ኦሪት ዘሌዋውያን 19:1-18

ኦሪት ዘሌዋውያን 19:1-18 አማ05

እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ሕዝብ ይህን ንገር፦ ‘እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ እናትና አባቱን ያክብር፤ እኔ ባዘዝኩት መሠረት ሰንበትን ይጠብቅ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ “ወደ ጣዖት አምልኮ አትመለሱ፤ ወይም ብረት አቅልጣችሁ አማልክትን አትሥሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “ለአንድነት መሥዋዕት አንድ ዐይነት እንስሳ በምተሠዉበት ጊዜ፥ የሰጠኋችሁን ሥርዓት ጠብቁ፤ መሥዋዕቱም በእኔ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል። ሥጋውም እንስሳው በታረደበት ዕለት ወይም በማግስቱ መበላት አለበት፤ እስከ ሦስተኛው ቀን ተርፎ የቈየ ማናቸውም ሥጋ በእሳት ይቃጠል። በሦስተኛው ቀን ቢበላ ርኩስ ነው፤ መሥዋዕቱም ተቀባይነት አይኖረውም፤ ከእርሱ የሚበላ ማንም ሰው ለእኔ የተቀደሰውን እንደ ተራ ነገር በመቊጠሩ በደል ይሆንበታል፤ ከሕዝቤም ይለያል። “የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ በእርሻችሁ ድንበር ያለውን እህል አትጨዱ፤ ስታጭዱ የቀረውንም ቃርሚያ ለመሰብሰብ ወደ ኋላ አትመለሱ፤ የወይን መከርህንም ስትሰበስብ በሐረጉ ላይ ተሰውሮ የቀረውን ወይም በመሬት ላይ የረገፈውን የወይን ዘለላ አጥርተህ ለመልቀም እንደገና ወደ ኋላ አትመለስ፤ ይህን ሁሉ ለድኾችና ለመጻተኞች ተውላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “አትስረቁ፤ አታታሉ፤ ውሸት አትናገሩ፤ በስሜ በሐሰት አትማሉ፤ የአምላካችሁንም ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። “በጐረቤትህ ላይ ግፍ አትሥራ፤ ወይም ንብረቱን አትቀማው፤ ቀጥረህ የምታሠራውን ሰው ደመወዝ ለአንድ ሌሊት እንኳ በአንተ ዘንድ አይደር። ደንቆሮውን አትስደብ፤ ዐይነ ዕውሩንም ለማሰናከል በፊቱ እንቅፋት አታኑር፤ አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ። “የፍርድ ውሳኔ በምትሰጡበት ጊዜ ታማኞችና ትክክለኞች ሁኑ፤ ለሁሉም በትክክል ፍረዱ እንጂ ለድኻው ስለ ድኽነቱ አድልዎ አታድርጉለት፤ ባለጸጋውንም ስለ ሀብቱ ብዛት አትፍሩት። በሕዝብህ መካከል እየዞርክ የስም አጥፊነት ወሬ አታሰራጭ፤ ሰውን ወደ ሞት አደጋ የሚያደርስ ምንም ነገር አታድርግ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ። “ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ በእርሱ ምክንያት ኃጢአት እንዳይሆንብህ ገሥጸው። መበቀል አትፈልግ፤ በወገንህ በማንም ላይ ቂም አትያዝ፤ ነገር ግን ጐረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።