ማቴዎስ 5:27-48

ማቴዎስ 5:27-48 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“ ‘አታመንዝር’ ዝንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል። ቀኝ ዐይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሃልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና። “ ‘ሚስቱን የሚፈታት ሁሉ የፍችዋን ጽሕፈት ይስጣት’ ተባለ። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል። “ደግሞ ለቀደሙት ‘በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፤ አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው። “ ‘ዐይን ስለ ዐይን ጥርስም ስለ ጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ። ለሚለምንህ ስጥ፤ ከአንተም ይበደር ዘንድ ከሚወደው ፈቀቅ አትበል። “ ‘ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፤ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፤ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።

ማቴዎስ 5:27-48 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“ ‘አታመንዝር’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን በምኞት ዐይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከርሷ ጋራ አመንዝሯል። ቀኝ ዐይንህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። ቀኝ እጅህ ቢያሰናክልህ ቈርጠህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። “ ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍችውን ጽሕፈት መስጠት አለበት’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ዝሙት ፈጽማ እስካልተገኘች ድረስ፣ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እንድታመነዝር ያደርጋታል፤ በዚህ ሁኔታ የተፈታችውንም ሴት የሚያገባ ያመነዝራል። “ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘በሐሰት አትማል፤ በጌታ ፊት የማልኸውንም ጠብቅ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ፈጽሞ አትማሉ እላችኋለሁ፤ በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር የእግሩ ማረፊያ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም ቢሆን አትማል፤ ከጠጕራችሁ መካከል አንዲቷን እንኳ ነጭ ወይም ጥቍር ማድረግ አትችሉምና። ስለዚህ ስትነጋገሩ ቃላችሁ፣ ‘አዎን’ ከሆነ ‘አዎን’፤ ‘አይደለም’ ከሆነ ‘አይደለም’ ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ሁሉ ከክፉው የሚመጣ ነውና። “ ‘ዐይን በዐይን፣ ጥርስ በጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ‘ክፉ አድራጊውን ሰው አትቃወሙት’፤ ነገር ግን ቀኝ ጕንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጕንጭህን ደግሞ አዙርለት። አንድ ሰው እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢከስስህ ካባህን ጨምረህ ስጠው። አንድ ሰው አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል የሚያህል ርቀት እንድትሄድ ቢያስገድድህ ዕጥፉን መንገድ ዐብረኸው ሂድ። ለሚለምንህ ስጥ፤ ከአንተም ሊበደር የሚሻውን ፊት አትንሣው። “ ‘ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ እላችኋለሁ፤ እንደዚህም በማድረጋችሁ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ። እርሱ ፀሓዩን ለክፉዎችና ለመልካሞች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል። የሚወድዷችሁን ብቻ ብትወድዱ ምን ዋጋ ታገኛላችሁ? ቀራጮችስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁን ብቻ እጅ የምትነሡ ከሆነ ከሌሎች በምን ትሻላላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ስለዚህ የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።

ማቴዎስ 5:27-48 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል። ቀኝ ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሃልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና። ሚስቱን የሚፈታት ሁሉ የፍችዋን ጽሕፈት ይስጣት ተባለ። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል። ደግሞ ለቀደሙት፦ በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፥ አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው። ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ። ለሚለምንህ ስጥ፥ ከአንተም ይበደር ዘንድ ከሚወደው ፈቀቅ አትበል። ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ።

ማቴዎስ 5:27-48 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ ‘አታመንዝር!’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ‘ሴትን ተመልክቶ የተመኛት ሁሉ፥ ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመነዘረ’ እላችኋለሁ። የቀኝ ዐይንህ ለኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ አውጥተህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። ቀኝ እጅህ የኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ ቈርጠህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። “ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍችዋን ማስረጃ ይስጣት” ተብሏል። እኔ ግን “በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በቀር፥ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እንድታመነዝር ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል” እላችኋለሁ። ደግሞም ለቀደሙ ሰዎች “በሐሰት አትማሉ፤ ነገር ግን መሐላችሁን ለጌታ ፈጽሙ” የተባለውን ሰምታችኋል። እኔ ግን “በፍጹም አትማሉ” እላችኋለሁ። ሰማይ የእግዚአብሔር ዙፋን ስለ ሆነች፥ በሰማይም ቢሆን፥ ምድርም የጌታ እግር ማሳረፊያ ስለ ሆነች በምድርም አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ስለ ሆነች በኢየሩሳሌምም አትማሉ፤ ከጸጒርህ አንዲቱን እንኳ ነጭ ወይም ጥቊር ማድረግ ስለማትችል በራስህም ቢሆን አትማል። ስለዚህ ንግግራችሁ “አዎ” ከሆነ “አዎ፥” ወይም “አይደለም” ከሆነ “አይደለም” ይሁን። ከዚህ የተረፈ ቃል ግን ከሰይጣን ነው። “ ‘ዐይን ስለ ዐይን፥ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፤ ክፉ የሚያደርግባችሁን ሰው አትበቀሉት። ነገር ግን ቀኝ ጒንጭህን ለሚመታህ፥ ግራ ጒንጭህን አዙርለት። አንድ ሰው ሸሚዝህን ለመውሰድ ፈልጎ ቢከስህ፥ ኮትህንም እንዲወስድ ተውለት። አንድ ሰው ‘ከእኔ ጋር ጥቂት መንገድ ሂድ’ ብሎ ቢያስገድድህ፥ አንተ ደግሞ እጥፍ መንገድ ሂድለት። ለሚለምንህ ስጥ፤ ከአንተ መበደር ለሚፈልግ እምቢ አትበለው።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ ‘ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚጠሉአችሁ በጎ አድርጉ፤ ክፉ ለሚያደርጉባችሁና ለሚያሳድዱአችሁ ጸልዩ” እላችኋለሁ። ይህን ብታደርጉ፥ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ። እርሱ ለክፉዎችና ለደጎች ፀሐዩን ያወጣል፤ እንዲሁም ለጻድቃንና ለግፈኞች ዝናቡን ያዘንባል። የሚወዱአችሁን ሰዎች ብቻ ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ኃጢአተኞችስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ለወንድሞቻችሁ ብቻ ሰላምታ የምትሰጡ ከሆነ ምን ብልጫ ያለው ነገር ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ስለዚህ የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተም ፍጹሞች ሁኑ።

ማቴዎስ 5:27-48 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“‘አታመንዝር’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወደ ሴት አይቶ የተመኛት ሁሉ ከወዲሁ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል። ቀኝ ዐይንህ ብታሰናክልህ ከአንተ አውጥተህ ጣላት፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱ ክፍል ቢጠፋ ይሻልሃልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ከአንተ ቆርጠህ ጣላት፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱ ክፍል ቢጠፋ ይሻልሃልና። “‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ ወረቀት ጽሕፈት ይስጣት’ ተብሏል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል። “ደግሞም ለቀደሙት ‘በውሸት አትማል ነገር ግን የማልኸውንም ለጌታ ስጥ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በፍጹም አትማሉ፤ በሰማይ አትማሉ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አትማሉ የእግሩ ማረፊያ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አትማሉ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፤ አንዲቱን ጠጉር እንኳ ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ስለዚህ ንግግራችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከእነዚህ የተረፈ ግን ከክፉው ነው። “‘ዐይን ስለ ዐይን፥ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ክፉውን አትቃወሙት፤ ነገር ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ ሊከስህ ፈልጎ እጀ ጠባብህን ሊወስድ የፈለገ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ እንድትሄድ ቢያስገድድህ፥ ሁለት ምዕራፍ ከእርሱ ጋር ሂድ። ለሚጠይቅህ ስጥ፤ ከአንተ ሊበደር ከሚፈልገው ፊትህን አታዙር። “‘ባልንጀራህን ውደድ፥ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ ይህን በማድረግ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች እንድትሆኑ ነው፤ እርሱ ለክፉዎችና ለደጎች ፀሐዩን ያወጣልና፥ ለጻድቃንና ለኃጥኣንም ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ሽልማት ታገኛላችሁ? ቀራጮች እንኳ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁን ብቻ ሰላም የምትሉ ከሆነ ምን የበለጠ ነገር ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ስለዚህ የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።