የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 5:27-48

ማቴዎስ 5:27-48 NASV

“ ‘አታመንዝር’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን በምኞት ዐይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከርሷ ጋራ አመንዝሯል። ቀኝ ዐይንህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። ቀኝ እጅህ ቢያሰናክልህ ቈርጠህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። “ ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍችውን ጽሕፈት መስጠት አለበት’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ዝሙት ፈጽማ እስካልተገኘች ድረስ፣ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እንድታመነዝር ያደርጋታል፤ በዚህ ሁኔታ የተፈታችውንም ሴት የሚያገባ ያመነዝራል። “ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘በሐሰት አትማል፤ በጌታ ፊት የማልኸውንም ጠብቅ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ፈጽሞ አትማሉ እላችኋለሁ፤ በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር የእግሩ ማረፊያ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም ቢሆን አትማል፤ ከጠጕራችሁ መካከል አንዲቷን እንኳ ነጭ ወይም ጥቍር ማድረግ አትችሉምና። ስለዚህ ስትነጋገሩ ቃላችሁ፣ ‘አዎን’ ከሆነ ‘አዎን’፤ ‘አይደለም’ ከሆነ ‘አይደለም’ ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ሁሉ ከክፉው የሚመጣ ነውና። “ ‘ዐይን በዐይን፣ ጥርስ በጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ‘ክፉ አድራጊውን ሰው አትቃወሙት’፤ ነገር ግን ቀኝ ጕንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጕንጭህን ደግሞ አዙርለት። አንድ ሰው እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢከስስህ ካባህን ጨምረህ ስጠው። አንድ ሰው አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል የሚያህል ርቀት እንድትሄድ ቢያስገድድህ ዕጥፉን መንገድ ዐብረኸው ሂድ። ለሚለምንህ ስጥ፤ ከአንተም ሊበደር የሚሻውን ፊት አትንሣው። “ ‘ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ እላችኋለሁ፤ እንደዚህም በማድረጋችሁ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ። እርሱ ፀሓዩን ለክፉዎችና ለመልካሞች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል። የሚወድዷችሁን ብቻ ብትወድዱ ምን ዋጋ ታገኛላችሁ? ቀራጮችስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁን ብቻ እጅ የምትነሡ ከሆነ ከሌሎች በምን ትሻላላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ስለዚህ የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች