ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ ‘አታመንዝር!’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ‘ሴትን ተመልክቶ የተመኛት ሁሉ፥ ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመነዘረ’ እላችኋለሁ። የቀኝ ዐይንህ ለኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ አውጥተህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። ቀኝ እጅህ የኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ ቈርጠህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። “ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍችዋን ማስረጃ ይስጣት” ተብሏል። እኔ ግን “በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በቀር፥ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እንድታመነዝር ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል” እላችኋለሁ። ደግሞም ለቀደሙ ሰዎች “በሐሰት አትማሉ፤ ነገር ግን መሐላችሁን ለጌታ ፈጽሙ” የተባለውን ሰምታችኋል። እኔ ግን “በፍጹም አትማሉ” እላችኋለሁ። ሰማይ የእግዚአብሔር ዙፋን ስለ ሆነች፥ በሰማይም ቢሆን፥ ምድርም የጌታ እግር ማሳረፊያ ስለ ሆነች በምድርም አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ስለ ሆነች በኢየሩሳሌምም አትማሉ፤ ከጸጒርህ አንዲቱን እንኳ ነጭ ወይም ጥቊር ማድረግ ስለማትችል በራስህም ቢሆን አትማል። ስለዚህ ንግግራችሁ “አዎ” ከሆነ “አዎ፥” ወይም “አይደለም” ከሆነ “አይደለም” ይሁን። ከዚህ የተረፈ ቃል ግን ከሰይጣን ነው። “ ‘ዐይን ስለ ዐይን፥ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፤ ክፉ የሚያደርግባችሁን ሰው አትበቀሉት። ነገር ግን ቀኝ ጒንጭህን ለሚመታህ፥ ግራ ጒንጭህን አዙርለት። አንድ ሰው ሸሚዝህን ለመውሰድ ፈልጎ ቢከስህ፥ ኮትህንም እንዲወስድ ተውለት። አንድ ሰው ‘ከእኔ ጋር ጥቂት መንገድ ሂድ’ ብሎ ቢያስገድድህ፥ አንተ ደግሞ እጥፍ መንገድ ሂድለት። ለሚለምንህ ስጥ፤ ከአንተ መበደር ለሚፈልግ እምቢ አትበለው።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ ‘ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚጠሉአችሁ በጎ አድርጉ፤ ክፉ ለሚያደርጉባችሁና ለሚያሳድዱአችሁ ጸልዩ” እላችኋለሁ። ይህን ብታደርጉ፥ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ። እርሱ ለክፉዎችና ለደጎች ፀሐዩን ያወጣል፤ እንዲሁም ለጻድቃንና ለግፈኞች ዝናቡን ያዘንባል። የሚወዱአችሁን ሰዎች ብቻ ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ኃጢአተኞችስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ለወንድሞቻችሁ ብቻ ሰላምታ የምትሰጡ ከሆነ ምን ብልጫ ያለው ነገር ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ስለዚህ የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተም ፍጹሞች ሁኑ።
የማቴዎስ ወንጌል 5 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 5:27-48
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos