የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 8:1-21

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 8:1-21 አማ05

ከዚህ በኋላ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የዳዊት ከተማ ከሆነችው ከጽዮን ለማምጣትና ወደ ቤተ መቅደሱ ለማስገባት የእስራኤል የነገድ መሪዎችና የጐሣ አለቆች ሁሉ እርሱ ወደሚገኝበት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ ጠራ፤ የእስራኤልም ወንዶች ሁሉ የዳስ በዓል በሚከበርበት ኢታኒም ተብሎ በሚጠራው በሰባተኛው ወር ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ተሰበሰቡ። መሪዎቹ ሁሉ በተሰበሰቡ ጊዜም ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አንሥተው ተሸክሙ። ወደ ቤተ መቅደስ አገቡት፤ እንዲሁም ሌዋውያንና ካህናት የእግዚአብሔር መገኛ ድንኳንና በድንኳኑም ውስጥ የነበሩትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ አምጥተው ወደ ቤተ መቅደስ አገቡ። ንጉሥ ሰሎሞንና መላው የእስራኤል ሕዝብ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ተሰበሰቡ፤ ከብዛቱም የተነሣ ሊቈጠር የማይቻል ብዙ በግና የቀንድ ከብት መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። ከዚህም በኋላ ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ወደ ቤተ መቅደስ በማግባት በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ወደ ቦታው አምጥተው በኪሩቤል ክንፍ ሥር አኖሩት። የተዘረጉ የኪሩቤል ክንፎችም ታቦቱንና የታቦቱ መሸከሚያ መሎጊያዎችን ሸፍነው ነበር። መሎጊያዎቹ ረጃጅሞች ስለ ሆኑ ጫፎቻቸው በቤተ መቅደሱ ውስጥ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ለሚቆም ሰው ሁሉ በግልጥ ይታዩ ነበር፤ በሌላ አቅጣጫ የሚቆም ግን አያያቸውም፤ መሎጊያዎቹም እስከ ዛሬ በዚያው ይገኛሉ፤ የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር እንደ ወጡ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በገባ ጊዜ ሙሴ በሲና ተራራ በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ካኖራቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች በቀር በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ሌላ ምንም ነገር አልነበረም። ካህናቱ ከቤተ መቅደሱ እንደ ወጡ ቤተ መቅደሱ ድንገት በደመና ተሞላ፤ በደመናውም ውስጥ የነበረው የእግዚአብሔር ክብር ቤቱን ስለ ሞላ ካህናቱ ተመልሰው ለመግባትና አገልግሎታቸውን ለማከናወን አልቻሉም። በዚህ ጊዜ ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጸለየ፥ “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! አንተ በደመናው ጨለማ ውስጥ እኖራለሁ ብለሃል፤ እነሆ አሁን ግርማ ሞገስ ያለው ቤተ መቅደስ ለአንተ ሠርቻለሁ፤ እርሱም አንተ ለዘለዓለም የምትኖርበት ቦታ ይሆናል።” በዚያ ቆመው ሳሉ፥ ንጉሥ ሰሎሞን ፊቱን ወደ እነርሱ መልሶ የእግዚአብሔር በረከት በእነርሱ ላይ እንዲወርድ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን! ለአባቴ ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን አጽንቶ ጠብቆአል፤ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፦ ‘ሕዝቤን ከግብጽ ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ የሚሠራበት በመላው እስራኤል ምንም ዐይነት ከተማ አልመረጥኩም፤ አሁን ግን በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን መርጬአለሁ።’ ” ቀጥሎም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን ለመሥራት ዐቅዶ ነበር፤ እግዚአብሔርም አባቴን ዳዊትን ‘ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ ትሠራ ዘንድ በልብህ ማሰብህ መልካም ነው። ነገር ግን እርሱን የሚሠራልኝ ልጅህ ነው እንጂ አንተ አይደለህም፤ ከአንተ የሚወለደው ልጅ ቤተ መቅደሴን ይሠራል’ አለው። “እነሆ እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቆአል፤ ስለዚህም እኔ በአባቴ እግር ተተክቼ የእስራኤል ንጉሥ ሆኜአለሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ቤተ መቅደስንም ሠርቼአለሁ፤ እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከቀድሞ አባቶቻችን ጋር ቃል ኪዳን የገባበት የድንጋይ ጽላት ለሚገኝበትም ታቦት ማኖሪያ የሚሆን ቦታ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አዘጋጅቼአለሁ።”