ኦሪት ዘሌዋውያን 16:20-34

ኦሪት ዘሌዋውያን 16:20-34 አማ05

አሮን ቅድስተ ቅዱሳኑን፥ የመገናኛውን ድንኳን የቀረውን ክፍልና መሠዊያውንም የማንጻት ሥርዓት ከፈጸመ በኋላ ለዐዛዜል የተመረጠውን ፍየል ወስዶ ለእግዚአብሔር ያቀርባል። ሁለት እጆቹን በፍየሉ ራስ ላይ ይጭናል፤ የሕዝቡን ክፋት፥ ኃጢአትና ዐመፅ ሁሉ በመናዘዝ አዛውሮ በፍየሉ ራስ ላይ ያሸክመዋል፤ ከዚህ በኋላ ለዚህ ሥራ የተመደበ ሰው ፍየሉን ነድቶ ወደ በረሓ ይወስደዋል። ፍየሉንም ኃጢአታቸውን ሁሉ ተሸክሞ ምንም ሰው ወደማይኖርበት ምድረ በዳ ወስዶ ይለቀዋል። “አሮንም ወደ ድንኳኑ ይግባ፤ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ከመግባቱ በፊት ለብሶት የነበረውን የክህነት ልብስ አውልቆ፥ በዚያ ይተወው፤ በተቀደሰውም ቦታ ሰውነቱን ታጥቦ የዘወትር ልብሱን ይልበስ፤ ከዚያም ወጥቶ የራሱንና የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተስረይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቅርብ። ኃጢአትን ለማስተስረይ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውንም የእንስሳ ስብ፥ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ የተመረጠውን ፍየል እየነዳ ወደ በረሓ ይዞት ሄዶ የነበረውም ሰው ወደ ሰፈር ከመግባቱ በፊት ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም ይታጠብ። ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ሆነው የቀረቡትና ኃጢአትን ለማስተስረይ ደማቸው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ የነበረው ኰርማና ፍየልም ከሰፈር ወደ ውጪ ተወስደው በእሳት ይቃጠሉ፤ እንዲሁም ቆዳቸው፥ ሥጋቸውና የሆድ ዕቃቸው በሙሉ ይቃጠል። እነርሱንም የሚያቃጥለው ሰው ወደ ሰፈር ከመመለሱ በፊት ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም ይታጠብ። “ከዚህ የሚከተሉትን መመሪያዎች በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ቋሚ ሥርዓት አድርጋችሁ ትጠብቁአቸዋላችሁ፦ ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን እስራኤላውያንና በእነርሱ መካከል የሚኖሩ መጻተኞች ራሳቸውን ማዋረድ አለባቸው፤ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አይሥሩበት። በዚያን ዕለት ንጹሖች እንድትሆኑ የኃጢአት ማስተስረይ ይደረግላችኋል፤ ከዚያም ከኃጢአታችሁ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የነጻችሁ ትሆናላችሁ፤ ያም ዕለት እንደ ሰንበት የዕረፍት ቀን ይሁንላችሁ፤ በዚያን ቀን ራሳችሁን አዋርዱ ይህም የዘለዓለም ሥርዓት ነው። በአባቱ ምትክ ሊቀ ካህናት እንዲሆን ተለይቶ የሚሾመው ካህን የተቀደሰ የክህነት በፍታ ልብሱን ለብሶ ያስተሰርያል። እርሱም ለቅድስተ ቅዱሳኑ፥ ለመገናኛው ድንኳን፥ ለመሠዊያው፥ ለካህናቱና ለጉባኤው ያስተሰርያል። በዓመት አንድ ጊዜ የእስራኤላውያንን ኃጢአት ሁሉ ማስተስረይ የዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል።” በዚህም ዐይነት ሙሴ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ።