“አሮን ለቅድስተ ቅዱሳኑ፣ ለመገናኛው ድንኳንና ለመሠዊያው የሚያደርገውን ስርየት ከፈጸመ በኋላ፣ በሕይወት ያለውን ፍየል ወደ ፊት ያቅርበው። ሁለት እጆቹን በሕይወት ባለው ፍየል ራስ ላይ ይጫን፤ በላዩም የእስራኤላውያንን ክፋትና ዐመፅ፣ ኀጢአታቸውንም ሁሉ ይናዘዝበት፤ እነዚህንም በፍየሉ ራስ ላይ ይጫን፤ ፍየሉንም ለዚሁ ተግባር በተመደበ ሰው እጅ ወደ ምድረ በዳ ይስደደው። ፍየሉም ኀጢአታቸውን ሁሉ ተሸክሞ ወደ ምድረ በዳ ይሄዳል፤ ሰውየውም ፍየሉን ሰው ሊኖርበት በማይችል ስፍራ ይልቀቀው። “ከዚህ በኋላ አሮን ወደ መገናኛው ድንኳን ሄዶ፣ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ሊገባ ሲል የለበሳቸውን የበፍታ ልብሶች አውልቆ በዚያው ይተዋቸው። በተቀደሰውም ስፍራ ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ፤ የዘወትር ልብሱንም ይልበስ፤ ከዚያም ወጥቶ ለራሱ ማስተስረያ የሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፤ ለሕዝቡም ማስተስረያ የሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ። የኀጢአት መሥዋዕቱንም በመሠዊያው ላይ ያቃጥል። “የሚለቀቀውን ፍየል የወሰደው ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ሰፈር መግባት ይችላል። ደማቸው ለማስተስረያነት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የገባው፣ ለኀጢአት መሥዋዕት የቀረቡት ወይፈንና ፍየል ከሰፈር ውጭ ተወስደው ቈዳቸው፣ ሥጋቸውና ፈርሳቸው ይቃጠል። እነዚህንም የሚያቃጥል ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ሰፈር መግባት ይችላል። “ለእናንተ የተሰጣችሁ የዘላለም ሥርዐት ይህ ነው፦ ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን ሰውነታችሁን አድክሙ፤ የአገሩ ተወላጅም ሆነ በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ ምንም ሥራ አይሥራ፤ የምትነጹበት ስርየት በዚህች ዕለት ይደረግላችኋልና፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከኀጢአታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ። ይህች የፍጹም ዕረፍት ሰንበት ናት፤ ሰውነታችሁን አድክሙባት፤ የዘላለም ሥርዐት ናት። ሊቀ ካህናት ለመሆን አባቱን በመተካት የተቀባና የተሾመ ካህን ያስተስርይ፤ የተቀደሰውንም የበፍታ ልብስ ይልበስ፤ ለቅድስተ ቅዱሳኑ፣ ለመገናኛው ድንኳንና ለመሠዊያው፣ ለካህናቱና ለማኅበረ ሰቡ ሁሉ ያስተስርይ። “ይህ የዘላለም ሥርዐት ይሁናችሁ፤ በዚህም ሥርዐት መሠረት ለእስራኤላውያን ኀጢአት ሁሉ በዓመት አንድ ጊዜ ስርየት ይደረግ።” እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ ተደረገ።
ዘሌዋውያን 16 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘሌዋውያን 16
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘሌዋውያን 16:20-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች