እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲህ ባላቸው፦ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ። ከእናንተ ሰው ሁሉ እናቱንና አባቱን ይፍራ፥ ሰንበታቴንም ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። ወደ ጣዖታትም ዘወር አትበሉ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም የአማልክት ምስሎች ለእናንተ አታድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። የደኅንነትንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ስትሰዉ እርሱን ደስ እንድታሰኙበት ሠውት። በምትሠውት ቀንና በነጋው ይበላል፤ እስከ ሦስተኛውም ቀን ድረስ ቢተርፍ በእሳት ይቃጠላል። በሦስተኛውም ቀን ቢበላ ጸያፍ ነው፥ ደስም አያሰኝም፤ የበላውም ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን ነገር አርክሶአልና ኃጢአቱን ይሸከማል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። የምድራችሁንም መከር በሰበሰባችሁ ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር ፈጽማችሁ አትጨዱ፥ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ። የወይንህንም ቃርሚያ አትቃርም፥ የወደቀውንም የወይንህን ፍሬ አትሰብስብ፤ ለድሆችና ለእንግዶች ተወው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። አትስረቁ፥ አትካዱም፥ ከእናንተም እርስ በርሳችሁ ሐሰት አትነጋገሩ። በስሜም በሐሰት አትማሉ፥ የአምላካችሁንም ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። በባልንጀራህ ግፍ አታድርግ፥ አትቀማውም። የሞያተኛው ዋጋ እስከ ነገ ድረስ በአንተ ዘንድ አይደርብህ። ደንቆሮውን አትስደብ፥ በዕውርም ፊት ዕንቅፋት አታድርግ፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። በፍርድ ዓመፃ አታድርጉ፤ ለድሀ አታድላ፥ ባለ ጠጋውንም አታክብር፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በእውነት ፍረድ። በሕዝብህ መካከል በሸንጋይነት አትዙር፤ በባልንጀራህም ደም ላይ አትቁም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ በባልነጀራህ ምክንያት ኃጢአት እንዳይሆንብህ ገሥጸው። አትበቀልም፥ በሕዝብህም ልጆች ቂም አትያዝ፥ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
ኦሪት ዘሌዋውያን 19 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 19:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች