መቅደሱንም፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ መሠዊያውንም ማስተስረይ ከፈጸመ በኋላ ሕያውን ፍየል ያቀርባል፤ አሮንም ሁለቱን እጆቹን በሕያው ፍየል ራስ ላይ ይጭናል፥ በላዩም የእስራኤልን ልጆች በደል ሁሉ መተላለፋቸውንም ሁሉ ኃጢአታቸውንም ሁሉ ይናዘዛል፤ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል፥ በተዘጋጀው ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰድደዋል። ፍየሉም ኃጢአታቸውን ሁሉ ወደ በረሀ ይሸከማል፤ ፍየሉንም በምድረ በዳ ውስጥ ይለቅቀዋል። አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባል፥ ወደ መቅደሱም በገባ ጊዜ የለበሰውን የበፍታ ልብስ ያወልቃል፥ በዚያም ይተወዋል፤ በተቀደሰውም ስፍራ ገላውን በውኃ ይታጠባል፥ ሌላውንም ልብስ ለብሶ ይወጣል፤ የእርሱንም የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የሕዝቡንም የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፥ ለራሱም ለሕዝቡም ያስተሰርያል። የኃጢአቱንም መሥዋዕት ስብ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ለመለቀቅ የሚሆነውን ፍየል የወሰደ ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል። ለማስተስረያም እንዲሆን ደማቸው ወደ መቅደስ የገባውን የኃጢአቱን መሥዋዕት ወይፈንና የኃጢአቱን መሥዋዕት ፍየል ከሰፈሩ ወደ ውጭ ያወጡአቸዋል፤ ቁርበታቸውንም፥ ሥጋቸውንም፥ ፈርሳቸውንም በእሳት ያቃጥላሉ። ያቃጠላቸውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል። ይህም የዘላለም ሥርዓት ይሁንላችሁ፤ በዚህ ቀን ትነጹ ዘንድ ማስተስረያ ይሆንላችኋልና በሰባተኛው ወር ከወሩም በአስረኛው ቀን ራሳችሁን አስጨንቍት፥ የአገር ልጅም በእናንተ መካከል የተቀመጠም እንግዳ ሥራን ሁሉ አትሥሩበት፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከኃጢአታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ። ታላቅ ሰንበት ይሆንላችኋል፥ ራሳችሁንም ታዋርዳላችሁ፤ የዘላለም ሥርዓት ነው። የሚቀባውም፥ በአባቱም ፈንታ ካህን ሊሆን የሚካነው ካህን ያስተስርይ፥ የተቀደሰውንም የበፍታ ልብስ ይልበስ፤ ለቅድስተ ቅዱሳንም ያስተስርይ፤ ለመገናኛውም ድንኳን ለመሠዊያውም ያስተስርይ፤ ለካህናቱም ለጉባኤውም ሕዝብ ሁሉ ያስተስርይ። ይህም አንድ ጊዜ በዓመት ለእስራኤል ልጆች ስለ ኃጢአታቸው ሁሉ ያስተሰርይ ዘንድ የዘላለም ሥርዓት ይሁንላችሁ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረገ።
ኦሪት ዘሌዋውያን 16 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 16:20-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች