሎሞን እንዲህ አለ፥ “ጌታ በደመናው ጨለማ ውስጥ እኖራለሁ ብሏል። 13እኔም ለዘለዓለም የምትኖርበት ማደሪያ ቤት በእውነት ሠራሁልህ አለ። እኔም አሁን ግርማ ሞገስ ያለው ማደሪያ ቤት ሠርቼልሀለሁ፤ ለዘለዓለም ማደሪያህ ቦታም ይሆናል።”
14ንጉሥ ሰሎሞንም የእስራኤል ጉባኤ በዚያ ቆመው ሳሉ፥ ወደ እነርሱ ፊቱን ዞር አድርጎ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ ባረከ። 15እንዲህም አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ ጌታ ይባረክ! ለአባቴ ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን በአፉ እንደ ተናገረ፥ በእጁም ፈጽሙአል፤ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፦ 16#2ሳሙ. 7፥4-11፤ 1ዜ.መ. 17፥3-10።‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብጽ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ፥ ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ የሚሠራበት በመላው እስራኤል ምንም ዓይነት ከተማ አልመረጥኩም፤ አሁን ግን በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን መርጫለሁ።’
17 #
2ሳሙ. 7፥1-3፤ 1ዜ.መ. 17፥1፤2። “አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለጌታ ቤተ መቅደስን ለመሥራት ዐቅዶ ነበር። 18ጌታም አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፥ ‘ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ ለመስራት በልብህ ማሰብህ መልካም ነው። 19#2ሳሙ. 7፥12፤13፤ 1ዜ.መ. 17፥11፤12።ነገር ግን ለስሜ ቤት የሚሠራው ከአንተ የሚወለደው ልጅ እንጂ አንተ አይደለህም’።
20“እነሆ ጌታ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቆአል፤ ስለዚህም እኔ በአባቴ ቦታ ተተክቼ፥ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀመጥኩ፤ ጌታም ቃል እንደገባው፥ ለእስራኤል አምላክ ለጌታ ለስሙ ቤት ሠራሁ። 21ከግብጽ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከቀድሞ አባቶቻችን ጋር ጌታ ያደረገው ቃል ኪዳን ላለበት ታቦት ማኖሪያ አዘጋጅቼአለሁ።”
ሰሎሞን ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው ጸሎት
(2ዜ.መ. 6፥12-42)
22ከዚያም ሰሎሞን የእስራኤል ሕዝብ ሁሉም በተገኙበት ተነሥቶ በጌታ መሠዊያ ፊት ለፊት ቆመ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘረጋ። 23እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ! በላይ በሰማይ በታችም በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፥ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ አገልጋዮችህ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፤ 24ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውንም የተስፋ ቃል የጠበቅህ፥ በአፍህ እንደተናገርከው ሁሉ እነሆ ዛሬ በእጅህ ፈጸምከው። 25#1ነገ. 2፥4።አሁንም የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ! ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት ‘አንተ በፊቴ ትሄድ እንደነበረው ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በፊቴም በቅንነት ቢመላለሱ ከዘርህ በእስራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚነግሥ ልጅ መቼም አላሳጣህም’ ስትል የተናገርከውን የተስፋ ቃል ፈጽም! 26አሁንም የእስራኤል አምላክ ሆይ! አገልጋይህ ለነበረው ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ሁሉ እንዲፈጸም አድርግ።
27 #
2ዜ.መ. 2፥6። “በውኑ እግዚአብሔር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ ሰማያት፥ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ሊይዝህ አይችልም፤ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ! 28አቤቱ ጌታ፥ አምላኬ ሆይ! ወደ አገልጋይህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፤ ዛሬም አገልጋይህ በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ። 29#ዘዳ. 12፥11።‘ስሜ ይጠራበታል’ ወዳልከው ስፍራ ወደዚህ ቤት ዐይኖችህ ቀንና ሌሊት ይመልከቱ፤ አገልጋይህም በዚህ ስፍራ የምጸልየውን ጸሎት ስማ። 30አገልጋይህና ሕዝብህ እስራኤል በዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በማደሪያህ በሰማይ ስማን፤ ሰምተህም ይቅር በለን።
31“አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢበድል፥ አለመበደሉን በመሐላ እንዲያረጋግጥ ሲጠየቅ፥ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት በሚገኘው መሠዊያ ፊት መሐላ ቢያደርግ፥ 32በሰማይ ሆነህ ስማ፥ አድርግም፥ ለአገልጋዮችህም ፍርድን ስጥ፤ በበደለኛውም ላይ ፍረድ፤ ስለአካሄዱም ቅጣው፤ ንጹሑንም ነጻ አውጣው፥ እንደ ጽድቁም ክፈለው።
33“ሕዝብህ እስራኤል አንተን ስለ በደሉ በጠላቶቻቸው ፊት ድል ቢመቱ፥ ነገር ግን ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ በዚህም ቤት ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥ 34አንተ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ በምርኮ የሚገኙትንም ሕዝብህን ኃጢአት ይቅር በማለት ለቀድሞ አባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር መልሳቸው።
35“አንተን በማሳዘናቸው ምክንያት ዝናብ እንዳይዘንብላቸው አድርገህ በምትቀጣቸው ጊዜ፥ በፈጸሙት በደል በመጸጸት ፊታቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ መልሰው በትሕትና ቢለምኑህ፥ 36አንተ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ በማሳየት የአገልጋዮችህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ርስት አድርገህ ለሕዝብህ በሰጠሃቸው ምድር ዝናብ እንዲዘንብ አድርግ።
37“በምድሪቱ ላይ ረሀብ ወይም ቸነፈር ቢመጣ፥ በውርጭ፥ በዋግና በአንበጣ ወይም በኩብኩባ መንጋ ቢትወረር፥ የሕዝብህም ጠላት የአገሩን ቀበሌዎች ከብቦ ቢያስጨንቃቸው፥ መቅሠፍትና ደዌ ሁሉ ቢሆን፥ 38ልብን የሚያሸብር መራር ኀዘን ደርሶባቸው፥ ከማንም ሰው ወይም ከሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ቤተ መቅደስ እጃቸውን በመዘርጋት በሚጸልዩበት ጊዜ፥ 39በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ በደላቸውን ይቅር በል፤ እርዳቸው፤ በሰው ልብና አእምሮ ያለውን ሐሳብ ሁሉ መርምረህ የምታውቅ አንተ ብቻ ነህ፤ ስለዚህ ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የሚገባውን ዋጋ ስጠው። 40በዚህም ዓይነት ሕዝብህ ለቀድሞ አባቶቻችን ርስት አድርገህ በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ለአንተ ታዛዦች እንዲሆኑና እንዲያከብሩህ አድርግ።
41“ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ፥ ግን ከስምህ ታላቅነት የተነሣ ከሩቅ የመጣ የባዕድ አገር ሰው ቢኖር፥ 42ሰዎች ከሩቅ የሚመጡት ስለ ታላቁ ስምህ፥ ስለ ጠንካራዪቱ እጅህ፥ ስለ ተዘረጋችው ክንድህ ሰምተው ነውና፤ እንግዳው መጥቶ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢጸልይ፥ 43አንተ ጸሎቱን ስማ፤ ሕዝብህ እስራኤላውያን እንደሚያደርጉት በመላው ዓለም የሚኖሩ ሕዝቦች አንተን በማወቅ እንዲታዘዙህና እንዲያከብሩህ አድርግ፤ በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ የዚህን ሰው ጸሎት ስማ፤ እንድታደርግለት የሚለምንህንም ሁሉ ፈጽምለት፤ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ይህ እኔ የሠራሁት ቤተ መቅደስ የአንተ ስም የሚጠራበት መሆኑን ያውቃሉ።
44“ጠላቶቻቸውን ለመውጋት እንዲዘምቱ ሕዝብህን በምታዝበት ጊዜ በየትኛውም ስፍራ ሆነው ወደዚህች ወደ መረጥኻት ከተማና እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው በሚጸልዩበት ጊዜ፥ 45በሰማይም ሆነህ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በመስማት ዓላማቸውን ደግፍ።
46“መቼም በደል የማይሠራ የለምና ሕዝብህ ኃጢአት በመሥራት አንተን ሲያሳዝኑህ፥ አንተም ተቆጥተህ ጠላቶቻቸው ድል እንዲነሡአቸውና ወደ ሌላ አገር ማርከው እንዲወስዱአቸው በምትፈቅድበት ጊዜ፥ ምንም እንኳ ያ አገር ሩቅ ቢሆን፥ 47ምርኮኞች ሆነው በሚኖሩባት በዚያች አገር ሳሉ ‘ኃጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ዐምፀናልም’ ብለው በመናዘዝ ተጸጽተው ንስሓ ቢገቡ፥ 48ማርከው በወሰዱአቸው በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸው በእውነትና በቅን መንፈስ ተጸጽተው ንስሓ በመግባት አንተ ለቀድሞ አባቶቻችን ወደ ሰጠሃቸው ወደዚህች ምድር፥ አንተም ወደ መረጥኻት ወደዚህች ከተማና እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ቢጸልዩ፥ 49በመኖሪያህ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን በመስማት ፍረድላቸው። 50ኃጢአታቸውንና አንተን ያሳዘኑበትን ዐመፅ ሁሉ ይቅር በል፤ ጠላቶቻቸውም እንዲራሩላቸው አድርግ፤ 51እነርሱ እኮ እንደ እቶን እሳት ከምታቃጥል ከግብጽ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህ ናቸው።
52“በጠሩህም ጊዜ ሁሉ ትሰማቸው ዘንድ ለአገልጋይህና ለሕዝብህ ልመና ዐይኖችህ የተገለጡ ይሁኑ። 53እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! የቀድሞ አባቶቻችንን ከግብጽ ምድር ባወጣህ ጊዜ ከዓለም ሕዝብ ሁሉ መካከል እስራኤልን የራስህ ሕዝብ እንዲሆን የመረጥከው መሆኑን በአገልጋይህ በሙሴ አማካይነት ተናግረሃል።”
የጸሎቱ መደምደሚያ
54ሰሎሞን ጸሎቱን ከፈጸመ በኋላ እጆቹን እንደ ዘረጋ ተንበርክኮ ከነበረበት መሠዊያ ፊት ተነሥቶ ቆመ። 55ድምፁንም ከፍ በማድረግ በዚያ ተሰብስቦ በነበረው ሕዝብ ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር በረከት እንዲወርድ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ 56#ዘዳ. 12፥10፤ ኢያ. 21፥44፤45።“በገባው የተስፋ ቃል መሠረት ለሕዝቡ ሰላምን የሰጠ እግዚአብሔር ይመስገን፤ በአገልጋዩ በሙሴ አማካይነት ከሰጠውም መልካም ተስፋ ምንም የቀረ የለም። 57አምላካችን እግዚአብሔር ከቀድሞ አባቶቻችን ጋር እንደ ነበረ ሁሉ ከእኛ ጋርም ይኑር፤ ምንጊዜም፤ አይተወንም፤ አይጥለንም፤ 58ለቀድሞ አባቶቻችን የሰጠውን ትእዛዞች፥ ደንቦችና ሥርዓቶችን በመጠበቅ እንደ እርሱ ፈቃድ መኖር እንድንችል ለእርሱ ታዛዦች እንድንሆን ያድርገን። 59የእኔ ያገልጋዩና የሕዝቡ የእስራኤል የየዕለት ፍላጎት ይሟላ ዘንድ እነዚህ ለእግዚአብሔር ያቀረብኳቸው ልመናዎች ቀንና ሌሊት ወደ እግዚአብሔር አምላክ ይቅረቡ። 60በዚህ ዓይነት የዓለም ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ መሆኑንና ያለ እርሱም ሌላ አምላክ አለመኖሩን ያውቃሉ፤ 61በዛሬው ቀን እንዳደረጋችሁት በድንጋጌው ትኖሩና ትእዛዞቹንም ታከብሩ ዘንድ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ታማኞች ሁኑ።”
የቤተ መቅደሱ መመረቅ
(2ዜ.መ. 7፥4-10)
62ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞንና ከእርሱ ጋር እስራኤላውያን ሁሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ። 63ሰሎሞንም ኻያ ሁለት ሺህ የቀንድ ከብቶችንና አንድ መቶ ኻያ ሺህ በጎችን የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ በዚህም ዓይነት ንጉሥ ሰሎሞንና እስራኤላውያን ሁሉ ቤተ መቅደሱ ለእግዚአብሔር የተለየ እንዲሆን አደረጉ። 64እንዲሁም በዚያኑ ቀን ከቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ያለውን አደባባይ መካከለኛ ክፍል ለእግዚአብሔር የተለየ እንዲሆን አደረገ፤ ቀጥሎም በሙሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህል ቁርባንና የኅብረት መሥዋዕት፥ የእንስሶች ስብ ሁሉ ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት ከነሐስ የተሠራው መሠዊያ ይህን ሁሉ መሥዋዕት መያዝ ስለማይችል ነው።
65በዚያም በቤተ መቅደሱ ሰሎሞንና የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ሰባት ቀን ሙሉ የዳስ በዓል አክብረው ሰነበቱ፤ በስተ ሰሜን ከሐማት መተላለፊያ አንሥቶ በስተ ደቡብ እስከ ግብጽ ድንበር ድረስ ካለው ምድር ሁሉ የመጣው ሕዝብ እጅግ ብዙ ነበር። 66በሚቀጥለውም ቀን ሰሎሞን ሕዝቡን ሁሉ አሰናበተ፤ ሁሉም ሰሎሞንን መረቁ፤ እግዚአብሔር ለአገልጋዩ ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ስለ አደረገው በጎ ነገር ሁሉ ደስ ብሎአቸው ወደየቤታቸው ሄዱ።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 8: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ