የሉቃስ ወንጌል 22:26-38

የሉቃስ ወንጌል 22:26-38 አማ54

እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን። በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው? የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ። ነገር ግን እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በአሥራ ሁለቱ በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ። ጌታም፦ ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ። እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ ወደ ወኅኒም ወደ ሞትም ከአንተ ጋር ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ አለው። እርሱ ግን፦ ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ እንዳታውቀኝ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዛሬ ዶሮ አይጮኽም አለው። ደግሞም፦ ያለ ኮረጆና ያለ ከረጢት ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ አንዳች ጐደለባችሁን? አላቸው። እነርሱም፦ አንዳች እንኳ አሉ። እርሱም፦ አሁን ግን ኮረጆ ያለው ከእርሱ ጋር ይውሰድ፥ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ። እላችኋለሁና፥ ይህ፦ ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ሊፈጸም ግድ ነው፤ አዎን፥ ስለ እኔ የሚሆነው አሁን ይፈጸማልና አላቸው። እነርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ አሉት። እርሱም፦ ይበቃል አላቸው።