ሉቃስ 22:26-38

ሉቃስ 22:26-38 NASV

በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይሁን፤ ይልቁን ከእናንተ ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ፣ ገዥ የሆነም እንደ አገልጋይ ይሁን። ለመሆኑ፣ በማእድ ከተቀመጠና ቆሞ ከሚያስተናግድ ማን ይበልጣል? በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ ያለሁት እንደ አንድ አገልጋይ ነው። እናንተም ሳትለዩኝ በመከራዬ ጊዜ በአጠገቤ የቆማችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም ደግሞ በመንግሥቴ እሾማችኋለሁ፤ ይኸውም በመንግሥቴ ከማእዴ እንድትበሉና እንድትጠጡ፣ ደግሞም በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ እንድትፈርዱ ነው።” ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ስምዖን፣ ስምዖን ሆይ፤ እነሆ፤ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።” ስምዖንም፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ ከአንተ ጋራ ወህኒ ለመውረድም፣ ለመሞትም ዝግጁ ነኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ እልሃለሁ፤ ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ፣ አላውቀውም ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ከዚያም ኢየሱስ፣ “ያለ ኰረጆ፣ ያለ ከረጢትና ያለ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ምንም አልጐደለብንም” አሉ። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ግን ኰረጆም፣ ከረጢትም ያለው ሰው ይያዝ፤ ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ይግዛ። እላችኋለሁና፤ ‘ከዐመፀኞች ጋራ ተቈጠረ’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ መፈጸም አለበት፤ ስለ እኔ የተጻፈው ፍጻሜው በርግጥ ደርሷል።” ደቀ መዛሙርቱም፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆ፤ ሁለት ሰይፎች እዚህ አሉ” አሉት። እርሱም፣ “ይበቃል” አላቸው።