አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል። ቀኝ ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሃልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና። ሚስቱን የሚፈታት ሁሉ የፍችዋን ጽሕፈት ይስጣት ተባለ። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል። ደግሞ ለቀደሙት፦ በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፥ አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው። ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ። ለሚለምንህ ስጥ፥ ከአንተም ይበደር ዘንድ ከሚወደው ፈቀቅ አትበል። ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ።
የማቴዎስ ወንጌል 5 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 5:27-48
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos