1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 9
9
እግዚአብሔር ለሰሎሞን እንደገና ተገለጠለት
(2ዜ.መ. 7፥11-22)
1ንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን፥ ቤተ መንግሥቱንና ሊሠራው የፈለገውን ሌላውንም ሁሉ ከፈጸመ በኋላ፥ 2#1ነገ. 3፥5፤ 2ዜ.መ. 1፥7።እግዚአብሔር ከዚህ በፊት በገባዖን እንደ ተገለጠለት አሁንም እንደገና ተገለጠለት። 3“በፊቴ ያቀረብከውን ጸሎትና ልመና ሰምቼአለሁ፤ እርሱም ለዘለዓለም ለስሜ መጠሪያ እንዲሆን የሠራኸውን ቤተ መቅደስ ቀድሼዋለሁ፤ ዘወትርም እጠብቀዋለሁ። 4አንተ ግን አባትህ ዳዊት እንዳደረገው በቅንነትና በታማኝነት እኔን ብታገለግል፥ የእኔን ሕግና ሥርዓት ብትጠብቅ፥ ያዘዝኩህንም ሁሉ ብትፈጽም፥ 5#1ነገ. 2፥4።ለአባትህ ለዳዊት ‘ከዘሮችህ በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚነግሥ ልጅ አላሳጣህም’ በማለት የሰጠሁትን የተስፋ ቃል በመጠበቅ፥ ዙፋንህ በእስራኤል ለዘለዓለም ጸንቶ እንዲኖር አደርጋለሁ። 6ነገር ግን አንተ ወይም ዘሮችህ እኔን መከተል ትታችሁ የሰጠኋችሁን ሕጎችና ትእዛዞች ባትፈጽሙና ባዕዳን አማልክትን ብታመልኩ፥ 7እስራኤላውያንን ከሰጠኋቸው ምድር ተነቃቅለው እንዲባረሩ አደርጋለሁ፤ ስሜ እንዲጠራበት የቀደስኩትንም ይህን ቤተ መቅደስ እተወዋለሁ፤ በየአገሩ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ እስራኤልን መሳለቂያና መዘባበቻ ያደርጓታል። 8#2ነገ. 25፥9፤ 2ዜ.መ. 36፥19።ይህ ከፍ ከፍ ብሎ የሚታየው ቤተ መቅደስ ፈርሶ የፍርስራሽ ክምር ይሆናል፤ በዚያ በኩል የሚያልፉ ሰዎች ይህን አይተው በመደንገጥ ‘እግዚአብሔር ይህን አገርና ይህን ቤተ መቅደስ ለምን እንዲህ አደረገ?’ በማለት ይሳለቁበታል። 9ራሳቸው የሚሰጡትም መልስ ‘የእስራኤል ሕዝብ የቀድሞ አባቶቻቸውን ከግብጽ ምድር ያወጣ ጌታ አምላካቸውን በመተዋቸው ምክንያት ነው፤ ከዚህም በቀር ለእግዚአብሔር የነበራቸውን ታማኝነት ትተው ሌሎችን አማልክት አመለኩ፤ ሰገዱላቸውም፤ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ የጥፋት መቅሠፍት ያመጣባቸውም ስለዚህ ነው’ የሚል ነው።”
ሰሎሞን ለኪራም የከፈለው ወሮታ
(2ዜ.መ. 8፥1-2)
10ሰሎሞን ቤተ መቅደሱንና ቤተ መንግሥቱን ለመሥራት የፈጀበት ጊዜ ኻያ ዓመት ነበር። 11የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለዚህ ሁሉ ሥራ ለሰሎሞን የሚያስፈልገውን የሊባኖስ ዛፍና ዝግባ ከብዙ ወርቅ ጋር ሰጥቶት ነበር፤ ሥራውም ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ ሰሎሞን በገሊላ ምድር የሚገኙትን ኻያ ታናናሽ ከተሞችን ለኪራም ሰጠው። 12ኪራምም ሄዶ ከተሞቹን አየ፤ ነገር ግን ደስ አላሰኙትም። 13ሰሎሞንን “ወንድሜ ሆይ! የሰጠኸኝ ከተሞች ለካ እነዚህ ናቸውን?” አለው፤ በዚህ ምክንያት እስከ ዛሬ ድረስ ያ አካባቢ በሙሉ ካቡል እየተባለ ይጠራል። 14ኪራም ለሰሎሞን የላከለት ወርቅ አራት ሺህ ኪሎ ግራም ያኽል የሚመዝን ነበር።
ሰሎሞን ያከናወናቸው ሌሎች ሥራዎች
(2ዜ.መ. 8፥3-18)
15ለሰሎሞን ቤተ መቅደሱን፥ ቤተ መንግሥቱን፥ የኢየሩሳሌምን ቅጽር የሠሩለትና ከከተማይቱም በስተ ምሥራቅ በኩል ያለውን ሚሎ ተብሎ የሚጠራውን ጐድጓዳ ስፍራ ሞልተው ያስተካከሉለት የጉልበት ሥራ ለመሥራት የሚገደዱ ሠራተኞች ነበሩ፤ እንዲሁም ሐጾር፥ መጊዶና ጌዜር ተብለው የሚጠሩ ከተሞችንም እንዲሠሩለት አደረገ። 16ቀደም ሲል የግብጽ ንጉሥ በጌዜር ላይ አደጋ ጥሎ፥ ነዋሪዎችዋን ከነዓናውያንን ገድሎ ከተማይቱንም አቃጥሎ በቁጥጥሩ ሥር አድርጓት ነበር፤ ከዚያም በኋላ ሴት ልጁን ለሰሎሞን በዳረለት ጊዜ የጌዜርን ከተማ ማጫ አድርጎ ሰጣት። 17ሰሎሞንም ጌዜርንና የታችኛውን ቤትሖሮን እንደገና አሠራ። 18ባዕላት፥ በይሁዳ በረሓማ አገር የምትገኝ ታማር ተብለው የሚጠሩትን ከተሞች እንደገና ሠራ። 19እነዚህም የስንቅ ማከማቻዎች፥ ፈረሶችና ሠረገሎች የሚጠበቁባቸው፥ ከተሞችን ከተመ፤ ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም፥ በሊባኖስና በግዛቱ ሁሉ የሚፈልገውን ገነባ።
20ከእስራኤል ሕዝብ ያልሆኑትን ከአሞራውያን፥ ከኬጢያውያን፥ ከፌርዛውያን፥ ከኤው ያውንና ከኢያቡሳውያን ሕዝቦች ሁሉ የተረፉትን፥ 21እስራኤላውያን ዘሮቻቸውን ለማጥፋት ያልቻሉትንና በምድሪቱ የቀሩትን እነዚህን እስከ ዛሬ እንደሚደረገው ሁሉ፥ ሰሎሞን ለግዳጅ ሥራ መለመላቸው። 22ሰሎሞን ከእስራኤላውያን ወገን ማንንም ባርያ አድርጎ አላሠራም፤ እነርሱ ባለ ሥልጣኖች፥ ወታደሮች፥ የጦር መኰንኖች፥ የጦር አዛዦች፥ ሠረገላ ለሚነዱ ሁሉ ኀላፊዎችና ፈረሰኞች ሆነው ያገለግሉ ነበር።
23ሰሎሞን ለሚያከናውነው የሕንጻ ሥራ የጉልበት ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለተመደቡት ሰዎች አምስት መቶ ኀምሳ ኀላፊዎች ነበሩአቸው።
24የግብጽ ንጉሥ ልጅ የነበረችው ሚስቱ ከዳዊት ከተማ ራሱ ወዳሠራላት ቤተ መንግሥት ከተዘዋወረች በኋላ ሰሎሞን ከከተማይቱ በስተ ምሥራቅ የሚገኘውን ጐድጓዳ ስፍራ ተሞልቶ በመስተካከል እንዲሠራ አደረገ።
25 #
ዘፀ. 23፥17፤ 34፥23፤ ዘዳ. 16፥16። ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ባሠራው መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት በዓመት ሦስት ጊዜ ያቀርብ ነበር፤ ከዚህም ሁሉ ጋር ለእግዚአብሔር ዕጣን ያሳርግ ነበር፤ በዚህም ዓይነት የቤተ መቅደሱ ሥራ ተፈጸመ።
26እንዲሁም ንጉሥ ሰሎሞን በኤዶም ምድር በቀይ ባሕር ዳርቻ በምትገኘው በኤላት አጠገብ ባለችው በዔጽዮንጋብር መርከቦችን ሠራ። 27ንጉሥ ኪራምም ከሰሎሞን ሰዎች ጋር የሚያገለግሉ የሠለጠኑ መርከበኞችን ላከለት። 28እነርሱም በመርከብ ተጉዘው ወደ ኦፊር ምድር ከሄዱ በኋላ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ሲመለሱ ከዐሥራ አራት ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ወርቅ ይዘውለት መጡ።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 9: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ