በመቅደስ ነገር የሚያገለግሉ ከመቅደስ የሆነውን ነገርን እንዲመገቡ፥ በመሠዊያውም የሚጸኑ ከመሠዊያው እንዲካፈሉ አታውቁምን? እንዲሁ ደግሞ ወንጌልን የሚያበስሩ ከወንጌል ቀለባቸውን እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል። እኔ ግን ከእነዚህ በአንዱም ምንም አልተጠቀምሁም። እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፤ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛል። ወንጌልን ብሰብክ እንኳ ግዴታዬ ነውና የምመካበት የለኝም፤ ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ! ይህን በፈቃዴ ባደርገው ዋጋ አለኝና፤ ያለ ፈቃዴ ግን ባደርገው መጋቢነት በአደራ ተሰጥቶኛል። እንግዲህ ዋጋዬ ምንድነው? በወንጌል ካለኝ መብት በሙሉ ሳልጠቀምበት ወንጌልን እየሰበክሁ ወንጌልን ያለ ክፍያ ባስተምር ነው። ከሰው ሁሉ ነጻ የወጣሁ ስሆን፥ ብዙዎችን እንድጠቅም እንደ ባርያ ራሴን ለሁሉ አስገዛሁ። አይሁድንም ለመጥቀም ስል ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን መጥቀም እንድችል፥ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፥ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንኩ። ሕግ የሌላቸውን ለመጠቅም ስል፥ የእግዚአብሔር ህግ ሳይኖረኝ ቀርቶ ሳይሆን በክርስቶስ ሕግ ስር ሳለሁ፥ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለኝ ሆንኩ። ደካሞችን መጥቀም እንድችል ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንኩ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን ማዳን እንድችል፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ። በወንጌልም ተካፋይ እንድሆን፥ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ። በሩጫ መወዳደሪያ ስፍራ የሚሮጡት ሁሉ እንደሚሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ሽልማቱን ዋጋውን እንደሚቀበል አታውቁምን? ስለዚህ እናንተም እንድትቀበሉ ሩጡ። የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ራሱን መግዛት ይለማመዳል፤ እነርሱ ጠፊውን አክሊል፤ እኛ ግን የማይጠፋውን፥ ለማግኘት ነው። ስለዚህ እኔ በከንቱ እንደሚሮጥ እንዲሁ አልሮጥም፤ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የቀረሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ።
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9 ያንብቡ
ያዳምጡ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9:13-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos