ዘሌዋውያን 19:1-18

ዘሌዋውያን 19:1-18 NASV

እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ጉባኤ እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ። “ ‘ከእናንተ እያንዳንዱ እናቱንና አባቱን ያክብር፤ ሰንበታቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “ ‘ወደ ጣዖታት ዘወር አትበሉ፤ ወይም ከቀለጠ ብረት ለራሳችሁ አማልክት አትሥሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “ ‘የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በምታቀርቡበት ጊዜ፣ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁ አድርጋችሁ አቅርቡ። መሥዋዕቱም ባቀረባችሁት ዕለት ወይም በማግስቱ ይበላ፤ እስከ ሦስተኛው ቀን የተረፈ ማንኛውም ነገር ይቃጠል። በሦስተኛውም ቀን ቢበላ ርኩስ ነው፤ ተቀባይነትም የለውም። ከመሥዋዕቱ የሚበላ ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን ነገር አርክሷልና ይጠየቅበታል፤ ያም ሰው ከወገኑ ተለይቶ ይጥፋ። “ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ በዕርሻችሁ ዳርና ዳር ያለውን አትጨዱ፤ ቃርሚያውንም አትልቀሙ። የወይንህን ዕርሻ አትቃርም፤ የወደቀውንም አትልቀም፤ ለድኾችና ለመጻተኞች ተውላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “ ‘አትስረቁ። “ ‘አትዋሹ። “ ‘ከእናንተ አንዱ ሌላውን አያታልል። “ ‘በስሜ በሐሰት አትማሉ፤ በዚህም የአምላካችሁን ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ ‘ባልንጀራህን አታጭበርብር፤ አትቀማውም። “ ‘የሙያተኛውን ደመወዝ ሳትከፍል አታሳድር። “ ‘ደንቈሮውን አትርገም፤ በዐይነ ስውሩም ፊት ዕንቅፋት አታኑር፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ ‘ፍርድ አታዛቡ፤ ለድኻው አታድላለት፤ ለትልቁም ሰው ልዩ አክብሮት አትስጥ፤ ለብርቱው አታድላ፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በጽድቅ ፍረድ። “ ‘በሕዝብህ መካከል ሐሜት አትንዛ። “ ‘የባልንጀራህን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ነገር አታድርግ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “ ‘ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ የበደሉ ተካፋይ እንዳትሆን ባልንጀራህን በግልጽ ገሥጸው። “ ‘ወገንህን አትበቀል፤ ወይም በመካከልህ ከሚኖር በማንኛውም ሰው ላይ ቂም አትያዝ፤ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።