የሉቃስ ወንጌል 22
22
1ፋሲካም የሚባለው የቂጣ በዓል ቀረበ። 2የካህናት አለቆችና ጻፎችም እንዴት እንዲያጠፉት ይፈልጉ ነበር፤ ሕዝቡን ይፈሩ ነበርና።
3ሰይጣንም ከአሥራ ሁለቱ ቍጥር አንዱ በነበረው የአስቆሮቱ በሚባለው በይሁዳ ገባ፤ 4ሄዶም እንዴት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ከካህናት አለቆችና ከመቅደስ አዛዦች ጋር ተነጋገረ። 5እነርሱም ደስ አላቸው፥ ገንዘብም ሊሰጡት ተዋዋሉ። 6እሺም አለ፥ ሕዝብም በሌለበት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር።
7ፋሲካንም ሊያርዱበት የሚገባው የቂጣ በዓል ደረሰ፤ 8ጴጥሮስንና ዮሐንስንም፦ ፋሲካን እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን ብሎ ላካቸው። 9እነርሱም፦ ወዴት እናዘጋጅ ዘንድ ትወዳለህ? አሉት። 10እርሱም አላቸው፦ እነሆ፥ ወደ ከተማ ስትገቡ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደ ሚገባበት ቤት ተከተሉት፤ 11ለባለቤቱም፦ መምህሩ፦ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል በሉት፤ 12ያም በደርብ ላይ ያለውን የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን። 13ሄደውም እንዳላቸው አገኙና ፋሲካን አሰናዱ።
14ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። 15እርሱም፦ ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ 16እላችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም አላቸው። 17ጽዋንም ተቀበለ አመስግኖም፦ ይህን እንካችሁ በመካከላችሁም ተካፈሉት፤ 18እላችኋለሁና፥ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም አለ። 19እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ ቆርሶም ሰጣቸውና፦ ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። 20እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ፦ ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው። 21ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ እጅ እነሆ በማዕድ ከእኔ ጋር ናት። 22የሰው ልጅስ እንደ ተወሰነው ይሄዳል፥ ነገር ግን አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት። 23ከእነርሱም ይህን ሊያደርግ ያለው ማን እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር።
24ደግሞም ማናቸውም ታላቅ ሆኖ እንዲቈጠር በመካከላቸው ክርክር ሆነ። 25እንዲህም አላቸው፦ የአሕዛብ ነገሥታት ይገዙአቸዋል፥ በላያቸውም የሚሠለጥኑት ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ። 26እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን። 27በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው? የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ።
28ነገር ግን እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ 29-30አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በአሥራ ሁለቱ በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ።
31ጌታም፦ ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ 32እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ። 33እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ ወደ ወኅኒም ወደ ሞትም ከአንተ ጋር ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ አለው። 34እርሱ ግን፦ ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ እንዳታውቀኝ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዛሬ ዶሮ አይጮኽም አለው።
35ደግሞም፦ ያለ ኮረጆና ያለ ከረጢት ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ አንዳች ጐደለባችሁን? አላቸው። እነርሱም፦ አንዳች እንኳ አሉ። 36እርሱም፦ አሁን ግን ኮረጆ ያለው ከእርሱ ጋር ይውሰድ፥ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ። 37እላችኋለሁና፥ ይህ፦ ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ሊፈጸም ግድ ነው፤ አዎን፥ ስለ እኔ የሚሆነው አሁን ይፈጸማልና አላቸው። 38እነርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ አሉት። እርሱም፦ ይበቃል አላቸው።
39ወጥቶም እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ደግሞ ተከተሉት። 40ወደ ስፍራውም ደርሶ፦ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ አላቸው። 41ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፥ ተንበርክኮም፦ አባት ሆይ፥ 42ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። 43ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታ መልአክ ታየው። 44በፍርሃትም ሲጣጣር አጽንቶ ይጸልይ ነበር፤ ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ። 45ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣና ከኀዘን የተነሣ ተኝተው ሲያገኛቸው፦ 46ስለ ምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ አላቸው።
47ገናም ሲናገር እነሆ፥ ሰዎች መጡ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱም ይሁዳ የሚባለው ይቀድማቸው ነበር፥ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ቀረበ። 48ኢየሱስ ግን፦ ይሁዳ ሆይ፥ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን? አለው። 49በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ በሰይፍ እንምታቸውን? አሉት። 50ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው። 51ኢየሱስ ግን መልሶ፦ ይህንስ ፍቀዱ አለ፤ ጆሮውንም ዳስሶ ፈወሰው። 52ኢየሱስም ወደ እርሱ ለመጡበት ለካህናት አለቆችና ለመቅደስ አዛዦች ለሽማግሌዎችም፦ ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ወጣችሁን? 53በመቅደስ ዕለት ዕለት ከእናንተ ጋር ስሆን እጆቻችሁን አልዘረጋችሁብኝም፤ ይህ ግን ጊዜያችሁና የጨለማው ሥልጣን ነው አላቸው።
54ይዘውም ወሰዱት ወደ ሊቀ ካህናት ቤትም አገቡት፤ ጴጥሮስም ርቆ ይከተለው ነበር። 55በግቢ መካከልም እሳት አንድደው በአንድነት ተቀምጠው ሳሉ ጴጥሮስ በመካከላቸው ተቀመጠ። 56በብርሃኑም በኩል ተቀምጦ ሳለ አንዲት ገረድ አየችውና ትኵር ብላ፦ ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለች። 57እርሱ ግን፦ አንቺ ሴት፥ አላውቀውም ብሎ ካደ። 58ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላው አይቶት፦ አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ አለው። ጴጥሮስ ግን፦ አንተ ሰው፥ እኔ አይደለሁም አለ። 59አንድ ሰዓትም የሚያህል ቆይቶ ሌላው አስረግጦ፦ እርሱ የገሊላ ሰው ነውና በእውነት ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለ። 60ጴጥሮስ ግን፦ አንተ ሰው፥ የምትለውን አላውቅም አለ። ያን ጊዜም ገና ሲናገር ዶሮ ጮኸ። 61ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም፦ ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እንዳለው የጌታ ቃል ትዝ አለው። 62ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።
63ኢየሱስንም የያዙት ሰዎች ይዘብቱበትና ይደበድቡት ነበር፤ 64ሸፍነውም ፊቱን ይመቱት ነበርና፦ በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር እያሉ ይጠይቁት ነበር። 65ሌላም ብዙ ነገር እየተሳደቡ በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር።
66በነጋም ጊዜ የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች ጻፎችም ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱትና 67ክርስቶስ አንተ ነህን? ንገረን አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ብነግራችሁ አታምኑም፤ 68ብጠይቅም አትመልሱልኝም አትፈቱኝምም። 69ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኃይል ቀኝ ይቀመጣል። 70ሁላቸውም፦ እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን? አሉት። እርሱም፦ እኔ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ አላቸው። 71እነርሱም፦ ራሳችን ከአፉ ሰምተናልና ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል? አሉ።
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 22: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ