1 ቆሮንቶስ 9:13-27
1 ቆሮንቶስ 9:13-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የጣዖታቱ ካህናት የጣዖታቱን መባ እንደሚበሉ አታውቁምን? መሠዊያውን የሚያገለግሉም መሥዋዕቱን እንደሚካፈሉ አታውቁምን? ለቤተ እግዚአብሔር ሹሞች መተዳደሪያቸው የቤተ እግዚአብሔር መባ ነው። ጌታችንም እንዲሁ ወንጌልን ለሚያስተምሩ ሰዎች ለሕይወታቸው መተዳደሪያ በዚያው ወንጌልን በማስተማር ይሆን ዘንድ አዘዘ። እኔ ግን ይህንም ቢሆን አልፈቀድሁትም፤ ይህን የጻፍሁም ይህን እንዳገኝ ብዬ አይደለም፤ እኔ ግን ምስጋናዬ ከሚቀርብኝ ሞት ይሻለኛል። ወንጌልን ባስተምርም መመስገን አይገባኝም፤ ታዝዤ አድርጌዋለሁና፤ ወንጌልን ባላስተምር ደግሞ ወዮልኝ። ይህንስ በፈቃዴ አድርጌው ብሆን ዋጋዬን ባገኘሁ ነበር፤ በግድ ከሆነ ግን በተሰጠኝ መጋቢነት አገለገልሁ። እንግዲህ ዋጋዬ ምንድን ነው? ወንጌልን ባስተምርም በሹመቴ የማገኘው ሳይኖር ወንጌልን ያለ ዋጋ እንዳስተምር ባደርግ ነው። እኔ ከሁሉ ይልቅ ነጻ ስሆን ብዙዎችን ወደ ሃይማኖት እሰበስባቸው ዘንድ እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛሁ። አይሁድን እጠቅማቸው ዘንድ ለአይሁድ እንደ አይሁዳዊ ሆንሁላቸው፤ ከኦሪት በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ እኔ ራሴ ከኦሪት በታች ሳልሆን ከኦሪት በታች ላሉት ከኦሪት በታች እንዳለ ሰው ሆንሁላቸው። የእግዚአብሔርን ሕግ የዘነጋሁ ሳልሆን፥ በክርስቶስ ሕግም ሳለሁ ሕግ የሌላቸውን እጠቅማቸው ዘንድ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለው ሆንሁላቸው። ደካሞችንም እጠቅማቸው ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁላቸው፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶቹን አድን ዘንድ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ። በወንጌልም ትምህርት አንድነት ይኖረኝ ዘንድ ስለ ወንጌል ትምህርት ሁሉን አደርጋለሁ። በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሽቀዳደሙ ሁሉ እንደሚፋጠኑ አታውቁምን? ለቀደመው የሚደረግለት ዋጋ አለ፤ እንዲሁ እናንተም እንድታገኙ ፈጽማችሁ ሩጡ። የሚታገል ሁሉ በሁሉ ነገር ይታገሣል፤ እነርሱስ የሚጠፋውንና የሚያልፈውን የምስጋናቸውን ዋጋ አክሊል ያገኙ ዘንድ ይበረታሉ፤ እኛ ግን የማያልፈውን አክሊል ለማግኘት እንታገሣለን። እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፤ ነፋስንም እንደሚጐስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም። ነገር ግን ለሌላ ሳስተምር፥ እኔ ለራሴ የተናቅሁ እንዳልሆን ሰውነቴን አስጨንቃታለሁ፥ ሥጋዬንም አስገዛዋለሁ።
1 ቆሮንቶስ 9:13-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ምግባቸውን ከቤተ መቅደስ እንደሚያገኙ፣ በመሠዊያውም የሚያገለግሉ ከመሥዋዕቱ እንደሚካፈሉ አታውቁምን? እንደዚሁም ወንጌልን የሚሰብኩ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ከወንጌል እንዲቀበሉ ጌታ አዝዟል። እኔ ግን ከእነዚህ መብቶች በአንዱ እንኳ አልተጠቀምሁም፤ አሁንም ይህን የምጽፍላችሁ እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች ታደርጉልኛላችሁ በሚል ተስፋ አይደለም፤ ማንም ትምክሕቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና። ወንጌልን መስበኬ አያስመካኝም፤ የምሰብከው ግዴታዬ ስለ ሆነ ነው፤ ወንጌልን ባልሰብክ ግን ወዮልኝ! በፈቃደኝነት ብሰብክ ሽልማት አለኝ፤ በፈቃደኝነት ካልሆነ ግን፣ የምፈጽመው ተግባር የተጣለብኝን ዐደራ መወጣት ብቻ ይሆናል። ታዲያ ሽልማቴ ምንድን ነው? ሽልማቴማ ወንጌልን ስሰብክ በመብቴ ሳልጠቀም ወንጌልን ያለ ክፍያ መስበክ ነው። እኔ ነጻ ሰው ነኝ፤ የማንም ባሪያ አይደለሁም፤ ነገር ግን ብዙዎችን እመልስ ዘንድ ራሴን ለሰው ሁሉ ባሪያ አደርጋለሁ። አይሁድን እመልስ ዘንድ ከአይሁድ ጋራ እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፣ ከሕግ በታች ያሉትን እመልስ ዘንድ ከሕግ በታች እንዳሉት ሆንሁ። እኔ ራሴ ከእግዚአብሔር ሕግ ነጻ ያልሆንሁና፣ ለክርስቶስ ሕግ የምገዛ ብሆንም፣ ሕግ የሌላቸውን እመልስ ዘንድ፣ ሕግ እንደሌለው ሰው ሆንሁ። ደካሞችን እመልስ ዘንድ፣ ከደካሞች ጋራ እንደ ደካማ ሆንሁ። በሚቻለኝ ሁሉ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉም ጋራ ሁሉን ነገር ሆንሁ። ይህን ሁሉ የማደርገው፣ ከወንጌል በረከት እካፈል ዘንድ፣ ስለ ወንጌል ብዬ ነው። በሩጫ ውድድር የሚሮጡ ብዙዎች እንደ ሆኑ፣ ሽልማቱን የሚቀበለው ግን አንዱ ብቻ እንደ ሆነ አታውቁምን? ስለዚህ ሽልማቱን እንደሚቀበል ሰው ሩጡ። ለውድድር የሚዘጋጅ ማንኛውም ሰው በሁሉም ነገር ራሱን ይገዛል፤ እነርሱ ዐላፊ ጠፊ የሆነውን አክሊል ለማግኘት ይደክማሉ፤ እኛ ግን ለዘላለም የማይጠፋውን አክሊል ለማግኘት እንደክማለን። ስለዚህ እኔ ግብ እንደሌለው ሰው በከንቱ አልሮጥም፤ ደግሞም ነፋስን እንደሚጐስም ሰው እንዲያው አልታገልም፤ ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ እኔ ራሴ ውድቅ ሆኜ እንዳልቀር፣ ሰውነቴን እየጐሰምሁ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ።
1 ቆሮንቶስ 9:13-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በመቅደስ ነገር የሚያገለግሉ ከመቅደስ የሆነውን ነገርን እንዲመገቡ፥ በመሠዊያውም የሚጸኑ ከመሠዊያው እንዲካፈሉ አታውቁምን? እንዲሁ ደግሞ ወንጌልን የሚሰብኩ ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል። እኔ ግን ከእነዚህ ሁሉ ምንም አልተጠቀምሁም። እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፤ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና። ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም፤ ግድ ደርሶብኝ ነውና፤ ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ። ይህን በፈቃዴ ባደርገው ደመወዝ አለኝና፤ ያለ ፈቃዴ ግን ባደርገው መጋቢነት በአደራ ተሰጥቶኛል። እንግዲህ ደመወዜ ምንድር ነው? ወንጌልን እየሰበክሁ በወንጌል ካለኝ መብት በሙሉ እንዳልጠቀም ወንጌልን ያለ ዋጋ ብናገር ነው። ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንድጠቅም እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ። አይሁድንም እጠቅም ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ፥ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፥ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ፤ ሕግ የሌላቸውን እጠቅም ዘንድ፥ ያለ እግዚአብሔር ህግ ሳልኖር ነገር ግን በክርስቶስ ሕግ በታች ሳለሁ፥ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደ ሌለኝ ሆንሁ፤ ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ። በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ። በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ። የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፥ እኛ ግን የማይጠፋውን። ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፥ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ።
1 ቆሮንቶስ 9:13-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ምግባቸውን ከቤተ መቅደስ እንደሚያገኙና በመሠዊያው ላይ መሥዋዕት የሚያቀርቡና የሚያገለግሉ ከመሥዋዕት ተካፍለው እንደሚበሉ ታውቁ የለምን? እንዲሁም ደግሞ ወንጌልን የሚያስተምሩ ቀለባቸውን ከዚሁ ሥራቸው እንዲያገኙ ጌታ ደንግጎአል። እኔ ግን በእነዚህ መብቶች በአንዱም አልተጠቀምኩም፤ ይህንንም የጻፍኩት ይህ መብቴ ሳይከበርልኝ ለምን ቀረ? በማለት አይደለም። ሰው ትምክሕቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ይልቅ ብሞት ይሻለኛል። ወንጌልን ማስተማር ግዴታዬ ስለ ሆነ የምመካበት ነገር አይደለም፤ እንዲያውም ወንጌልን ሳላስተምር ብቀር ወዮልኝ! የወንጌልን ቃል ያለ ግዴታ በፈቃዴ ባበሥር የድካም ዋጋ ይኖረኛል፤ በግዴታ ባደርገው ግን በዐደራ የተሰጠኝን ኀላፊነት ፈጸምኩ እንጂ ሌላ ያደረግኹት ነገር አለ ማለት አይደለም። ታዲያ፥ የድካሜ ዋጋ ምንድን ነው? እንግዲህ የድካሜ ዋጋ ወንጌልን በማስተማሬ ያለኝን መብት ሳልጠቀምበት ወንጌልን የማስተማር ሥራዬን ያለ ደመወዝ በነጻ መፈጸም ነው። እኔ የማንም ባሪያ ሳልሆን ነጻ ሰው ነኝ፤ ይሁን እንጂ በተቻለኝ መጠን ብዙዎቹን በማዳን ለመጥቀም ብዬ የሁሉም ባሪያ ሆኜአለሁ። ከአይሁድ ጋር ስሆን አይሁድን ለማዳን እንደ አይሁዳዊ ሆንኩ፤ እኔ ከሕግ በታች ባልሆንም እንኳ ከሕግ በታች ያሉትን ለማዳን ስል ከሕግ በታች እንዳሉት ሰዎች ሆንኩ። እኔ የእግዚአብሔር ሕግ ያለኝና ከክርስቶስ ሕግ ሥር ብሆንም እንኳ ሕግ የሌላቸውን አሕዛብ ለማዳን ስል ሕግ እንደሌለው ሰው ሆንኩ። በእምነት ደካሞች የሆኑትን ለማዳን ስል እንደ ደካሞች ደካማ ሆንኩ፤ በተቻለ መጠን ጥቂቶችን ለማዳን ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር ሆንኩ። ይህን ሁሉ ማድረጌ የወንጌልን በረከት ለመካፈል ስለ ወንጌል ብዬ ነው። በሩጫ ውድድር ሁሉም እንደሚሮጡና ከእነርሱም አንዱ ብቻ ሽልማት እንደሚቀበል ታውቁ የለምን? ስለዚህ እናንተም ሽልማትን ለመቀበል ሩጡ። በሩጫ የሚወዳደሩ ሁሉ አድካሚ ልምምድ ያደርጋሉ፤ እነርሱ እንዲህ የሚደክሙት የሚጠፋውንና ጊዜያዊ የሆነውን አክሊል ለማግኘት ነው፤ እኛ ግን የምንደክመው የማይጠፋውንና ዘለዓለማዊ የሆነውን አክሊል ለማግኘት ነው። እኔ ግን ግብ እንደሌለው ሰው በከንቱ አልሮጥም፤ ነፋስን በቡጢ እንደሚመታ ሰው በከንቱ የምሰነዝር ሰው አይደለሁም። ስለዚህ ሌሎችን ወደ ውድድር ከጠራሁ በኋላ እኔ ራሴ ከውድድሩ ውጪ ሆኜ እንዳልገኝ ሰውነቴን እየተቈጣጠርኩ እንዲታዘዝልኝ አደርገዋለሁ።
1 ቆሮንቶስ 9:13-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በመቅደስ ነገር የሚያገለግሉ ከመቅደስ የሆነውን ነገርን እንዲመገቡ፥ በመሠዊያውም የሚጸኑ ከመሠዊያው እንዲካፈሉ አታውቁምን? እንዲሁ ደግሞ ወንጌልን የሚያበስሩ ከወንጌል ቀለባቸውን እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል። እኔ ግን ከእነዚህ በአንዱም ምንም አልተጠቀምሁም። እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፤ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛል። ወንጌልን ብሰብክ እንኳ ግዴታዬ ነውና የምመካበት የለኝም፤ ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ! ይህን በፈቃዴ ባደርገው ዋጋ አለኝና፤ ያለ ፈቃዴ ግን ባደርገው መጋቢነት በአደራ ተሰጥቶኛል። እንግዲህ ዋጋዬ ምንድነው? በወንጌል ካለኝ መብት በሙሉ ሳልጠቀምበት ወንጌልን እየሰበክሁ ወንጌልን ያለ ክፍያ ባስተምር ነው። ከሰው ሁሉ ነጻ የወጣሁ ስሆን፥ ብዙዎችን እንድጠቅም እንደ ባርያ ራሴን ለሁሉ አስገዛሁ። አይሁድንም ለመጥቀም ስል ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን መጥቀም እንድችል፥ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፥ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንኩ። ሕግ የሌላቸውን ለመጠቅም ስል፥ የእግዚአብሔር ህግ ሳይኖረኝ ቀርቶ ሳይሆን በክርስቶስ ሕግ ስር ሳለሁ፥ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለኝ ሆንኩ። ደካሞችን መጥቀም እንድችል ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንኩ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን ማዳን እንድችል፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ። በወንጌልም ተካፋይ እንድሆን፥ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ። በሩጫ መወዳደሪያ ስፍራ የሚሮጡት ሁሉ እንደሚሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ሽልማቱን ዋጋውን እንደሚቀበል አታውቁምን? ስለዚህ እናንተም እንድትቀበሉ ሩጡ። የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ራሱን መግዛት ይለማመዳል፤ እነርሱ ጠፊውን አክሊል፤ እኛ ግን የማይጠፋውን፥ ለማግኘት ነው። ስለዚህ እኔ በከንቱ እንደሚሮጥ እንዲሁ አልሮጥም፤ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የቀረሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ።