የሉቃስ ወንጌል 22:26-38

የሉቃስ ወንጌል 22:26-38 አማ05

እናንተ ግን እንደ እነርሱ ልትሆኑ አይገባም፤ ይልቅስ ከእናንተ መካከል ትልቅ የሆነ እንደ ትንሽ ይሁን፤ አለቃ የሆነም እንደ አገልጋይ ይሁን። በማእድ ተቀምጦ ከሚመገበውና ቆሞ ከሚያገለግለው የትኛው ነው ትልቅ? ትልቅ የሚባለው በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደ አገልጋይ ነኝ። እናንተ በመከራዬ ጊዜ ሁሉ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ ቈይታችኋል። ስለዚህ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም እናንተን እሾማችኋለሁ። በመንግሥቴም በማእድ ተቀምጣችሁ ትበላላችሁ፤ ትጠጣላችሁ፤ በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱም የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ስምዖን! ስምዖን! እነሆ፥ ገበሬ ስንዴውን ከገለባ አበጥሮ እንደሚለይ እንዲሁም ሰይጣን እናንተን ሊያበጥራችሁ ፈለገ። ነገር ግን የአንተ እምነት እንዳይጠፋ እኔ ለአንተ እጸልያለሁ፤ እንደገና በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና።” ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ለእስራትም ሆነ ለሞት ከአንተ ጋር አብሬ ለመሄድ ዝግጁ ነኝ!” አለ። ኢየሱስ ግን “ጴጥሮስ ሆይ! ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ‘አላውቀውም’ ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እልሃለሁ” አለው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “የገንዘብ ቦርሳ፥ ከረጢት፥ ጫማም ሳትይዙ በላክኋችሁ ጊዜ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” አላቸው። እነርሱም “ምንም የጐደለብን ነገር አልነበረም” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ግን የገንዘብ ቦርሳም ሆነ ከረጢት ያለው ይያዝ፤ ሰይፍም የሌለው ልብሱን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ። ስለ እኔ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም ስለሚገባው ‘ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ’ የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል በእኔ ላይ መፈጸም አለበት እላችኋለሁ።” ደቀ መዛሙርቱም “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ እዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ!” አሉት። እርሱም “ይበቃል!” አላቸው።