የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 8:1-21

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 8:1-21 አማ54

ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ያወጡ ዘንድ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆችን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች የአባቶቻቸውን ቤቶች መሳፍንት፥ ንጉሡ ሰሎሞን ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰባቸው። የእስራኤልም ሰዎች ኤታኒም በሚባል በሰባተኛው ወር በበዓሉ ጊዜ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ተከማቹ። የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ፤ ካህናቱም ታቦቱን አነሡ። የእግዚአብሔርንም ታቦት፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ በድንኳኑም ውስጥ የነበረውን የተቀደሰውን ዕቃ ሁሉ አመጡ፤ እነዚህንም ሁሉ ካህናቱና ሌዋውያኑ አመጡ። ንጉሡም ሰሎሞን ከእርሱም ጋር የተሰበሰቡ የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ከእርሱ ጋር በታቦቱ ፊት ሆነው፥ ከብዛታቸው የተነሣ የማይቈጠሩትንና የማይመጠኑትን በጎችና በሬዎች ይሠዉ ነበር። ካህናቱም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት በቤቱ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች ወደ ነበረው ወደ ስፍራው አመጡት። ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ነበር፤ ኪሩቤልም ታቦቱንና መሎጊያዎቹን በስተላይ በኩል ሸፍነው ነበር። መሎጊያዎቹም ረጃጅሞች ነበሩ፤ በቅድስተ ቅዱሳን ፊት ከመቅደሱ ውስጥ ጫፎቻቸው ይታዩ ነበር፤ በውጭ ያለ ግን አያያቸውም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ። በታቦቱም ውስጥ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ፥ ሙሴ በኮሬብ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች በቀር ምንም አልነበረበትም። ካህናቱም ከመቅደሱ በመጡ ጊዜ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው። የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶ ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ ለማገልገል ይቆሙ ዘንድ አልቻሉም። ሰሎሞንም “እግዚአብሔር ‘በጨለማው ውስጥ እኖራለሁ፤’ ብሎአል፤ እኔም ለዘላለም የምትኖርበት ማደሪያ ቤት በእውነት ሠራሁልህ፤” አለ። ንጉሡም ፊቱን ዘወር አድርጎ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መረቀ፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ቆመው ነበር። እርሱም አለ “‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብጽ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ ስሜ በዚያ ይሆን ዘንድ፥ በእርስዋም ቤት ይሠራልኝ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከተማ አልመረጥሁም፤ አሁን ግን ስሜ በዚያ ይሆን ዘንድ ኢየሩሳሌምን መርጫለሁ፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ይሆን ዘንድ ዳዊትን መርጫለሁ፤’ ብሎ ለአባቴ ለዳዊት በአፉ የተናገረ፥ በእጁም የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። አባቴም ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ይሠራ ዘንድ በልቡ አሰበ። እግዚአብሔርም አባቴን ዳዊትን ‘ለስሜ ቤት ትሠራ ዘንድ በልብህ አስበሃልና ይህን በልብህ ማሰብህ መልካም አደረግህ። ነገር ግን ከወገብህ የሚወጣው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል እንጂ ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም፤’ አለው። እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል አጸና፤ እግዚአብሔርም ተስፋ እንደ ሰጠ በአባቴ በዳዊት ፋንታ ተነሣሁ፤ በእስራኤልም ዙፋን ላይ ተቀመጥሁ፤ ለእስራኤልም አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ሠራሁ። ከግብጽም ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ላለበት ታቦት ስፍራ በዚያ አደረግሁለት።”