የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ቆሮንቶስ 9:13-27

1 ቆሮንቶስ 9:13-27 NASV

በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ምግባቸውን ከቤተ መቅደስ እንደሚያገኙ፣ በመሠዊያውም የሚያገለግሉ ከመሥዋዕቱ እንደሚካፈሉ አታውቁምን? እንደዚሁም ወንጌልን የሚሰብኩ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ከወንጌል እንዲቀበሉ ጌታ አዝዟል። እኔ ግን ከእነዚህ መብቶች በአንዱ እንኳ አልተጠቀምሁም፤ አሁንም ይህን የምጽፍላችሁ እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች ታደርጉልኛላችሁ በሚል ተስፋ አይደለም፤ ማንም ትምክሕቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና። ወንጌልን መስበኬ አያስመካኝም፤ የምሰብከው ግዴታዬ ስለ ሆነ ነው፤ ወንጌልን ባልሰብክ ግን ወዮልኝ! በፈቃደኝነት ብሰብክ ሽልማት አለኝ፤ በፈቃደኝነት ካልሆነ ግን፣ የምፈጽመው ተግባር የተጣለብኝን ዐደራ መወጣት ብቻ ይሆናል። ታዲያ ሽልማቴ ምንድን ነው? ሽልማቴማ ወንጌልን ስሰብክ በመብቴ ሳልጠቀም ወንጌልን ያለ ክፍያ መስበክ ነው። እኔ ነጻ ሰው ነኝ፤ የማንም ባሪያ አይደለሁም፤ ነገር ግን ብዙዎችን እመልስ ዘንድ ራሴን ለሰው ሁሉ ባሪያ አደርጋለሁ። አይሁድን እመልስ ዘንድ ከአይሁድ ጋራ እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፣ ከሕግ በታች ያሉትን እመልስ ዘንድ ከሕግ በታች እንዳሉት ሆንሁ። እኔ ራሴ ከእግዚአብሔር ሕግ ነጻ ያልሆንሁና፣ ለክርስቶስ ሕግ የምገዛ ብሆንም፣ ሕግ የሌላቸውን እመልስ ዘንድ፣ ሕግ እንደሌለው ሰው ሆንሁ። ደካሞችን እመልስ ዘንድ፣ ከደካሞች ጋራ እንደ ደካማ ሆንሁ። በሚቻለኝ ሁሉ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉም ጋራ ሁሉን ነገር ሆንሁ። ይህን ሁሉ የማደርገው፣ ከወንጌል በረከት እካፈል ዘንድ፣ ስለ ወንጌል ብዬ ነው። በሩጫ ውድድር የሚሮጡ ብዙዎች እንደ ሆኑ፣ ሽልማቱን የሚቀበለው ግን አንዱ ብቻ እንደ ሆነ አታውቁምን? ስለዚህ ሽልማቱን እንደሚቀበል ሰው ሩጡ። ለውድድር የሚዘጋጅ ማንኛውም ሰው በሁሉም ነገር ራሱን ይገዛል፤ እነርሱ ዐላፊ ጠፊ የሆነውን አክሊል ለማግኘት ይደክማሉ፤ እኛ ግን ለዘላለም የማይጠፋውን አክሊል ለማግኘት እንደክማለን። ስለዚህ እኔ ግብ እንደሌለው ሰው በከንቱ አልሮጥም፤ ደግሞም ነፋስን እንደሚጐስም ሰው እንዲያው አልታገልም፤ ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ እኔ ራሴ ውድቅ ሆኜ እንዳልቀር፣ ሰውነቴን እየጐሰምሁ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ።