አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 8
8
የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ቤተ መቅደስ መግባት
(2ዜ.መ. 5፥2—6፥2)
1ከዚህ በኋላ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የዳዊት ከተማ ከሆነችው ከጽዮን ለማምጣትና ወደ ቤተ መቅደሱ ለማስገባት የእስራኤል የነገድ መሪዎችና የጐሣ አለቆች ሁሉ እርሱ ወደሚገኝበት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ ጠራ፤ #2ሳሙ. 6፥12-16፤ 1ዜ.መ. 15፥25-29። 2የእስራኤልም ወንዶች ሁሉ የዳስ በዓል በሚከበርበት ኢታኒም ተብሎ በሚጠራው በሰባተኛው ወር ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ተሰበሰቡ። #ዘሌ. 23፥24። 3መሪዎቹ ሁሉ በተሰበሰቡ ጊዜም ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አንሥተው ተሸክሙ። 4ወደ ቤተ መቅደስ አገቡት፤ እንዲሁም ሌዋውያንና ካህናት የእግዚአብሔር መገኛ ድንኳንና በድንኳኑም ውስጥ የነበሩትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ አምጥተው ወደ ቤተ መቅደስ አገቡ። 5ንጉሥ ሰሎሞንና መላው የእስራኤል ሕዝብ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ተሰበሰቡ፤ ከብዛቱም የተነሣ ሊቈጠር የማይቻል ብዙ በግና የቀንድ ከብት መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። 6ከዚህም በኋላ ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ወደ ቤተ መቅደስ በማግባት በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ወደ ቦታው አምጥተው በኪሩቤል ክንፍ ሥር አኖሩት። 7የተዘረጉ የኪሩቤል ክንፎችም ታቦቱንና የታቦቱ መሸከሚያ መሎጊያዎችን ሸፍነው ነበር። 8መሎጊያዎቹ ረጃጅሞች ስለ ሆኑ ጫፎቻቸው በቤተ መቅደሱ ውስጥ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ለሚቆም ሰው ሁሉ በግልጥ ይታዩ ነበር፤ በሌላ አቅጣጫ የሚቆም ግን አያያቸውም፤ መሎጊያዎቹም እስከ ዛሬ በዚያው ይገኛሉ፤ 9የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር እንደ ወጡ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በገባ ጊዜ ሙሴ በሲና ተራራ በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ካኖራቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች በቀር በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ሌላ ምንም ነገር አልነበረም። #ዘዳ. 10፥5።
10ካህናቱ ከቤተ መቅደሱ እንደ ወጡ ቤተ መቅደሱ ድንገት በደመና ተሞላ፤ 11በደመናውም ውስጥ የነበረው የእግዚአብሔር ክብር ቤቱን ስለ ሞላ ካህናቱ ተመልሰው ለመግባትና አገልግሎታቸውን ለማከናወን አልቻሉም። #ዘፀ. 40፥34-35። 12በዚህ ጊዜ ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጸለየ፥
“እግዚአብሔር አምላክ ሆይ!
አንተ በደመናው ጨለማ ውስጥ እኖራለሁ ብለሃል፤ #መዝ. 18፥11፤ 97፥2።
13እነሆ አሁን ግርማ ሞገስ ያለው ቤተ መቅደስ ለአንተ ሠርቻለሁ፤
እርሱም አንተ ለዘለዓለም የምትኖርበት ቦታ ይሆናል።”
ሰሎሞን ለሕዝቡ የተናገረው ቃል
(2ዜ.መ. 6፥3-11)
14በዚያ ቆመው ሳሉ፥ ንጉሥ ሰሎሞን ፊቱን ወደ እነርሱ መልሶ የእግዚአብሔር በረከት በእነርሱ ላይ እንዲወርድ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ 15“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን! ለአባቴ ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን አጽንቶ ጠብቆአል፤ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፦ 16‘ሕዝቤን ከግብጽ ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ የሚሠራበት በመላው እስራኤል ምንም ዐይነት ከተማ አልመረጥኩም፤ አሁን ግን በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን መርጬአለሁ።’ ” #2ሳሙ. 7፥4-11፤ 1ዜ.መ. 17፥3-10።
17ቀጥሎም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን ለመሥራት ዐቅዶ ነበር፤ 18እግዚአብሔርም አባቴን ዳዊትን ‘ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ ትሠራ ዘንድ በልብህ ማሰብህ መልካም ነው። #2ሳሙ. 7፥1-3፤ 1ዜ.መ. 17፥1-2። 19ነገር ግን እርሱን የሚሠራልኝ ልጅህ ነው እንጂ አንተ አይደለህም፤ ከአንተ የሚወለደው ልጅ ቤተ መቅደሴን ይሠራል’ አለው። #2ሳሙ. 7፥12-13፤ 1ዜ.መ. 17፥11-12።
20“እነሆ እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቆአል፤ ስለዚህም እኔ በአባቴ እግር ተተክቼ የእስራኤል ንጉሥ ሆኜአለሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ቤተ መቅደስንም ሠርቼአለሁ፤ 21እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከቀድሞ አባቶቻችን ጋር ቃል ኪዳን የገባበት የድንጋይ ጽላት ለሚገኝበትም ታቦት ማኖሪያ የሚሆን ቦታ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አዘጋጅቼአለሁ።”
ሰሎሞን ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው ጸሎት
(2ዜ.መ. 6፥12-42)
22ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በሕዝቡ ፊት ተነሥቶ በመሠዊያው ፊት ለፊት ቆመ፤ እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ 23እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ለአገልጋዮቹ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅና ከልባቸው ታማኞች እስከ ሆኑ ድረስ ፍቅሩን የሚያጸና በላይ በሰማይ በታችም በምድር እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም! 24ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውንም የተስፋ ቃል አጽንተሃል፤ የተናገርከውም ቃል ሁሉ እነሆ ዛሬ ተፈጽሞአል፤ 25አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ለአባቴ ለዳዊት ‘አንተ ታደርግ በነበረው ዐይነት ልጆችህ ታዛዦች ቢሆኑና በፊቴም በቅንነት ቢመላለሱ ሁልጊዜ ከዘርህ በእስራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚነግሥ ልጅ አላሳጣህም’ ስትል የተናገርከውን የተስፋ ቃል ፈጽም! #1ነገ. 2፥4። 26አሁንም የእስራኤል አምላክ ሆይ! አገልጋይህ ለነበረው ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ሁሉ እንዲፈጸም አድርግ።
27“በውኑ እግዚአብሔር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ ሰማያት፥ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ሊይዝህ አይችልም፤ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ? #2ዜ.መ. 2፥6። 28ይሁን እንጂ፥ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! ወደ አገልጋይህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፤ ዛሬም አገልጋይህ በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ። 29ስሜ ይጠራበታል ወዳልከው ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቀንና ሌሊት ተመልከት፤ እኔም አገልጋይህ ወደዚህ ቤተ መቅደስ የምጸልየውን ጸሎት ስማ። #ዘዳ. 12፥11። 30ፊታችንን ወደዚህ ቤተ መቅደስ መልሰን በምንጸልይበት ጊዜ የእኔንና የሕዝብህን ጸሎት ስማ፤ ከመኖሪያህ ከሰማይ ሆነህ ስማን፤ ይቅርም በለን።
31“አንድ ሰው ባልንጀራውን መበደሉን የሚገልጥ ክስ ቀርቦበት በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ ወደሚገኘው መሠዊያ አምጥተውት ከበደል ንጹሕ መሆኑን በመሐላ በሚያረጋግጥበት ጊዜ፥ 32በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ለአገልጋዮችህም ፍርድን ስጥ፤ ይኸውም በደል የሠራው ሰው በጥፋቱ መጠን እንዲቀጣ፥ ንጹሑም ነጻ እንዲወጣ አድርግ።
33“ሕዝብህ እስራኤል በደል ሠርተው አንተን በማሳዘናቸው ምክንያት በጠላቶቻቸው ድል ሲሆኑ ተጸጽተውም ወደ አንተ በመመለስ ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢመጡና የአንተን ይቅርታ ለማግኘት ራሳቸውን ዝቅ አድርገው በትሕትና ቢለምኑህ፥ 34አንተ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ በምርኮ የሚገኙትንም ሕዝብህን ኃጢአት ይቅር በማለት ለቀድሞ አባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር መልሰህ አግባቸው።
35“ሕዝብህ በደል ሠርተው አንተን በማሳዘናቸው ምክንያት ዝናብ እንዳይዘንብላቸው አድርገህ በምትቀጣቸው ጊዜ፥ በፈጸሙት በደል በመጸጸት ፊታቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ መልሰው በትሕትና ቢለምኑህ፥ 36አንተ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን ስማ፤ የአገልጋዮችህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ቅን የሆነውንም ነገር ማድረግ ይችሉ ዘንድ አስተምራቸው፤ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሆይ፥ ለዘለዓለም ርስት አድርገህ ለሕዝብህ በሰጠሃቸው በዚህች ምድር ዝናብ እንዲዘንብ አድርግ።
37“በምድሪቱ ላይ ረሀብ ወይም ቸነፈር በሚመጣበት ጊዜ፥ እንዲሁም በውርጭ በዋግና በአንበጣ ወይ በኩብኩባ መንጋ በሚወድምበት ጊዜ፥ ወይም ጠላቶቻቸው በሕዝብ ላይ አደጋ በሚጥሉበት ጊዜ፥ ወይም በሕዝብህ ላይ ልዩ በሽታና ደዌ በሚደርስባቸው ጊዜ፥ 38ጸሎታቸውን ስማ፤ በሕዝብህ በእስራኤል መካከል ልብን የሚያሸብር መራር ሐዘን ደርሶባቸው እጃቸውን ወደዚህ ቤተ መቅደስ በመዘርጋት በሚጸልዩበት ጊዜ፥ 39ጸሎታቸውን ስማ፤ በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን በመስማት በደላቸውን ይቅር በላቸው፤ ርዳቸውም፤ በሰው ልብና አእምሮ ያለውን ሐሳብ ሁሉ መርምረህ የምታውቅ አንተ ብቻ ነህ፤ ስለዚህ ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የሚገባውን ዋጋ ስጠው፤ 40በዚህም ዐይነት ሕዝብህ ለቀድሞ አባቶቻችን ርስት አድርገህ በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ለአንተ ታዛዦች እንዲሆኑና እንዲያከብሩህ አድርግ።
41-42“በሩቅ አገር የሚኖር የውጪ አገር ሰው የስምህን ገናናነትና ለሕዝብህ ያደረግኸውን ድንቅ ነገር ሁሉ ሰምቶ፥ በዚህ ቤተ መቅደስ ሊያመልክህና ሊጸልይ ቢመጣ፥ 43አንተ ጸሎቱን ስማ፤ ሕዝብህ እስራኤላውያን እንደሚያደርጉት በመላው ዓለም የሚኖሩ ሕዝቦች አንተን በማወቅ እንዲታዘዙህና እንዲያከብሩህ አድርግ፥ በምትኖርበት በሰማይ ሆነህ የዚህን ሰው ጸሎት ስማ፤ እንድታደርግለት የሚለምንህንም ሁሉ ፈጽምለት፤ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ይህ እኔ የሠራሁት ቤተ መቅደስ የአንተ ስም የሚጠራበት መሆኑን ያውቃሉ።
44“ጠላቶቻቸውን ለመውጋት እንዲዘምቱ ሕዝብህን በምታዝበት ጊዜ በየትኛውም ስፍራ ሆነው ወደዚህች ወደ መረጥኻት ከተማና እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው በሚጸልዩበት ጊዜ፥ 45በሰማይም ሆነህ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በመስማት ዓላማቸውን ደግፍ።
46“መቼም በደል የማይሠራ የለምና ሕዝብህ ኃጢአት በመሥራት አንተን ሲያሳዝኑህ፥ አንተም ተቈጥተህ ጠላቶቻቸው ድል እንዲነሡአቸውና ወደ ሌላ አገር ማርከው እንዲወስዱአቸው በምትፈቅድበት ጊዜ፥ ምንም እንኳ ያ አገር ሩቅ ቢሆን፥ 47ምርኮኞች ሆነው በሚኖሩባት በዚያች አገር ሳሉ ‘ኃጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ዐምፀናልም’ ብለው በመናዘዝ ተጸጽተው ንስሓ ቢገቡ፥ 48ማርከው በወሰዱአቸው በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸው በእውነትና በቅን መንፈስ ተጸጽተው ንስሓ በመግባት አንተ ለቀድሞ አባቶቻችን ወደ ሰጠሃቸው ወደዚህች ምድር፥ አንተም ወደ መረጥኻት ወደዚህች ከተማና እኔ ለአንተ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ፊታቸውን መልሰው ቢጸልዩ፥ 49በመኖሪያህ በሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውን በመስማት ፍረድላቸው፤ 50ኃጢአታቸውንና አንተን ያሳዘኑበትን ዐመፅ ሁሉ ይቅር በል፤ ጠላቶቻቸውም እንዲራሩላቸው አድርግ፤ 51እነርሱ እኮ እንደ እቶን እሳት ከምታቃጥል ከግብጽ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህ ናቸው።
52“በጠሩህ ጊዜ ሁሉ ትሰማቸው ዘንድ ለአገልጋይህና ለሕዝብህ ልመና ዐይኖችህ የተገለጡ ይሁኑ። 53እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! የቀድሞ አባቶቻችንን ከግብጽ ምድር ባወጣህ ጊዜ ከዓለም ሕዝብ ሁሉ መካከል እስራኤልን የራስህ ሕዝብ እንዲሆን የመረጥከው መሆኑን በአገልጋይህ በሙሴ አማካይነት ተናግረሃል።”
የጸሎቱ መደምደሚያ
54ሰሎሞን ጸሎቱን ከፈጸመ በኋላ እጆቹን እንደ ዘረጋ ተንበርክኮ ከነበረበት መሠዊያ ፊት ተነሥቶ ቆመ። 55ድምፁንም ከፍ በማድረግ በዚያ ተሰብስቦ በነበረው ሕዝብ ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር በረከት እንዲወርድ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ 56“በገባው የተስፋ ቃል መሠረት ለሕዝቡ ሰላምን የሰጠ እግዚአብሔር ይመስገን፤ በአገልጋዩ በሙሴ አማካይነት ከሰጠውም መልካም ተስፋ ምንም የቀረ የለም። #ዘዳ. 12፥10፤ ኢያሱ 21፥44-45። 57አምላካችን እግዚአብሔር ከቀድሞ አባቶቻችን ጋር እንደ ነበረ ሁሉ ከእኛ ጋርም ይኑር፤ ምንጊዜም፤ አይተወንም፤ አይጥለንም፤ 58ለቀድሞ አባቶቻችን የሰጠውን ትእዛዞች፥ ደንቦችና ሥርዓቶችን በመጠበቅ እንደ እርሱ ፈቃድ መኖር እንድንችል ለእርሱ ታዛዦች እንድንሆን ያድርገን። 59የእኔ ያገልጋዩና የሕዝቡ የእስራኤል የየዕለት ፍላጎት ይሟላ ዘንድ እነዚህ ለእግዚአብሔር ያቀረብኳቸው ልመናዎች ቀንና ሌሊት ወደ እግዚአብሔር አምላክ ይቅረቡ። 60በዚህ ዐይነት የዓለም ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ መሆኑንና ያለ እርሱም ሌላ አምላክ አለመኖሩን ያውቃሉ፤ 61በዛሬው ቀን እንዳደረጋችሁት በድንጋጌው ትኖሩና ትእዛዞቹንም ታከብሩ ዘንድ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ታማኞች ሁኑ።”
የቤተ መቅደሱ መመረቅ
(2ዜ.መ. 7፥4-10)
62ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞንና ከእርሱ ጋር እስራኤላውያን ሁሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ፤ 63ሰሎሞንም ኻያ ሁለት ሺህ የቀንድ ከብቶችንና አንድ መቶ ኻያ ሺህ በጎችን የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ በዚህም ዐይነት ንጉሥ ሰሎሞንና እስራኤላውያን ሁሉ ቤተ መቅደሱ ለእግዚአብሔር የተለየ እንዲሆን አደረጉ። 64እንዲሁም በዚያኑ ቀን ከቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ያለውን አደባባይ መካከለኛ ክፍል ለእግዚአብሔር የተለየ እንዲሆን አደረገ፤ ቀጥሎም በሙሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባንና የኅብረት መሥዋዕት፥ የእንስሶች ስብ ሁሉ ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት ከነሐስ የተሠራው መሠዊያ ይህን ሁሉ መሥዋዕት መያዝ ስለማይችል ነው።
65በዚያም በቤተ መቅደሱ ሰሎሞንና የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ሰባት ቀን ሙሉ የዳስ በዓል አክብረው ሰነበቱ፤ በስተ ሰሜን ከሐማት መተላለፊያ አንሥቶ በስተ ደቡብ እስከ ግብጽ ድንበር ድረስ ካለው ምድር ሁሉ የመጣው ሕዝብ እጅግ ብዙ ነበር፤ 66በሚቀጥለው ቀን ሰሎሞን ሕዝቡን ሁሉ አሰናበተ፤ ሁሉም ሰሎሞንን መረቁ፤ እግዚአብሔር ለአገልጋዩ ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ስለ አደረገው በጎ ነገር ሁሉ ደስ ብሎአቸው ወደየቤታቸው ሄዱ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 8: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997